ሪፖርት | ደደቢት አሁንም ነጥብ መጣሉን ቀጥሎበታል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ መካሄድ ሲጀምር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የተደረገው የደደቢት እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ባሳለፍነው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ከሜዳቸው ውጪ በተሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙባቸው የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ውስጥ በተከላካይ ስፍራ ላይ ሠለሞን ሀብቴን አስወጥተው ስዩም ተስፋዬን ሲያስገቡ በጉዳት በዛሬው ጨዋታ ላይ ባልነበረው አቤል ያለው ምትክ ለአቤል እንዳለ ዕድል በመስጠት በ4-3-3 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል። በአንጻሩ ከረጅም ሳምንታት በኃላ ባሳለፍነው ሳምንት ወልዲያ ከተማን 2 – 0 በመርታት ወደ ድል አድራጊነት በተመለሱት ድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ያሬድ ዘውድነህ እና አህመድ ረሺድ በመስመር ተከላካይነት ጨዋታውን ሲጀምሩ አማካይ ክፍል ላይም ኢማኑኤል ላሪያ በሚካኤል አኮፉ ምትክ ወደ ሜዳ ገብቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በአመዛኙ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ከአራቱ ተከላካዮች ፊት የተሰለፉት ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች ኢማኑኤል ላሪያ እና ሳውሬል ኦልሪሽ በጣም በጠበበ ቅርፅ መጫወታቸው ከመስመር አጥቂዎቹ ደካማ የመከላከል ተሳትፎ  ጋር ተዳምሮ ደደቢቶች ከመስመሮች በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ብልጫ እንዲወስዱ አድርጓል። ለዚህም ማሳያ በሚሆን መልኩ 12ተኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ከግራ መስመር አሻምቶት ጌታነህ ከበደ እና ሽመክት ጉግሳ ለጥቂት ያመለጣቸው እንዲሁም በ25ተኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ያሻማውና በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ኤፍሬም አሻሞ በግንባሩ እና በእግሩ አከታትሎ ሞክሮ የድሬው ግብጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ያዳነበት የሚጠቀሱ ነበሩ። የደደቢቶች የበላይነት በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ 20ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ከግብ ክልል ውጪ በቀጥታ ወደፊት የላከውን ኳስ ያሬድ ዘውድነህ ተደርቦ ሲመለስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው የአብስራ ተስፋዬ ሞክሮ ሳምሶን ያዳነበት አጋጣሚ ሌላኛው ጠንካራ ሙከራ ነበር። ምንም አይነት ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም በተጫዋቾቻቸው ደካማ የሆነ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር የተነሳ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ በጣም ደካማ የሆነ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ50ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ተስፋዬ ከመስመር ያሻገረው እና የድሬው ተከላካይ ያሬድ ዘውድነህ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ኳሷ ተቆርጣበት ወደ ግብ ልታመራ ስትል ራሱ ያሬድ እንደምንም ካዳነበት አጋጣሚ በቀር ምንም አይነት የግብ ሙከራን ማየት አልቻልንም፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በቻሉት አቅም ሁሉ የአሸናፊነቱን ግብ ለማግኘት ሲጥሩ የነበሩት ደደቢቶችም ይህ ነው የሚባል የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በእንቅስቃሴ የቡድኑ የመከላከል ሚዛን እጅግ ተፋልሶ የነበረውን ደደቢትን ከማጥቃት ይልቅ በአንድ ነጥቡ ለመርጋት በማሰብ በፍፁም መከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ ሶስት የመከላከል ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ጭምር ቀይሮ በማስገባት ጨዋታውን መጨረስ ችለዋል፡፡

ጨዋታው 0ለ0 በሆነ ውጤት መጠናቁን ተከትሎ መሪው ደደቢት አሁንም ነጥቦችን በመጣል መሪነቱን አሳልፎ ለመስጠት ቢቃረብም ሊጉን በ33 ነጥብ በመምራት ከቀጠለ ሲሆን ድሬደዋ ከተማ ደግሞ ወደ ወራጅ ቀጠናው ተመልሶ በ18 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት

” በአጠቃላይ በ90ደቂቃው አጥቅተን መጫወት ብንችልም ግቦችን ማስቆጠር ባለመቻላችን አቻ ልንለያይ ችለናል፡፡ማሸነፍ የነበረብን ቢሆንም የተገኙ የግብ እድሎችን መጠቀም አለመቻላችን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡”

አሰልጣኝ ስምዖን አባይ – ድሬዳዋ ከተማ

“በተለይ የመጀመሪያ አጋማሽ በነበረው የቡድኔ እንቅስቃሴ ደስተኛ አይደለሁም፡፡በሁለተኛው አጋማሽ በቂ በሚባል ደረጃ ባይሆንም ጥሩ መሻሻሎችን አሳይተን ነበር፤ አሁን ካለንበት ደረጃ አንፃር ግን ከሜዳ ውጭ አንድ ነጥብ ይዘን መመለሳችን አያስከፋም፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *