የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ተጀምሯል

የ2010 የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ ዓዲግራት ላይ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጀመር ወልዋሎ ዓ.ዩ በሜዳው አርባምንጭን አስተናግዶ ጨዋታው በሙሉ ደቂቃ ያለ ግብ በመጠናቀቁ በተሰጠው የመለያ ምት አርባምንጭ 2 – 1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል፡፡ 

ወልዋሎ ዓዲግራት ዮኒቨርስቲ በሜዳው አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደበት ጨዋታ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ነገር ግን ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ ነበር። 60ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ የአርባምንጭ ፈራሚ አማካዩ ገዛኸኝ እንዳለ በሰራው ጥፋት የዕለቱ ፌድራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ በቀጥታ ቀይ ካርድ አሰናብተውታል። ጨዋታውም ያለግብ በመጠናቀቁ በተሰጠው የመለያ ምት እንግዳው አርባምንጭ ከተማ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ በመለያ ምቱ ወልዋሎ ዓዲግራቶች ከመቱት የመለያ ምት አንዱን ብቻ ሲያስቆጥሩ መኩሪያ ደሱ ፣ ኢብራሂም ፋይስኒ ፣ አብርሀ ትአረ እና ኤፍሬም ጌታቸው የመቷቸው አራት ፍፁም ቅጣት ምቶች መክነዋል። በአርባምንጮች በኩል ደግሞ ሁለት ኳሶች ከመረብ ሲዋሀዱ ታገል አበበ ፣ ብሩክ ዋቆ እና አስጨናቂ ፀጋዬ መለያ ምቶችን ያመከኑ ተጫዋቾች ናቸው።

አርባምንጭ በቀጣይ የኢትዮጵያ ቡና እና የወልዲያን አሸናፊ የሚያገኝ ይሆናል። ወልዋሎ አና አርባምንጭ በዛው ዓዲግራት ላይ የ21ኛውን ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በቀጣዩ ረቡዕ ያደርጋሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዋንጫ ቀጣይ መርሀ ግብሮች 

ሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2010

09፡00 ፋሲል ከተማ ከ አዳማ ከተማ (ጎንደር)

ረቡዕ ግንቦት 22 ቀን 2010

11፡00 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መቐለ ከተማ (አአ)

ረቡዕ ሰኔ 6 ቀን 2010

09፡00 መከላከያ ከ ድሬዳዋ ከተማ (አአ)

09፡00 ጅማ አባ ጅፋር ከ ደደቢት (ጅማ)

09፡00 ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና (ሀዋሳ)

11፡00 ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልዲያ (አአ)

ሀሙስ ሰኔ 7 ቀን 2010

11፡00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ (አአ)