ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ

የሦስተኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታን የተመለከቱ ሀሳቦችን እንደሚከተለው አንስተናል።

ድሬዳዋ ላይ የመጀመሪያ ድሉን ያሳካው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸነፊነቱን ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን በድሉ ወቅት የአዳዲስ ተጫዋቾቹ ሚና ለነገው ጨዋታ ተነሳሽነትን የሚፈጥርለት ነው። አዲስ ግደይ እና ከነዓን ማርክነህ ግብ ማስቆጠራቸው አማኑኤል ገብረሚካኤል ፍፁም ቅጣት ምት ማስገኘቱ የአዲሶቹን ፈራሚዎች ዝግጁነትን የሚጨምር ክስተት ነበር ፤ በጨዋታው የሪቢን ንግላንዴም እንቅስቃሴም መልካም ነበር። በአጨዋወት ረገድ ግን የነገ ተጋጣሚውን የመሀል ሜዳ ድክመት በመጠቀም ክፍተቶችን የሚፈጥሩ ቅብብሎችን ለመከወን ካልቀለለው በቀር ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም የተሻለ አስፈሪነት የሚታይበት ከቀጥተኛ ኳሶች ነው። በድሬዳዋው ጨዋታ ቡድኑ ከፈጠራቸው ሰባት አጋጣሚዎች ውስጥ አራቱ ከኋላ እና ከመስመር ከተጣሉ ካሶች ሲገኙ አንዱ ከቆመ ኳስ ሌላኛው ደግሞ ከተጋጣሚ የቅብብል ስህተት የመነጨ ነበር። በቅብብሎች ተመስርቶ ግብ አፋፍ ላይ የደረሰው ሙከራም አንድ ብቻ ነበር። ይህንን ስንመለከት በነገው ጨዋታም ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለይም ከግራ መስመር የሚነሱ እና ከኋላ የሚላኩ ኳሶቹ ልዩነት ሊፈጥሩለት ይችላሉ። አሰልጣኝ ማሒር ዴቪድስ “የትኩረት ማጣት በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ ዛሬም ይስተዋል ነበር በዚህም ቅር ተስኝቻለው” ያሉት አስተያየታቸው የመቀረፉ ጉዳይም በነገው ጨዋታ ይጠበቃል።

የመጀመሪያ ጨዋታውን በሁለተኛው ሳምንት ያደረገው ሀዋሳ ከተማ ደካማ አጀማመር ነበር ያደረገው። አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የቀድሞው ክለቡን በአሰልጣኝነት በሚገጥምበት የነገው ጨዋታም ብዙ ደካማ ጎኖችን የማስትካከል ኃላፊነት ተጥሎበታል። በበርካታ ወጣት ተጫዋቾች የተገነባው ቡድኑ ኳስ ቁጥጥርን መሰረት ያደረገ አጨዋወትን ምርጫው ቢያደርግም የሦስቱን የፊት አጥቂዎቹን የኋልዮሽ እንቅስቃሴ ካላስተካከል በጊዮርጊስ አማካዮች የመዋጡ ነገር የሚቀር አይመስልም። ፊተኞቹ ያላቸውን ፍጥነት ያገናዘቡ ኳሶችም በቶሎ ከአማካይ ክፍሉ እንዲገኙም ይጠበቃል። የቡድኑ የኋላ መሰመር ስህተቶችም እንዲሁ ታርመው መምጣት የሚጠቅባቸው ጉዳዮች ናቸው። ከሰበታ ጋር ሁለቱንም የማጥቃት አማካዮቻቸውን ቀይረው ያስወጡት ሀዋሳዎች ምን አልባት ነገም ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች የመቀላቀል እና መሀል ሜዳቸው ላይ የተጫዋቾችን ቁጥር የመጨመር ዕቅድ ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠበቃል። የቡድኑን የፊት መስመር ስል ከማድረግ አንፃርም በጉዳት ያጣቸው ተጫዋቾች መኖራቸው ሌላው የቡድኑ ፈተና መሆኑ የማይቀር ነው።

በጨዋታው በሁለቱም ጨዋታዎች ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ እየታየ የሚገኘው አቤል ያለው ፣ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስተው ጥሩ የተነቀሳቀሱት ከነዓን ማርክነህ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ነገ በጊዮርጊስ በኩል የሚኖራቸው ሚና ተጠባቂ ይሆናል። ሀዋሳዎች የመጀመሪያ የሊጉን ጨዋታ እንዲያደርግ ዕድል የሰጡት ወጣቱ ወንድምአገኝ ኃይሉ እና ቸርነት አወሽ በሀዋሳ በኩል ሊታዩ የሚገባቸው ተጫዋቾች ናቸው።

ጌታነህ ከበደ ከመጠነኛ የጡንቻ መሳሳብ በድጋሚ ወደ ሜዳ የተመለሰ ሲሆን ባህሩ ነጋሽ ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ ሳላሀዲን ሰዒድ ፣ አስቻለው ታመነ እና ሳላሀዲን ባርጊቾ ልምምድ ቢጀምሩም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ናቸው። ከዚህ ወጪ መጠነኛ ጉዳት የገጠመው ደስታ ደሙ የመሰለፍ ጉዳይም እርግጥ አልሆነም።

የመሐል ተከላካያቸው ምኞት ደበበ ለጨዋታው መድረስ ያለየለት ጉዳይ የሆነባቸው ሀዋሳ ከተማዎችም ወጣቶቹ አጥቂዎች ሀብታሙ መኮንን እና ተባረክ ኢፋሞንም በጉዳት ሲያጡ በሰበታ ጨዋታ ጉዳት የገጠመው መስፍን ታፈሰም አይደርስላቸውም። ከዚህ ውጪ አለልኝ አዘነ አምና በተላለፈበት ቅጣት ምክንያት ጨዋታው ሲልፈው ሁለት የቡድኑ ተጫዋቾችም በኮቪድ 19 በመያዛቸው እንደማይኖሩ ማወቅ ችለናል። በአንፃሩ ለሀዋሳ ከተማዎች መልካም ዜና የሚሆነው መጠነኛ ጉዳት የነበረበት ዳንኤል ደርቤ እና ደስታ ዮሃንስ ወደ ሜዳ የሚመለሱ መሆኑ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 40 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 24 እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ 7 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። ቀሪዎቹ 9 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 67 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 31 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

– የሁለቱ ክለቦች ግንኙነት በድምሩ 98 ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን ምናልባትም በነገው ጨዋታ መጠኑ ወደ 100 እንደሚደፍን ይጠበቃል።

– ቡድኖቹ በተሰረዘው የውድድር ዓመት እና በ2011 የደርሶ መልስ ሁለት ጨዋታዎቻቸው ያለ ጎል መለያየታቸው ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

አብዱልከሪም መሀመድ – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ሀይደር ሸረፋ – ሙሉዓለም መስፍን – ከነዓን ማርክነህ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – አቤል ያለው – አዲስ ግደይ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – ምኞት ደበበ – ደስታ ዮሃንስ

ሄኖክ ድልቢ – ጋብርኤል አህመድ – ዘላለም ኢሳይያስ

ብሩክ በየነ – ቸርነት አወሽ – ብርሀኑ በቀለ


© ሶከር ኢትዮጵያ