በረከት አዲሱ ወደ እግር ኳስ ተመለሰ

በሲዳማ ቡና የሁለት አመታት እገዳ ከተጣለበት ከወራት በኃላ በፌዴሬሽኑ አማካይነት የተነሳለት አጥቂ በረከት አዲሱ በአንድ አመት የውል ስምምነት አርባምንጭ ከተማን ተቀላቅሏል።

በውድድር ዘመኑ አስከፊ ጊዜን በማሳለፍ የመጀመሪያውን ዙር  በሊጉ ግርጌ ያጠናቀቀው የአሰልጣኝ እዮብ ማለው አርባምንጭ ከተማ የሚታይበትን ከፍተኛ የአጥቂ ክፍተት ለመሙላት በማሰብ በረከት አዲሱን በአንድ አመት የውል ስምምነት አስፈርሞታል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሲዳማ ቡና ቆይታ እያደረገ የነበረው በረከት አዲሱ በክለቡ ባሳየው ከፍተኛ የዲሲፕሊን ችግር ምክንያት የሁለት አመታት እገዳ ተጥሎበት እንደቆየ ይታወሳል። ተጨዋቹ ከጥፋቴ በሚገባ ታርሜያለሁ በሚል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ባስገባው ደብዳቤም መሰረት ፌድሬሽኑ ይቅርታውን ተቀብሎ ሲዳማ ቡና ይቅርታ አድርጎለት በክለቡ እንዲቀጥል አልያም እንዲለቀቅ በሚል በደብዳቤ አሳውቋል። ይህን ተከትሎም የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዳማ ከተማ እና ንግድ ባንክ አጥቂ  ከሲዳማ ቡና መልቀቂያውን በመውሰድ በአርባምንጭ ከተማ የሙከራ ጊዜ ካሳለፈ በኃላ በአዞወቹ ለመቆየት ከስምምነት በመድረስ ፊርማውን አኑሯል፡፡

በተያያዘ ዜና አርባምንጭ ከተማ የቀድሞው የሀላባ ከተማ አጥቂ ከነበረው እና ባሳለፍነው ክረምት ወደ ድሬዳዋ ከተማ ቢያመራም ደካማ የውድድር ጊዜ በማሳለፍ ከክለቡ ከተለያየው የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ዘካሪያስ ፍቅሬ ጋር ድርድር እንደጀመረ ተሰምቷል። አዞዎቹ የፊት መስመራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር የአምናውን የከፍተኛ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ለማስፈረም ጥረት ላይ አንደሆኑ አሰልጣኝ እዮብ ማለ በተለይም ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል ፡፡ አርባምንጭ ከተማ የተስፋ ቡድኑ ምንም እንኳን ውድድር ላይ ባይሆንም አሰልጣኙ ጠንካራ ናቸው ያሏቸውን አራት ወጣት ተጨዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ማሳደጋቸውንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *