​ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾቹን አስጠንቅቋል

ድሬዳዋ ከተማ ስፖርት ክለብ ዘጠኝ ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሲሰጥ ከእነዚህ መካከልም በአንዳንዶቹ ላይ የገንዘብ ቅጣት ማስተላለፉ ታውቋል።

ድሬዳዋ ከተማ በ2008 ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ካደገበት አመት ጀምሮ ላለመውረድ የሚያደርገውን ትግል አስቀርቶ በዘንድሮ አመት ከፍተኛ ተፎካካሪ እንዲሆን በማሰብ ከፍተኛ የዝውውር  እንቅስቃሴ በማድረግ በሊጉ ደረጃ ጥራት ያላቸው በርካታ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም እስከ 13ኛው ሳምንት ድረስ ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት በወራጅ ቀጠናው ከመገኘት አላተረፈውም።

የክለቡ የበላይ አመራሮች አስቀድመው ቡድኑን ወደ ጥሩ አቋም እንዲመለስ በማሰብ ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር በስምምነት መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን በተጨማሪ የክለቡን ስራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ እስከዳር ጋር በስምምነት መለያየታቸውም ይታወቃል። አሁን ደግሞ ከወደ ድሬደዋ እየተሰማ ያለው ዜና ክለቡ እያስመዘገበ ላለው ደካማ እንቅስቃሴ ምክንያት ናቸው በማለት በዘጠኝ ተጨዋቾቹ ላይ የማስጠንቀቅያ ደብዳቤ ሰጥቷቸዋል። እንደ ምክንያት ሆኖ የቀረበው ደግሞ ክለቡን የሚመጥን እንቅስቃሴ አለማድረግ ( የአቋም መውረድ )  እና በህክምና ሰበብ ጉዳት አጋጥሟቸው በበቂ ሁኔታ በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ በሚገባ ከመፈፀም ይልቅ ሆን ብለው ችላ በማለት ክለቡን በሚፈለገው መልኩ ያላገለገሉ መሆናቸው እንደሆነ ታውቋል ። ክለቡ በማስጠንቀቂያ ብቻ አላበቃም ከላይ በቀረበው ምክንያት የተነሳ በአንዳንድ ተጫዋቾች ላይም የገንዘብ ቅጣትም እንዳስተላለፈ ሰምተናል። ክለቡ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውንም ሆነ የተቀጡትን ተጫዋቾች ስም ከመገረለፅ ገረን ተቆጥቧል።

ድሬዳዋ ከተማ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች በአንድ ጨዋታ ብቻ ድል ቀንቶት በስድስት ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቆ በአራት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዶ 9 ነጥብ በሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ክለቦቻችን ተጨዋቾቻቸው በሚያሳዩት የአቋም መውረድ እና በሌሎች ምክንያቶች ለተጫዋቾቻቸው አቋማችሁን አስተካክሉ በሚል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሲሰጡ በስፋት እየተመለከተን እንገኛለን። መቐለ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻም የሚጠቀሱ ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *