የአፍሪካ ቻምፒዮኗ ካሜሩን ከዓለም ዋንጫ ውጪ ሆናለች

ሩሲያ በቀጣዩ አመት ለምታስተናግደው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የአፍሪካ ዞን የምድብ ማጣሪያ አራተኛ ጨዋታዎች ሰኞ ምሽት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡ የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮን ካሜሮሩን ከምንግዜም ባላንጣዋ ናይጄሪያ ጋር አቻ ተለያይታ ከዓለም ዋንጫው መቅረቷን ስታረጋግጥ ሊቢያ ጊኒን 1-0 አሸንፋለች፡፡

በምደብ አንድ በቱኒዚያዋ ከተማ ሞንስቲር ጊኒን ያስተናገደችው ሊቢያ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረ ግብ 1-0 አሸንፋለች፡፡ ሃምዱ አል መስሪ በ36ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ግብ ሊቢያን ለድል ሲያበቃ በ69ኛው ደቂቃ መሃመድ አልጋዲ በሁለት ቢጫ ከሜዳ በመውጣቱ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ሊቢያዎች በ10 ተጫዋቾች ለመጨረስ ተገደዋል፡፡ የላፒ ባንጉራው ጊኒ በሁለተኛው 45 ያገኘውን የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ሁለቱ ሃገራት የምድቡ ግርጌ ላይ እንደመገኘታቸው ማክሰኞ የምድቡ መሪ ቱኒዚያ ኪንሻሳ ላይ ዲ.ሪ.ኮንጎን ማሸነፍ ወይም ነጥብ መጋራት ከቻለች ጊኒ እና ሊቢያ ከማጣሪያው ውጪ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡

ምድቡን ከ2006 የጀርመኑ የዓለም ዋንጫ በኃላ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ትኬቷን ለመቁረጥ ያለመችው ቱኒዚያ በ9 ነጥብ ስትመራ የምድቡ ከባድ ተፎካካሪዋ ዲ.ሪ. ኮንጎ በ6 ትከተላለች፡፡ ጊኒ እና ሊቢያ በእኩል 3 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

በምድብ ሁለት ናይጄሪያ ጎረቤቷ ካሜሩንን ከዓለም ዋንጫ ያሰናበተችበትን ውጤት ያውንዴ ላይ አግኝታለች፡፡ 1-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ከቀናት በፊት ኦዮ ላይ ከባድ ሽንፈት የደረሰበት የካሜሩን ብሄራዊ ቡድን የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡ የማይበገሩት አንበሶች በሱፐር ኢግልሶቹ ላይ ብልጫን ቢወስዱም ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት እንግዶቹ ናቸው፡፡ በ30ኛው ደቂቃ የካሜሩን ተከላካዮች ከግብ ክልላቸው በአግባቡ ማራቅ ያልቻሉትን ኳስ በትርምስ ውስጥ ሆኖ ሲጠባቀው በነበረው ሞሰስ ሳይመን ግብ ጠባቂው ፋብሪስ ኦንዳ ላይ አስቆጥሮ ናይጄሪያ መሪ መሆን ችላለች፡፡ በሁለተኛው 45 ካሜሩን ጫና ፈጥራ መጫወት ያቻለች ሲሆን በ75ኛው ደቂቃ የናይጄሪያው ግብ ጠባቂ ኢኪቹኩ ኢዜንዋ በአርኖድ ጆም ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ቪንሰንት አቡበከር አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በሁለተኛው 45 አቡበከር እና የአፍሪካ ዋንጫው ኮከብ ተጫዋች ክሪያስቲያን ባሶጎግ ተቀይረው መግባታቸው ለካሜሮን የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጨማሪ ጉልበት ቢሆንም በጣሊያን 1990፣ በዩናይትድ ስቴትስ 1994፣ ፈረንሳይ 1998፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ 2002፣ ደቡብ አፍሪካ 2010 እና ብራዚል 2014 የአለም ዋንጫዎች ተሳትፎ ያደረገችው ካሜሩን ከአለም ዋንጫው ቀርታለች፡፡ በሮጀር ሚላ ፊት አውራሪነት በዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ የደረሰች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሃገር የሆነችው ካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫን ጥር ላይ ለአምስተኛ ግዜ (ሁሉንም ዋንጫዎች ከሃገሯ ውጪ ነው ያሸነፈችው፡፡) ካሸነፈች በኋላ በደካማ አቋም ላይ ተገኝታለች፡፡

ከምድብ ሁለት ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የቀረበችው ናይጄሪያ በ10 ነጥብ ስትመራ ኮንስታንታይን ላይ አልጄሪያን የምትገጥመው ዛምቢያ በ4 ትከተላለች፡፡ ካሜሩን በ3 እንዲሁም አልጄሪያ በ1 ቀሪዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ አልጄሪያ ከዛምቢያ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ማሳካት ካልቻለች ከሁለት ተከታታይ የአለም ዋንጫ ተሳትፎዎች በኋላ መውደቋን ታረጋግጣለች፡፡

ውጤቶች
ካሜሮን 1-1 ናይጄሪያ
ሊቢያ 1-0 ጊኒ

ማክሰኞ ነሃሴ 30
15፡30 – ኮንጎ ሪፐብሊክ ከ ጋና (ስታደ ኪንቴሌ 3)
17፡30 – ኮትዲቯር ከ ጋቦን (ስታደ ደ ባኩ)
18፡00 – ቡርኪና ፋሶ ከ ሴኔጋል (ስታደ ኦገስት 4)
18፡30 – ዲ.ሪ. ኮንጎ ከ ቱኒዚያ (ኮምፕሌክስ ኦምኒስፖርትስ ስታደ ደ ማርቲርስ)
19፡00 – ማሊ ከ ሞሮኮ (ስታደ 26 ማርስ)
19፡00 – ደቡብ አፍሪካ ከ ኬፕ ቨርድ (ሞሰስ ማቢዳ ስታዲየም)
20፡00 – ግብፅ ከ ዩጋንዳ (ቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም)
21፡30 – አልጄሪያ ከ ዛምቢያ (ስታደ መሃመድ ሃምላዊ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *