​ሪፖርት | የሸገር ደርቢ ከአሰልቺ ጨዋታ ጋር ያለ ጎል ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ አካሄድ ከተጀመረ በኃላ ለ37ኛ ጊዜ የተገናኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ 11:00 ላይ ጨዋታቸውን አድርገው ከቀዝቃዛ እንቅስቃሴ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጀመር በፊት የአዲስ አበባ ስታድየም እጅግ ያማረ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ድባብ ፣ በክለቦቹ ትላልቅ አርማዎች እና ዝማሬዎች ከወትሮው በተለየ መልኩ ደምቆ ታይቷል። የዳኛው ፊሽካ ከመሰማቱ በፊትም በስታድየሙ የተገኘው ተመልካች የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን በአንድነት በመዘመር ለነበረው ድባብ ሌላ ውበት ጨምሮለታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ኤሌክትሪክን ከረታበት ስብስብ የቀኝ መስመር የአጥቂ ክፍል ላይ ጋዲሳ መብራቴን በበኃይሉ አሰፋ ብቻ በመቀየር በተመሳሳይ መልኩ በ4-3-3 አቀራረብ ጨዋታውን ጀምሯል። ለውጦች ተበራክተው የታዩበት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ዓዲግራት ላይ ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ አለማየው ሙለታን በበረከት ይስሀቅ የቀየረ ሲሆን በአሰላለፍ እና በተጨዋቾች ቦታ ላይ በርካታ ለውጦችን በማድረግ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደሜዳ ገብቷል። በዚህም አስራት ቱንጆን ከአጥቂ ጀርባ የተሰለፈ ሲሆን ቡድኑ ኤልያስ ማሞን ወደኃላ ገፍቶ በጥልቅ አማካይነት ሚና ተጠቅሟል። ከዚህ ውጪ ከጉዳት የተመለሰው አስቻለው ግርማም ከአማኑኤል ዮሀንስ ቀድሞ ጨዋታውን ጀምሯል።

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለት ተመሳሳይ ቡድኖችን ያሳየን ነበር። ሁለቱም  መሀል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥርን ለማግኘት ሲራኮቱ ቢታይም እጅግ በተጠጋጋው የተጨዋቾች አቋቋማቸው መሀል ሜዳው ተጨናንቆ አንዳቸውም በጥሩ የኳስ ፍሰት እና ቅብብል ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም የመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች እጅግ የተቀዛቀዙ ነበሩ። ጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያስተናገደውም 21ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ በቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ በኩል ይዞ የገባውን ኳስ ሞክሮ ሮበርት ሲያድንበት ነበር። ከዚህ ውጪ በመጠኑ ወደ ተቃራኒ ሜዳ በመግባት የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ በአስራት ቱንጆ በቀኝ መስመር በኩል የፈጠሩት ዕድል ፣ የ6ኛ ደቂቃ የሳሙኤል ሳኑሚ እና የ43ኛው ደቂቃ የኤልያስ ማሞ የርቀት ሙከራዎች ጨምሮ የሚጠቀሱ ነበሩ። ቅዱስ ጊዮርጊሶች 24ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ አሰፋ ከርቀት አክርሮ መቷት በግቡ አግዳሚ ለጥቂት ከወጣችው ሙከራ ውጪ በጥሩ የማጥቃት ፍሰት በቡናዎች ሳጥን ውስጥ የተገኙት የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ነበር። በዚህም አብዱልከሪም ኒኪማ መሀል ሜዳ ላይ አስናቀ ሞገስንን ኳስ አስጥሎ ለበሀይሉ ካሳለፈለት በኃላ በሀይሉ ከአሜ ጋር ተቀባብሎ ወደ ውስጥ ለመግባት የሞከረው ኳስ በቡና ተከላካዮች ተጨርፎ ወጥቶበታል። በአጠቃላይ ቡድኖቹ ለመጫወት በሞከሩበት አኳኋዋን ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር አለመቻላቸው በግልፅ የታየ ነበር። እንቅስቃሲያቸውም ነፍስ ዘርቶበት አስፈሪ ሲሆን ይታይ የነበረው ቅብብላቸው ከተጨናነቀው የመሀል ክፍል ወጥቶ ወደ መስመሮች በሚሄድበት ወቅት ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ የጀመረበት የጨዋታ ፍጥነት ምናልባትም ከመጀመሪያው የተሻለ ፉክክርን ሊያሳየን ነው የሚል ተስፋን በብዙዎች ዘንድ ያሳደረ ነበር። 46ኛው ደቂቃ ላይ ኢብራሂማ ፎፋና ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ምንተስኖት በግንባሩ ከሞከረ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በሌላኛው የሜዳው ክፍል አስቻለው ግርማ በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ሞክሮ ሮበርት አደኖበታል። ይህ ከሆነ ከአንድ ደቂቃ በኃላ ደግሞ በቀኝ መስመር በረጅሙ የተሻገረለት ኳስ በሀይሉ አሰፋ ከቅርብ ርቀት ኳሱ መሬት ሳይወርድ ለማግባት ሞክሮ ስቷል። ከነዚህ ሙከራዎች በኃላ ግን ጨዋታው ቀስ በቀስ ወደ ነበረበት የተቀዛቀዘ መንፈስ ተመልሷል። 

አልፎ አልፎ በሚታዩ እንቅስቃሴዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ የቀኝ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመሮች የተሻለ ጫና መፍጠሪያነት ሲያገለግሉ ቢታዩም አሁንም ንፁህ የግብ ዕድል ግን ማግኘት አልተቻላቸውም። 67ኛው ደቂቃ ላይ የረዘመን ኳስ ሀሪሰን ከግብ ክልሉ ወጥቶ በሚገባ ሳያርቀው አብዱልከሪም ኒኪማ አግኝቶ ወደግብ ሲሞክር አክሊሉ አያናው ያወጣበት እንዲሁም 66ኛው ደቂቃ ላይ ቶማስ ስምረቱ ከኤልያስ ማሞ የተነሳን ቅጣት ምት በግንባሩ ሞክሮ ወደውጪ የወጣበት አጋጣሚዎች ብቻ ትኩረት የሳቡ ነበሩ። ከነዚህ ውጪ ሮበርትም ሆኑ ሀሪሰን እምብዛም ሳይጨነቁ ጨዋታው ተገባዷል። በጨዋታው መገባደጃ ላይ ኢ/ዳኛ በአምላክ ተሰማ 4 ደቂቃዎችን ከጨመሩ በኃላ በስቴድየሙ ሰዐት መሰረት ሰከንዶች ሲቀሩት የጨዋታውን ማብቂያ ፊሽካ በማሰማታቸው መሀል ሜዳ ላይ የቅጣት ምት አግኝተው የነበትሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመምታት ዕድል ባለማግኘታቸው ደጋፊዎች ተቃውሞ አሰምተዋል። በመጨረሻም ቡድኖቹም በአመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነጥብ ተጋርተው የወጡበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

የሸገር ደርቢ በቅርብ አመታት የተጠባቂነቱን ያህል ተመልካቹን የሚመጥን እንቅስቃሴ እየታየበት አይገኝም። በተከታታይ ከተደረጉ 5 ጨዋታዎችም ሶስቱ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ

” ጨዋታው ሁለት አይነት መልክ አለው።  በመጀመሪያው አጋማሽ እኛ በጣም ቀርፋፋ ነበርን። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። ነገር ግን በሙሉ ጨዋታው የሚገባንን ያህል ተጫውተናል ብዬ አላስብም። ”

አሰልጣኝ ሀብተወልድ ደስታ

“ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሙሉ ለሙሉ ጥረት አድርገናል ማለት ይቻላል። የተሻለ ጨዋታም ተጫውተናል። ውጤቱም ይገባን ነበር። ሆኖም የጨዋታው አጋጣሚ ያሳየንን ነገር ተቀብለናል።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *