ሪፖርት| የኃይቆቹ የድል ጉዞ ቀጥሏል

አምስት ግቦች በተመዘገቡበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች ሰራተኞቹን አሸንፈዋል።

ሀይቆቹ ባለፈው ሳምንት ካሸነፈው ስብስባቸው አብዱልበሲጥ ከማልን በአዲሱ አቱላ ለውጠው ሲገቡ ሰራተኞቹ በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ ዋሀብ አዳምስ ፣ አፈወርቅ ሀይሉ እና አቤል ነጋሽን በፍፁም ግርማ ፣ አቡበከር ሳኒ እና ብዙአየሁ ሰይፈ ለውጠው ገብተዋል።

\"\"

ሁለት ተመሳሳይ ቡድኖች ባስመለከተን የመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት እና ሁለቱም ቡድኖች ከመስመር በሚሻሙ ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ነበር።
ገና በአራተኛው ደቂቃም የተጋጣሚ ተጫዋች ወደ ራሱ ግብ በማስቆጠሩ ኃይቆቹ መሪ መሆን ችለዋል። ግቡም ዓሊ ሱሌማን ከቆመ ኳስ ካሻማው በኋላ ሳሙኤል አስፈሪ በስህተት ነክቶት ከመረቡ ጋር መገናኘት ችሏል።


በጨዋታው ከተጋጣሚ የተሻለ ቅንጅት የነበራቸው ሀዋሳዎች በሀያኛው ደቂቃ በሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ወርቃማ ዕድል አባክነዋል። ሙጂብ መድሀኔ በረዥሙ አሻግሮት ኤፍሬም ያመቻቸለት ኳስ ነበር ከግብ ጠባቂው ፊትለፊት ሆኖ ያመከነው። ዘግይተው ወደ ጨዋታ ቅኝት የገቡት ሰራተኞቹ በጌታነህ ከበደ የቆመ ኳስ ሙከራ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዋል። በሀያ ዘጠነኛ ደቂቃም ወልቂጤዎች የቆመ ኳስ አጠቃቀማቸው ፍሬ አፍርቶ በብዙአየሁ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። አማካዩ ጌታነህ ከበደ በጥሩ መንገድ ያሻማው ኳስ ተጠቅሞ ነው በግንባሩ ግብ ያስቆጠረው። ሰራተኞቹ ከግቧ በኋላም በተመሳሳይ በቆመ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበውም ነበር።


ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ መቀዛቀዝ የታየባቸው ሀዋሳዎችም በኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ሁለት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ ላይም ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።


ላውረንስ ላርቴ ከ ከመአዘን የተሻማው ኳስ ተጠቅሞ ባደረገው ሙከራ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ የወልቂጤዎች ብልጫ የታየበት ነበር። ሰራተኞቹ ከብልጫ አልፈውም በተመስገን እና በጌታነህ የቆመ ኳስ አማከኝነት ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ሆኖም በሰባኛው ደቂቃ ብልጫ የተወሰደባቸው ኃይቆቹ በሙጂብ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። ሙጂብ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ነበር ግብ ያስቆጠረው ፤ የወልቂጤው ግብ ጠባቂ የሰራው ስህተት ለግቡ መቆጠር ምክንያት ነበር።


በሰባ ስምንተኛው ደቂቃ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበሩት ሰራተኞቹ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። አጥቂው ብዙአየሁ ሰይፈ ያመቻቸለት ኳስ ተጠቅሞ ነው ግሩም የረዥም ርቀት ግብ ያስቆጠረው። በሰማንያ አራተኛው ደቂቃም ሳሙኤል አስፈሪ በድጋሜ ራሱ ላይ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳዎች ወደ መሪነት ተመልሷል። ተከላካዩ የሀዋሳ ግብ ጠባቂ በረዥሙ የለጋው ኳስ ጨርፎ ነበር ወደ ራሱ ግብ ያስቆጠረው። ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊትም በጨዋታው አንድ ግብ አስቆጥሮ አንድ ግብ የሆነ ኳስ ያመቻቸው ብዙአየሁ በሁለት ቢጫዎች ከሜዳ ወጥቷል። ተመጣጣኝ ፉክክርና አምስት ግቦች እንዲሁም አንድ ተጫዋች ሁለት ኳሶች ወደ ራሱ ግብ ያስቆጠረበት ጨዋታ በሀይቆቹ አሸናፊነት ተጠቋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ የአሰልጣኞች አስተያየት ገብረክርስቶስ ቢራራ \”እንቅስቃሴው ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበር። ዛሬ መሸነፍ አይገባንም ፤ በሁለት የተለጉ ኳሶች ናቸው ግብ የገቡብን።
የትኩረት ማጣት ችግር አለብን\” ካሉ በኋላ ስለ መውረድ አደጋም ተከታዩን ብለዋል። \”ውድድሩ ገና ነው ፤ የመውረድ አደጋ አያስፈራኝም። ከዛ ይልቅ የተጫዋቾቼ ጉዳት ነው የሚያሳስበኝ\” ብለዋል። አሠልጣኝ ዘርዐይ ሙሉ በበኩላቸው \”የፈጠርነው ጫና ግብ እንዲቆጠር ምክንያት ሆኗል ፤ አጨዋወታችን ግን እንዳሰብነው አልነበረም ፤ ተጫዋቾቻችን ላይ የድካም ስሜት አለ\” ብለው \”ውድድሩ ገና ነው እቅዳችን ከፊታችን ያለው ጨዋታ ማሸነፍ ላይ ብቻ ነው\” በማለት ሀሳባቸውን አገባደዋል።