የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት ባለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል። እኛም እንደተለመደው በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረትን የሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዮችን በተከታዩ ፅሁፋችን ዳሰናቸዋል።

👉 ከሦስት ነጥብም በላይ ያስመዘገበው ኢትዮጵያ ቡና

በ2ኛ የጨዋታ ሳምንት ከተመለከትናቸው ውጤት ሁሉ ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከነማን የረታበት ጨዋታ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነበር። የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ ግብር በነበረው በዚሁ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከነማን 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ከዚህ ድል በስተጀርባ በልዩነት የሚነሳው ጉዳይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ገና ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ተመስገን ካስትሮ በሙጂብ ቃሲም ላይ በሰራው ጥፋት በኢንተርናሽናል አልቢትር ሊድያ ታደሰ የቀጥታ ቀይ ካርድ ሰለባ ይሆናል፤ ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀሪዎቹን 44 ያክል የሁለተኛ አጋማሽ ደቂቃዎች በ10 ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል።

ይህን ክፍተት ፋሲል ከነማ ይጠቀማል ተብሎ ሲጠበቅ በአንድ ተጫዋች የሚያንሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች እጅግ በሚያስደንቅ መልኩ በሁለተኛው አጋማሽ ሜዳ ላይ የተሻለ ቡድን ሆነው ነው የተገኙት። ከፍ ባለ ፍላጎት ይንቀሳቀሱ የነበሩት ቡናዎች 1-1 ውጤት በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ተጨማሪ ሁለት ግቦችን አክለው 3-1 በሆነ ውጤት ነበር ማሸነፍ የቻሉት። ታድያ ከዚህ ጨዋታ ቡናማዎቹ ያገኙት ነጥብ “ከሦስት ነጥብም በላይ” ነው ቢባል ተገቢ አይደለምን?

👉ፋሲል ከነማ?

ባሳለፍነው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን 1-0 ሲረታ በርካታ አድናቆቶች ሲጎርፍለት የነበረው ቡድን በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በአስር ተጫዋቾች በተጫወተው ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈትን ካስተናገደ ወዲህ በአሰልጣኝ ቡድኑ አባላትና ደጋፊው ከአቅም በታች እየተጫወቱ ነው ባላቸው ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ የትችት በትር እያረፈባቸው ይገኛል።

በተለይ ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ከተመስገን ካስትሮ በቀይ ካርድ መወገድ በኋላ በጨዋታው ላይ እንዲኖራቸው የተጠበቀውን የበላይነት ከማሳየት ይልቅ በኢትዮጵያ ቡና በብዙ መመዘኛዎች ብልጫ ተወስዶባቸው ተስተውሏል። ከቀይ ካርዱ መውጣት በኃላ ከፍተኛ ጫና በኢትዮጵያ ቡና የሜዳ አጋማሽ ፈጥረው ለመጫወት ያሰቡት ፋሲሎች ከኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካዮች በተለይም አሥራት ቱንጆ እግር በሚነሱና ማጥቃቱን ለማገዝ ወደ መሐል ሜዳ ከተጠጋው የፋሲል ከነማ ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍት ሜዳን ታሳቢ ተደርገው የሚጣሉ ኳሶችን ለመቆጣጠር ተቸግረው ተስተውሏል። በዚህ ሒደት ነበር የአቡበከር ናስር ፍፁም ቅጣት ምት የተገኘችው። በተመሳሳይም ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኃላ በተመሳሳይ ለማጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተጫዋቾች ወደ ተጋጣሚ ሜዳ የላኩት ፋሲሎች በኢትዮጵያ ቡናዎች የተሰነዘረባቸውን የመልሶ ማጥቃት ለመከከት በማያሳችል የተበታተነ ቁመና ላይ በመገኘትታቸው የተነሳ ሦስተኛዋን ግብ አስተናግደዋል።

የውድድር ዘመኑ ገና ጅማሮው ላይ ቢሆንም በፋሲል ደረጃ ለዋንጫ ከሚፎካከር ቡድን የቅዳሜው አይነት በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የቁጥር ብልጫ ኖሯቸው ያሳዩት እንቅስቃሴ በደጋፊዎች ዘንድ ፍፁም ተቀባይነት የለውም።

👉 የመጀመሪያ ድላቸውን ያስመዘገቡ ክለቦች

በመጀመሪያው ሳምንት በፋሲል ከነማ መሸነፋቸውን ተከትሎ ጥያቄዎች ተነስቶባቸው የነበሩት ፈረሰኞቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ምንም እንኳን በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸው እንቅስቃሴ ደካማ የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው በመግባት ድሬዳዋ ከተማን 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

በዚህም ጨዋታ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎቹ አዲስ ግደይና ከነዓን ማርክነህ ለአዲሱ ክለባቸው የመጀመሪያ ግባቸውን ሲያስቆጥሩ ከቀናት በፊት ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው አማኑኤል ገ/ሚካኤልም ተቀይሮ በመግባት የመጀመሪያውን ጨዋታ በማድረግ አንድ ፍፁም ቅጣት ምት ማስገኘት ችሏል።

ሌላኛው በዚህ ሳምንት የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘገበው ክለብ ሰበታ ከተማ ነው። በመጀመሪያ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አቻ የተለያዩት ሰበታዎች በዚህኛው ሳምንት ደግሞ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎችን በተመሳሳይ የ3-1 ውጤት ሲረቱ፤ በመጀመሪያ ጨዋታቸው በሀዲያ ሆሳዕና የተረቱት ወላይታ ድቻዎች በዚህኛው ሳምንት ደግሞ አዳማ ከተማን 2-0 በመርታት የመጀመሪያ ሦስት ነጥባቸውን አስመዝገበዋል። ኢትዮጵያ ቡናም ፋሲልን 3-1 በመርታት የዓመቱን የመጀመርያ ድል ያስመዘገበ ቡድን ሆኗል።

👉ዕድሎችን ፈጥሮ በአጥቂዎቹ ድክመት አንገቱን የደፋው ወልቂጤ

በሁለቱም አጋማሾች የወልቂጤ ከተማዎ አንፃራዊ የበላይነት በነበረበት የወልቂጤ ከተማና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው የሱፐር ስፖርት ቁጥራዊ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ወልቂጤ ከተማዎች 7 ግልፅ የሆነ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም አንዱንም መጠቀም ሳይችሉ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ተገደዋል።

በርከት ያሉ ፈጣሪ አማካዮችን በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ያካተቱት ወልቂጤ ከተማዎች እንዳለመታደል ሆኖ በሦስት አጋጣሚዎች የግቡ አግዳሚ እና ቋሚ ካመከኗቸው ኳሶች ውጭ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቻቸው በተለይ አህመድ ሁሴን በተጋጣሚ ሳጥን ከደረሰ ወዲህ ያለው አጨራረስ ደካማነት መነሻ ቡድኑ ከጅማ አባጅፋር ጋር ነጥብ ለመጋራት በቅቷል።

👉 አዳዲስ ተጫዋቾችን የተጠቀመው ጅማ አባጅፋር

ባልተከፈለ የተጫዋቾች ደሞዝ በፌደሬሽኑ አገልግሎት እንዳያገኙ ታግደው የነበሩት ጅማዎች ክፍያውን በመፈፀሙ በክረምቱ ያዘዋወራቸውን ተጫዋቾች በፌደሬሽኑ ማፀደቅ በመቻላቸው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከባለፈው በተለየ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ለውጥን ማድረግ ችለዋል።

ነገር ግን በዚህኛው ሳምንትም ወልቂጤን ሲገጥሙ ያለተጠባባቂ ግብጠባቂ ነበር። ባሳለፍነው ሳምንት አንድ ግብጠባቂ ብቻ በጨዋታ ዕለት ስብስባቸው አካተው አዳማን በገጠሙበት ጨዋታ በ8ኛው ደቂቃ ግብጠባቂያቸውን በቀጥታ ቀይ ካርድ በማጣታቸው የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ተጫዋቻቸውን በግብጠባቂነት ተጠቅመው አራት ግቦችን አስተናግደው መሸነፋቸው አይዘነጋም።

በቅዳሜው የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ክለቡን ከአዳማ ከተማ የተቀላቀለው ጃኮ ፔንዜ የጅማን ግብ እየጠበቀ ጨዋታውን ሲጀምር በተጠባባቂነት ግን የተሰየመ ግብ ጠባቂ አልነበረም። በተጨማሪም ክለቡን የተቀላቀሉት ተከላካዩ ወብሸት ዓለማየሁ፣ አማካዩ ትርታዬ ደመቀ፣ አጥቂው ሙሉቀን ታሪኩ እና ተቀይሮ የገባው ሳዲቅ ሴቾ ለክለባቸው የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

ክለቡ አዲሶቹን ፈራሚዎች ሙሉ በሙሉ ሲያገኝ ተጫዋቾቹ ካላቸው ልምድ በመነሳት በቀጣይ ለአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው መልካም ነግግ ይዞ እንደሚመጣ መገመት ይቻላል።

👉 ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገበው ሀዲያ ሆሳዕና

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እንደገና እየተዋቀረ የሚገው ሆሳዕና በዚህኛው ሳምንትም ከባህር ዳር ከተማ ጠንካራ ፈተና ቢገጥማቸውም በ90ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ገና 2ኛ ሳምንቱ ላይ ቢሆንም ዓምና ውድድሩ እስኪቋረጥ ድረስ ከሰንጠረዡ ግርጌ ሲዳክር የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ዘንድሮ በስብስብ ተቀይሮ የመክፈቻ ሁለቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ሊጉን በ6 ነጥብ እየመራ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ