​ሪፖርት| ቅዱስ ጊዮርጊስ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ባለድል ሆነ

በ2009 የውድድር አመት የፕሪምየር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ አሸናፊ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ በተገናኙበት የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ድል ማድረግ ችሏል።

በመጀመሪያዎቹ ሠላሳ ደቂቃዎች ሙሉ ለሙሉ በወላይታ ድቻ የሜዳ ክፍል ላይ አመዝኖ የተካሄደው ጨዋታ ምንም አይነት ሙከራ ያልታየበት ነበር  ። በአምስት ተከላካዮች የተዋቀረውን የድቻዎችን የተከላካይ ክፍል አልፈው ለመግባት የተቸገሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደቀኝ ባደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ክፍተቶችን ለማግኘት ሞክረዋል። ሆኖም የጊዮርጊስ አማካይ ክፍል ከድቻ አምስት ተከላካዮች ፊት ያለውን ቦታ ለመጠቀም ብዙ ጥረት አለማድረጉ ከፊት ሙሉ ለሙሉ በድቻ የተከላካይ መስመር ቁጥጥር ስር የነበሩትን ሶስቱን አጥቂዎች በቅብብል ለማግኘት እንዲቸገር አድርጎታል።

የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድን ከጥብቅ መከላከሉ ባሻገር ሁነኛ የመልሶ ማጥቃት ዕድልን ለማግኘት ሳይችል ለረጅም ደቂቃዎች በራሱ ሜዳ ላይ ቆይቶ የነበረ ቢሆንም ከ 25ኛው ደቂቃ በኃላ የተሻለ ወደተጋጣሚው ሜዳ ለመግባት የደፈረ ይመስል ነበር ።  ድቻዎች መጠነኛ መነቃቃት በማሳየት ላይ እንዳሉም 32ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር የተገኘውን እና አብዱልከሪም መሀመድ ያሻማውን ኳስ አሉላ ግርማ በግንባሩ በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል ። ከሁለት ደቂቃዎች ቆይታ በኃላም በአዲሱ የየድቻ ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮ እና ቡድኑ አምበል ተክሉ ታፈሰ መሀከል የተፈጠረውን የቅብብል ስህተት በመጠቀም አቡበከር ሳኒ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ቻለ ። በተከታታይ የተቆጠሩት ሁለቱ ግቦችም የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራዎች ነበሩ።


በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን የጨረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ 49ኛው ደቂቃ ላይ በአሜ መሀመድ አማካይነት ካደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሌላ ጥርት ያለ የግብ ዕድል ሲፈጥር አልተስተዋለም ። ከዚህ ውጪ 77ኛው ደቂቃ ኢብራሂማ ፍፋኖን በመተካት ወደሜዳ የገባው አዲሱ ፈራሚ ጋዲሳ መብራቴ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለክለቡ በማድረግ ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል ።

ድቻዎች ግብ ማስተናገዳቸውን ተከትሎ በሁለተኛው አጋማሽ  ላይ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ይታይባቸዋል ተብሎ ቢጠበቀም ከጥንቃቄ አጨዋወታቸው መላቀቅ አልቻሉም ። በርግጥ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የመስመር ተመላላሾቻቸው ከመሀል ተከላካዮቻቸው ተነጥለው ይታዩ የነበረ ቢሆንም የማጥቃት ተሳትፏቸው ግን አመርቂ አልነበረም ። ከጨዋታ እንቅስቃሴ ይልቅ በርካታ የቆመ ኳስ ዕድሎችን ያገኙት ድቻዎች 46ኛው ደቂቃ ላይ እሸቱ መና በቀጥታ ሞክሮት በጎን በኩል ከወጣው ኳስ በቀር ሌላ አስደንጋጭ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ። ከዚህ ውጪ 64ኛው ደቂቃ ላይ ደጉ ደበበ አሳጥሮ ወደ ሮበርት የላከውን ኳስ ያገኘው ጃኮ አራፋት ግልፅ አቋቋም ላይ ለነበረው ሌላው አጥቂ ፀጋዬ ብርሀኑ ሰጠ ተብሎ ሲጠበቅ በቀጥታ ሞክሮ ወደላይ የተነሳበት ኳስ የድቻ ምርጡ አጋጣሚ ነበር ። በዚህ መልኩም ይበልጥ የተቀዛቀዘው ሁለተኛ የጨዋታ አጋማሽ ሌላ ግብ እና ከመቀመጫ የሚያነሳ ሙከራ ሳይታይበት ተጠናቋል ። ቅዱስ ጊዮርጊስም ለ16ኛ ጊዜ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ማንሳት ችሏል ።



Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *