ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀምበሪቾ ዱራሜን ረቷል

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ፈረሠኞቹ በአቤል ያለው እና አማኑኤል ኤርቦ ግቦች ሀምበሪቾ ዱራሜን 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲገናኙ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ሀምበሪቾዎች ሽንፈት ከገጠመው ስብስባቸው ፀጋሰው ድማሙ ፣ ምንያምር ጴጥሮስ እና ዳግም በቀለን በማሳረፍ በምትካቸው ትዕግስቱ አበራ ፣ አቤል ከበደ እና ቶሎሳ ንጉሤን ሲተኩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንጻሩ በወልቂጤ ላይ ድል ካደረገው ስብስባቸው ጉዳት በገጠመው አማኑኤል ተርፉ ብሩክ ታረቀኝን የተኩበት ብቸኛ ለውጣቸው ሆኗል።

9 ሰዓት ሲል በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ይደረግበት እንጂ በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ሀምበሪቾዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲታትሩ ታይተዋል። በዚህ እንቅስቃሴያቸውም 4ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። የኋላሸት ፍቃዱ ሳጥን ውስጥ ያደረገውን ይህን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል በእግሩ መልሶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም በሁለቱም በኩል ክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ እያስመለከተን 23ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ፈረሠኞቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ናትናኤል ዘለቀ ከመሃል ሜዳ በረጅሙ ያቀበለውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ወደ ሳጥን ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው አቤል ያለው በግንባሩ በመግጨት እና የግብ ጠባቂውን ምንታምር መለሰ እጅ በመጣስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ጨዋታውን መምራት በጀመሩበት ቅጽበት በቀጣይ አምስት ደቂቃዎች እጅግ ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ጊዮርጊሶች 27ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው አቤል ያለው በድጋሚ በግንባሩ ቢገጭም በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል።

የመጨረሻ ኳሳቸው ደካማ ይሁን እንጂ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ሀምበሪቾዎች 28ኛው ደቂቃ ላይ በአፍቅሮት ሰለሞን አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ ጨዋታውም በሁለቱም በኩል ረፍት የለሽ እንቅስቃሴዎች እየተደረበት ቀጥሎ 42ኛው ደቂቃ ላይ ሀምበሪቾዎች አቻ የሚያደርጋቸውን ወርቃማ ዕድል አግኝተው ነበር። ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ የጊዮርጊሱ የመሃል ተከላካይ ብሩክ ታረቀኝ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት በረከት ወንድሙ ሲመታ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል በድንቅ ቅልጥፍና መልሶበት የግብ ዕድላቸው ባክኗል።

ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራቱ በፊት በቀሩ 5 ደቂቃዎች ውስጥም  ፈረሠኞቹ ሁለት የግብ ሙከራዎችን በአማኑኤል ኤርቦ አማካኝነት ማድረግ ችለው ነበር። በዚህም አጥቂው በቅድሚያ 43ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ዓየር ላይ እንዳለ በመምታት ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ረሱ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት በገባው ኳስ ያደረጋቸውን ሙከራዎች ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ ይዟቸዋል።

ከዕረፍት መልስ እንደ መጀመሪያ አጋማሽ የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች ሁሉ በአጋማሹ የመጀመሪያ አምስት ደቂቃዎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ጊዮርጊሶች በአቤል ያለው አማካኝነት ሁለት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተለይም 49ኛው ደቂቃ ላይ ፈጣኑ አጥቂ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ በግሩም ብቃት መልሶበታል።

በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እየተቀዛቀዙ የመጡት ሀምበሪቾዎች 53ኛው ደቂቃ ላይ በቁጥር በዛ ብለው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። በዚሁ እንቅስቃሴያቸውም በፍቃዱ አስረሳኸኝ ወደ ግብ ሞክሮት የመሃል ተከላካዩ ብሩክ ታረቀኝ ተደርቦ የመለሰበት ሙከራ ተጠቃሽ ነው።

በቀጣዮቹ 20 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ብልጫውን የወሰዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 63ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ረመዳን የሱፍ ከዳዊት ተፈራ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ ሲመልስበት ኳሱን ሲመለስ ያገኘው አማኑኤል ኤርቦ በቀላሉ አስቆጥሮታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም የጊዮርጊስ ዋና የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ የነበረው አማኑኤል ኤርቦ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው አቤል ያለው ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ አግዶበታል።

ጨዋታው በመሃል እየተቀዛቀዘ ሄዶ ግለት በጨመረበት የመጨረሻ 10 ደቂቃ ውስጥ በሁለቱም በኩል ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር። 83ኛው ደቂቃ ላይ በፈረሠኞቹ በኩል ተቀይሮ የገባው አላዛር ሳሙኤል ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ የቀነሰለትን ኳስ ያገኘው አብሮት ተቀይሮ የገባው ሀብቶም ገ/እግዚአብሔር ጥሩ የግብ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ በጥሩ ብቃት መልሶበታል።

ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም አብዱልሰላም የሱፍ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ሲመልስበት ኳሱን ያገኘው አፍቅሮት ሰለሞን ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በድጋሚ በድንቅ ብቃት አግዶበታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመረው 6 ደቂቃ ውሰጥም 3ኛው ደቂቃ ላይ በሀምበሪቾ በኩል ተቀይሮ የገባው ዳግም በቀለ ከሳጥን ውጪ በግሩም አጨራረስ መሬት ለመሬት መትቶ በማስቆጠር ሀምበሪቾን ለባዶ ከመሸነፍ አድኗል። ይህም የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።