ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና መከላከያ አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን መርሃ ግብር ሶዶ ላይ መከላከያን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በሜዳው ለአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች የነበረውን የበላይነት ከጦሩ ጋር ነጥብ በመጋራት ደምድሞታል፡፡ 

ጨዋታው በአፍሪካ መድረክ እና በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተከታታይ ድሎችን እያስመዘገበ የሚገኘው እና በሜዳው በሊጉ ለሚገኙ ቡድኖች ፈታኝ በመሆን በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ላይ ከፍ በማለት ላይ ይገኝ የነበረው ወላይታ ድቻን እና ከአስልጣኝ ሥዩም ከበደ መምጣት በኃላ ወደ ድል እየተመለሰ እና ከውራጅ ቀጠና ራሱን ለማራቅ እየጣረ የሚገኘው መከላከያን በማገናኘቱ ተጠባቂ እንዲሆን አስችሎታል።

እንደወትሮው ሁሉ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በሶዶ ስታድየም አከባቢ ከተለያዩ ወረዳዎች እና አጎራባች ከተሞች ቡድኑን ለመደገፍ በነቂስ የሚተመው የወላይታ ድቻ ደጋፊ ዛሬም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ ወደ ሜዳ ለመግባት ጥረት ሲያደርግ ታይቷል። ጨዋታው እነደከዚህ ቀደሙ የዕረፍት ቀናት ላይ አለመደርጉ የደጋፊውን ቁጥር በመጠኑም ቢሆን የቀነሰው ቢመስልም የማታ ማታ ግን ስታዲየሙ ከአፍ እስከ ገደፍ መሙላቱ አልቀረም። ቡድኖቹ ወደ ሜዳ ሲገቡም የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ማህበር ያዘጋጀው የእንኳን ደህና መጣችሁ ባነር ለእንግዳው ቡድን ቀርቦ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ተዘምሮ ጨዋታው ተጀምሯል።

ወላይታ ድቻ ባሳለፍነው እሁድ የሊጉን መሪ ደደቢትን 1-0 ካሸነፈበት 4-1-4-1 አሰላለፍ ውስጥ በጉዳት ባጣው ጸጋዬ ባልቻ ምትክ ያሬደ ዳዊትን ወደ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ሲያስገባ  መከላከያ ደግሞ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያሸነፈበትን የ4-4-2 አሰላለፍ ሳይቀይር ከስብስቡ ውስጥ የተሸ ግዛውን በቴድሮስ ታፈሰ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

በጨዋታው በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ያልተረጋጋ የኳስ እንቅስቃሴ ያሳዩ ሲሆን ወላይታ ድቻ ረጃጅም ኳሶችን ወደ መከላከያ የግብ ክልል ለመጣል ሲሞክር በአንጻሩ መከላከያዎች ኳስን መስርተው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ባለሜዳዎቹ ድቻዎች የሰሞኑ ጠንካራ አቋማቸው ተዳክሞ በታየበት በዚህ ክፍለ ጊዜ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት በሚሞክሩበት አጋጣሚ ቶሎ ቶሎ ሲቆራረጥባቸው እና በመከላከያ የመሃል ሜዳ የበላይነት ሲወሰድባቸው ታይቷል። ዳዊት እስቲፋኖስ ፣ አማኑኤል ተሸመ ፣ ሳሙኤል ታዬ እና በጨዋታው ድንቅ የነበረው ቴድሮስ ታፈሰ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ድቻዎች ከዚህ ቀደም በመስመር የሚሰነዝሩት ጥቃት ሲገታባቸው እና ብቸኛው የፊት አጥቂ ጃኮ አራፋትን ግልጋሎት በሚገባ ማግኘት ሲሳናቸውም ታይተዋል።

መከላከያዎች በሁለቱ አጥቂዎቻቸው ሳሙኤል ሳሊሶ እና ምንይሉ ወንድሙ አማካኝነት ጥቃት ለመሰንዘር ቢሞክሩም በተደጋጋሚ በድቻ የተከላካይ ክፍል ጥረት በተለይም በውበሸት አለማየሁ ኳስ የማጨናገፍ ክህሎት ድቻዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። የጦሩ ተሰላፊዎች የመሀል ሜዳ ብልጫቸውን በመጠቀም አንድም የጠራ የጎል እድል ማግኘት ባይችሉም በ40ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሜዳው ጫፍ በኩል ሳሙኤል ሳሊሶ ለምንይሉ ወንድሙ የላካት ኳስ የድቻ ተከላካዮች ለመመስ ጥረት በሚደረጉበት ወቅት ኳስ በእጅ ተነክቷል በማለት ጥያቄ ቢያቀርቡም የእለቱ ረዳት ዳኛ ጨዋታው እንዲቀጥል አድረገዋል፡፡ በዚህ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች አንድም ቀጥተኛ የሆነ ሙከራ ሳይደረግ ተጨዋቾቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች 4-4-2 ነበረውን አስላለፋቸውን በይበልጥ ለማጥቃት በሚመስል መልኩ ወደ 4-3-3 ሲቀይሩ በመጀመሪያው አጋማሽ ከአራቱ አማካዮች ተርታ የነበረውን ሳሙኤል ታዬን ወደ ቀኝ መስመር በማውጣት መሃል ላይ በቀሪዎቹ ሶስት አማካዮች ኳስን በሚገባ ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ተስተውለዋል። በአንጻሩ ድቻዎች በጨዋታ መሀከል የአምረላ ደልታታን እና ያሬድ ዳዊትን ቦታ ከመቀያየር ውጪ ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ መከላከያዎች ይህ ቅርጽ ከመጀመርያው አጋማሽ ይልቅ የጎል ዕድሎችን ሲፈጥርላቸውም ነበር። በተለይም በ47ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ታዬ ከቀኝ መስመር ያሻገራት ኳስ ዳዊት እስጢፋኖስ በግንባሩ አግኝቷት ወደ ውጪ የላካት በእለቱ የታየች የመጀመርያ የጎል አጋጣሚ ስትሆን ድቻዎች በረጃጅም ኳሶች ወደ መከላከያ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመግባት ቢሞክሩም ጃኮ አራፋትን በሚገባ በተቆጣጠሩት አወል አበደላ እና ምንተስኖት ከበደ የሚመራው የመከላከያ ተከላካይ ክፍል ምንም አስደጋጭ ሙከራ ማድርግ እንዳይችሉ አስገድዷቸዋል።

የመከላከያ ተጭኖ የመጫወት ሂደቱ ቀጥሎ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ምናልባትም 3 ነጥብ ማግኘት ሚያስችላቸውን ሙከራ በቀኝ መስመር ድንቅ ከነበረው ቴዎድሮስ ተፈሰ እና ዳዊት አስቲፋኖስ ጋር በመሆን ስብሮ የገባው ሳሙኤል ታዬ ጎል ውስጥ ለሚገኘው ምንይሉ ወንድሙ በአግባቡ አድርሶት መንይሉ በግንባሩ ሞክሮት አገባ ሲባል ወንደወሰን ገረመው በድንቅ ሁኔታ አውጥቶበታል። ድቻዎች በዚህ ክፈለ ጊዜ ወስጥ አምረላ ደልታታን በ ዮናታን ከበደ ፣ እሸቱ መናን በዘላለም እያሱ ቀይረው ቢያስገቡም በ71ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተመታውን ኳስ አብዱለስምድ አሊ በግንባሩ ሞክሮ ውደ ውጪ ከወጣችበት ኳስ ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም፡፡

መከላከያዎች ያሳኩትን የበላይነት ወደ ጎል ለመቀየር በማሰብ ማራኪ ወርቁን በሳሙኤል ታዬ ቀይረው በማስገባት አና በቴውድሮስ ተፈስ አማካይነት ተጭነው በመጫወት 87ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የመጣውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ማራኪ ወርቁ በግነባሩ ሞክሮ የድቻ ተከላካይ ክፍል እንደምንም ከግብ ክልል ስር አርቀውበታል። ጨዋታው በዚህ መልኩ ምንም ግብ ሳያስተናግድ ለወላይታ ድቻ ከተከታታይ ድል በኃላ ነጥብ የጣለበት ወደ መነቃቃት እየገባ የሚገኘው የስዩም ከበደው መከላከያ ደግሞ ወሳኟን ነጥብ ይዞ የተመለስበት ሆኖ ተገባዷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

ዘነበ ፍስሀ – ወላይታ ድቻ

“ጨዋታችን ዛሬ በፍፁም ልክ አልነበረም። ተጫዋቾቼ የተነጋገርንውን ሁሉ ዛሬ አልተገበሩም። በአጠቃላይ ጥሩ አደለንም፤ በቀጣይ እንድንዘጋጅ ብዙ ነገር ያመላከተን ጨዋታ ነበር። በተለይም መሐል ሜዳ ላይ ፍጹም የበላይነት ተውስዶብናል። ”

ስዩም ከበደ – መከላከያ

“ጨዋታው ጥሩ ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ሜዳው እንድትጫወት የሚፈቅድ አይደልም ፤ እንድትጫወት ቀርቶ ኳስ ለመቆጣጠር ያስቸግራል፤ እንደኔ የሚታየኝ ወላይታ ድቻ ለወደፊቱም ራሱ የሜዳ አድቫንቴጁን ያጣል ብዬ አስባለው፤ በተረፈ እኛ የምንፈልገውን አግኝተናል። ከሜዳችን ውጪ ጥሩ ውጤት አግኝተናል ፤ ከነሱ በተሻለ መልኩ የጎል እድል አግኝተን ነበር። ብንጠቀመው ኖሮ ለሚቀጥለው ጨዋታ በራስ መተማመን የሚሰጠን ድል እናስመዘግብ ነበር። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *