በረከት አዲሱ የቅጣት ይነሳልኝ ደብዳቤ ለኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስገብቷል

በ2009 የውድድር ዘመን ለሲዳማ ቡና እየተጫወተ ባለበት ወቅት ከክለቡ የዲሲፕሊን መመርያ ውጭ የክለቡን ስም እና ዝና የሚያጎድፍ ተግባር ፈጽሟል በሚል በክለቡ መተዳደርያ ደንብ መሰረት ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ በረከት አዲሱን ለሁለት አመት ከየትኛውም እግር ኳሳዊ እንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆን ቅጣት ማስተላለፉ ይታወቃል ።

ከዚህ ቀደም ባቀረብነው ዘገባ በረከት አዲሱ የሰራውን ጥፋት አምኖ ክለቡን ይቅርታ መጠየቁን ሲገልጽ ክለቡ ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ ከአንዴም ሁለቴ ከስህተቱ ያልታረመ በመሆኑ ይቅርታውን እንደማይቀበል በቦርድ የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን መግለፃችን ይታወቃል፡፡

ከበረከት አዲሱ መቀጣት ጋር ተያይዞ አሁን ያለው አዲስ መረጃ ለኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ ማስገባቱ ሲሆን ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን እና በክለብም ለንግድ ባንክ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ለሲዳማ ቡና በምችለው አቅም መጠን ሀገሬንም ክለቦቹን ማገልገሌን በማሰብ ፣ እንዲሁም ላጠፋሁት ጥፋት በይፋ ስህተቴን አምኜ ይቅርታ ብጠይቅም ምንም አይነት ምላሽ ያላገኘው በመሆኔ አሁን ያለሁበት ሁኔታ ከባድ መሆኑን ከግምት በማስገባት ቅጣቱን እንዲያነሳልኝ እጠይቃለው በማለት ደብዳቤ ማስገባቱን ሰምተናል።

በረከት አዲሱ ለሶከር ኢትዮዽያ በጉዳዩ ዙርያ በሰጠው አስተያየት ” ማጥፋቴን አምኛለው ፣ ተፀፅቻለው ፣ ይቅርታም ጠይቄአለው፡፡ ለምን እንዲህ እንደጨከኑብኝ አላውቅም፡፡ የይርጋለም ህዝብ እንዴት ሜዳ ውስጥ ሲዳማ ቡናን አገለግል እንደነበር ያውቃል፡፡ ለሀገሬም ብዙ ለፍቻለው፡፡ ሆኖም ግን ውሳኔውን ሊቀይሩልኝ ስላልቻሉ ኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን እንዲመለከተው ደብዳቤ አስገብቻለው፡፡ ምላሽም እየጠበኩ ነው” ብሏል።

ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ በረከት አዲሱ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ክለቡ በዚህ ጉዳይ የሚሰጠው ምላሽ ካለ የምናስተናግድ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *