​የ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ድልድል ይፋ ሆኗል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ በጁፒተር ሆቴል የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ የክለብ ተወካዮች እና የሚድያ አካላት በተገኙበት የ2009 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አፈጻጸም ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ የ2010 ውድድር ዓመት የእጣ ማውጣት ስነስርአትም ተከናውኗል።

ከስነስርዓቱ በፊት ከፕሪምየር ሊጉ የወረዱት 3 ክለቦች እና ከብሔራዊ ሊጉ ያደጉት 6 ክለቦች በሁለቱ ምድቦች የተደለደሉ ሲሆን ደሴ ከተማ፣ የካ ክፍለከተማ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ ሀ፤ ሚዛን አማን፣ ቡታጅራ ከተማ፣ ሀምበርቾ፣ ጅማ አባቡና እና መቂ ከተማ ደግሞ በምድብ ለ እንዲወዳደሩ ተወስኗል። ባለፈው ዓመት በምድብ ለ የተጫወተው ፌደራል ፖሊስ ዘንድሮ በምድብ ሀ ውድድሩን የሚያደርግ ይሆናል። በ2009 ዓ.ም. ከፕሪምየር ሊጉ መውረዱን ተከትሎ የወንድ እና የወጣት ቡድኖቹን ማፍረሱን ያስታወቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውሳኔውን ለማስቀየር እየተደረገ ያለው ጥረት ፍሬ እንደሚያፈራ ተስፋ በማድረግ በዕጣው እንዲካተት ተደርጓል።

በወጣው ዕጣ መሰረት የመጀመርያው ሳምንት መርሀግብር ይህንን ይመስላል፡-

ምድብ ሀ

ቡራዩ ከተማ ከ ፌደራል ፖሊስ

ደሴ ከተማ ከ ለገጣፎ ከተማ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ወሎ ኮምቦልቻ

ባህርዳር ከተማ ከ አክሱም ከተማ

ሱሉልታ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

የካ ክፍለከተማ ከ ሰበታ ከተማ

አማራ ውሀ ስራ ከ ኢትዮጵያ ውሀ ስፖርት

ሽረ እንዳስላሴ ከ ኢትዮጵያ መድን


ምድብ ለ

መቂ ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ

ዲላ ከተማ ከ ሀምበርቾ

ቡታጅራ ከተማ ከ ነገሌ ቦረና

ሻሸመኔ ከተማ ከ ካፋ ቡና

ሀድያ ሆሳዕና ከ ስልጤ ወራቤ

ሚዛን አማን ከ ጅማ አባ ቡና

ወልቂጤ ከተማ ከ ናሽናል ሲሚንቶ

ድሬደዋ ፖሊስ ከ ሀላባ ከተማ

በስነስርአቱ ላይ የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ የውድድር ስነስርዓት እና ስፖርት ማዘውተሪያ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ከፍተኛ ሊጉ የሚጀመርበት ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን ገልፀዋል። ከዚህ ቀደም የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ሊጉ ጥቅምት 11 እንደሚጀመር ማስታወቁ የሚታወስ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጥቅምት 25 ለመግፋት ተገዷል። የሊጉ ይፋዊ የመክፈቻ ቀን ጥቅምት 25 ቢሆንም ሁለት የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ባሉባቸው ከተሞች የሚደረጉ እና ከፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መርሀግብር ጋር የሚጋጩ ጨዋታዎች አንድ ቀን ቀደም ብለው ቅዳሜ ጥቅምት 24 እንደሚደረጉ ተገልጿል።

ፌዴሬሽኑ ያቀረበውን የ2009 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አፈጻጸም ሪፖርት እና በውድድሩ ዙሪያ የተደረገውን ውይይት ዋና ሃሳቦች ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *