ሪፖርት | ፈረሠኞቹ ኃይቆቹን በሰፊ የግብ ልዩነት ረተዋል

በሣምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ አቤል ያለው በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሦስት ግቦች ሀዋሳ ከተማን 3-0 መርታት ችሏል።

በሣምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲገናኙ ኃይቆቹ በስድስተኛው ሣምንት የስድስተኛ ሣምንት ጨዋታቸው የተራዘመባቸው ፈረሠኞቹ ደግሞ በአምስተኛው ሣምንት በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ 2-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገዋል። ሀዋሳዎች በሙጅብ ቃሲም ቦታ ተባረክ ሒፋሞን ተክተው ሲገቡ ጊዮርጊሶች ደግሞ በሞሰስ ኦዶ ቦታ ቢኒያም በላይን ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ቀን 9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበሩት የመጀመሪያ ጥቂት ደቂቃዎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩት ፈረሠኞቹ 7ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከሳጥን አጠገብ ዳዊት ተፈራ በተከላካዮች መሃል በድንቅ ሁኔታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ፈጥኖ በመውጣት ያገኘው አቤል ያለው ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ (በቺፕ)  መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በተሻለ ግለት የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በሁለቱም መስመሮች በተገኑ ተሾመ እና በቢኒያም በላይ አማካኝነት የሀዋሳን የመከላከል አደረጃጀት ሰብረው ለመግባት ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ ሀዋሳዎች በአንጻሩ ቀምተው በሚያገኙት ኳስ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል።

ጨዋታው 35ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሪነታቸውን ማጠናከር ችለዋል። ግቡም ከመጀመሪያው ግብ ጋር ፍጹም ተመሳሳይ በሆነ ሂደት ሲቆጠር አቤል ያለው ከዳዊት ተፈራ በተመቻለት ኳስ ግብ ጠባቂውን ቻርለስ ሉክዋጎን አልፎ አስቆጥሮታል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸው እና የፈረሠኞቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመመከት ፍጹም የተቸገሩት ሀዋሳዎች 42ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። አቤል ያለው በመድኃኔ ብርሃኔ በተሠራበት ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ አቤል ያለው ግብ አድርጎት በውድድር ዓመቱ ከሀብታሙ ታደሠ በመቀጠል ሐት-ትሪክ የሠራ ሁለተኛው ተጫዋች መሆን ችሏል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጹም የበላይነት እና የሀዋሳ ከተማ ያልተደራጀ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ በመጨረሻ ደቂቃዎች ፈረሠኞቹ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ተጨማሪ ግብ ሊያስቆጥሩ ተቃርበው ነበር። ዳዊት ተፈራ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ኃይቆቹ ኢዮብ ዓለማየሁ ፣ አቤኔዜር ኦቴ እና አቤኔዘር ዮሐንስን በመድኃኔ ብርሃኔ ፣ በአብዱልባሲጥ ከማል እና ሰለሞን ወዴሳ ተክተው ወደ ሜዳ በመግባት ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህም በተከላካይ ስህተት ያገኙትን ኳስ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን ጥቂት በመግፋት እና መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገውን ጥሩ ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ መልሶበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት ሀዋሳዎች 55ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። የጊዮርጊስ ተከላካዮች በሠሩት ስህተት ኳስ ያገኘው ታፈሰ ሰለሞን ወደ ውስጥ ያሻገረለትን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ሳይቆጣጠረው ቀርቶ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በመጠኑ እየተቀዛቀዙ የሄዱት ፈረሠኞቹ በአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራቸውን 56ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ረመዳን የሱፍ ከማዕዘን በተሻማ እና በተከላካዮች በተመለሰ ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ሲመልሰው ኳሱን ብቻውን ሆኖ ያገኘው አቤል ያለው በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወጥቶበት ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በኃይቆቹ ወደ ጨዋታ የመመለስ ጥረት በኩል በማጥቃት እንቅስቃሴው ጥረት ሲያደርግ የነበረው ዓሊ ሱሌይማን 65ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ተከላካዮች ተደርበው አግደውበታል። ያንኑ ኳስ ከማዕዘን ተቀባብለውት ራሱ ዓሊ ሱሌይማን ሙከራ ቢያደርግበትም በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን  በማረጋጋት እና በሚያገኟቸው ክፍተቶች የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ማስኬድ ሲችሉ ሀዋሳዎች በአንጻሩ ያገኟቸውን ወደ ጨዋታ የሚመለሱባቸውን የግብ ዕድሎች ባለመጠቀማቸው እየተቀዛቀዙ ሄደዋል። ሆኖም ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።