የጥሎ ማለፍ ፍፃሜ | መከላከያ ከ ወላይታ ድቻ

የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ፍፃሜ ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም 10:00 ላይ ሲደረግ መከላከያ ከ ወላይታ ድቻ ለዋንጫ ይፋለማሉ፡፡ በ2018 የካፍ ቶታል ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን የሚወክለው ክለብም ይታወቃል፡፡

ሰኞ በተደረጉት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች መከላከያ በባዬ ገዛኸኝ ጎል ታግዞ ወልድያነ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለፍጻሜ ሲቀርብ ወላይታ ድቻ ደግሞ ጅማ አባ ቡናን በአላዛር ፋሲካ ጎል በተመሳሳይ 1-0 በመርታት ለነገው የፍጻሜ ፍልሚያ ቀርቧል፡፡

በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት የተቸገረው መከላከያ እንዳለፉት አመታት ሁሉ በጥሎ ማለፉ ላይ ጥንካሬውን ማሳየቱን ቀጥሏል፡፡ በሁለተኛው ዙር ሀዋሳ ከተማን 2-1 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ ሲያልፍ የአምናው አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመለያ ምቶች አሸንፎ ለግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ችሏል፡፡ በመቀጠልም ወልድያን አሸንፎ ለፍጻሜው ደርሷል፡፡

ወላይታ ድቻ መጥፎ የውድድር ዘመን አሳልፎ በመጨረሻው ሳምንት በሊጉ መቆየቱን ሲያረጋግጥ በጥሎ ማለፉ ግን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ለፍጻሜ የቀረበበትን ጉዞ ማድረግ ችሏል፡፡ በሁለተኛው ዙር አርባምንጭ ከተማን  1-0 ፣ በሩብ ፍጻሜው ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመለያ ምቶች እንዲሁም በግማሽ ፍጻሜው ጅማ አባ ቡናን 1-0 በማሸነፍ ለፍጻሜው ቀርበዋል፡፡

 

እውነታዎች

– መከላከያ በቅርብ አመታት ጠንካራው የጥሎ ማለፍ ቡድን ነው፡፡ የዘንድሮውን ጨምሮ ካለፉት 5 የውድድር አመታት (ከ2005-2009) በአራቱ የፍጻሜ ተፋላሚ ሲሆን ዘንድሮ ለፍጻሜ ሲቀርብ ለተከታታይ 3 ጊዜ ነው፡፡

– መከላከያ ዋንጫውን ካነሳ ለ14ኛ ጊዜ ይሆናል፡፡ ይህም በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛው ነው፡፡

– ባለፉት 10 አመታት የጥሎ ማለፉ ድል ከአዲስ አበባ ክለቦች ወጥቶ አያውቅም፡፡ ወላይታ ድቻ የሚያሸንፍ ከሆነም ሐረር ቢራ (አሁን ሐረር ሲቲ) በ1999 ካሳካው ድል በኋላ የመጀመርያው ይሆናል፡፡

– በ2001 የተመሰረተው ወላይታ ድቻ ለፍጻሜ ሲደርስ ይህ የመጀመርያ ጊዜው ነው፡፡

– ወላይታ ድቻ ዋንጫውን ካነሳ ከ20 አመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ዋንጫ ያነሳ የሶዶ ክለብ ይሆናል፡፡ ለመጀመርያም ለመጨረሻም ጊዜ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ያነሳው የሶዶ ክለብ ወላይታ ቱሳ (1989) ነበር፡፡

– ዘንድሮ በተካሄዱት የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ማለትም በኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ (ሀዋሳ ከተማ) ፣ ከ20 አመት በታች ጥሎ ማለፍ (ሀዋሳ ከተማ) ፣ ከ17 አመት በታች ጥሎ ማለፍ (ወላይታ ድቻ) ሁሉም ዋንጫዎች ወደ ደቡብ ክልል አምርተዋል፡፡ ድቻ ካሸነፈም ሁሉም ዋንጫዎች ወደ ደቡብ ያመራሉ ማለት ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *