የኢትዮጵያ ዋንጫ | ቡና ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል

በመደበኛው ክፍለ ጊዜ 2-2 የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቡና እና ወልዲያ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በመለያ ፍፁም ቅጣት ምቶች በኢትዮጵያ ቡና 5-3 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

ተመጣጣኝ በሆነ እንቅስቃሴ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 3ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ ከቀኝ በኩል አሻምቶት አቡበከር ነስሩ በግንባሩ በገጨው ኳስ የመጀመሪያውን ሙከራ አስተናግዷል። ከአምስት ደቂቃዎች ቆይታ በኃላ ደግሞ ሳሙኤል ሳኑሚ ሚኪያስ መኮንን ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ባስቆጠረው ኳስ ኢትዮጵያ ቡና ቀዳሚ ሆኗል። ከጎሉ መቆጠር በኃላ ወደ ጨዋታው በቶሎ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ወልዲያዎች ኳስን መስርተው ከራሳቸው ሜዳ መውጣት ሲከብዳቸው ታይቷል። መሀል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸው የቁጥር ብልጫ እና የተከላካይ መስመሩን ወደ መሀል ሜዳ በማስጠጋት ጭምር በራሳቸው ሜዳ ላይ ነፃነት እንዳያገኙ ያደረጋቸው የተጋጣሚያቸው ሁኔታ ቅብብሎቻቸው ውጤታማ እንዳይሆን ያደረጉ ምክንያቶች ነበሩ። ሆኖም 17ኛው ደቂቃ ላይ ከብርሀኔ አንለይ የተነሳችው ኳስ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ኤደም ኮድዞ ጋር ከደረሰች በኃላ ኤደም በቀጥታ ሲሞክራት በሀሪሰን ብትድንም አንዷለም ንጉሴ አግኝቷት ወደ ግብነት ቀይሯታል። ወልዲያም በቶሎ አቻ መሆን ችሏል።

በቀሪው የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ውስጥ ለመግባት ሲሞክሩ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ያለቀላቸው የሚባሉ ዕድሎችን ባይፈጥሩም በሙከራ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። በ21ኛው እና 32ኛው ደቂቃዎች ኤልያስ ማሞ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ካደረጋቸው ሙከራዎች አንደኛው ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር ሌላኛውን ደግሞ ቢያድግልኝ ኤልያስ ተደርቦ አውጥቶበታል። በግራ እና ቀኝ እያሱ ታምሩ እና ኃይሌ ገ/ትንሳይን ባሳተፈ መልኩ ሲያጠቁ የነበሩት ቡናዎች ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶቻቸው የተመጠኑ ባለመሆናቸው ያሰቡትን ለማሳካት ተስኗቸዋል። 23ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ወደ ውስጥ ያሳለፈው እና ሳኑሚ ሳይደርስበት የቀረው ኳስ በዚህ በኩል ተጠቃሽ ነበር። 

በሂደት ለሁለቱ አጥቂዎቻቸው ኳሶችን በቀጥታ በመጣል ደካማውን እና ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትነውን የክሪዚስቶን ንታንቢ እና ትዕግስቱ አበራ የመሀል ተከላካይ ጥምረት መፈተን የጀመሩት ወልዲያዎች በተሻጋሪ ኳሶች ሙከራዎችን ማድረጋቸው አልቀረም። በ20ኛው ደቂቃ ከአማረ በቀለ ተሻምቶ በአንዷለም በግንባር የተገጨው እና ኢላማውን ያልጠበቀው እንዲሁም 27ኛው ደቂቃ ላይ ኤደም ከመስመር ወደ ውስጥ ልኮት በሀሪሰን የተያዘበት ኳስ ለዚህ ማስረጃ ነበሩ። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሲልም እንዲሁ ከቀጥተኛ ኳሶች ጥሩ ዕድሎችን የፈጠሩት ወልዲያዎች መሪ የምታደርጋቸውን ሌላ ግብ ከአምበላቸው አግኝተው ነበር ወደ እረፍት ያመሩት። አንዷለም ከአማረ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ በድንቅ አጨራረስ በግንባሩ በመግጨት ነበር ግቧን ያስቆጠረው።

ከእረፍት መልስ ከተካላካዮች ፊት ከአክሊሉ ዋለልኝ ጋር ተጣምሮ የነበረው አማኑኤል ዮሀንስን በማስወጣት ከሳኑሚ ጀርባ ከኤልያስ ማሞ ጋር በመሆን ማጥቃቱን እንዲያግዝ በማሰብ ሳምሶን ጥላሁንን ያስገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻለ ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል። ሆኖም አጨዋወታቸው ውጤት ለመጠበቅ ብቻ አስበው ከእረፍት ያተመለሱ የማይመስሉት ወልዲያዎችን ወደ ኃላ ቢገፋቸውም ክፍተት እንዲፈጥሩም ሆነ የመከላከል ስህተት እንዲሰሩ ማድረግ አልቻለም። የክሪዚስቶም ንታንቢ ፣ ኤልያስ ማሞ እና አክሊሉ ዋለልኝ ሙከራዎችም ከሳጥን ውጪ የተደረጉ ሲሆኑ የደረጄ አለሙን የግብ ጠባቂነት ጥረት የፈለገችውም አንዷ የኤልያስ ማሞ ሙከራ ብቻ ነበረች።  

ተጋጣሚያቸው ከተከላካይ ክፍሉ ጀርባ ሰፊ ክፍተት መተዉን እንደመጀመሪያው አጋማሽ በሚገባ ያልተጠቀሙበት ወልዲያዎች ያደረጉት ብቸኛ ሙከራ 67ኛው ደቂቃ ላይ የታየ ነበር። የቀኝ መስመር አማካዩ ያሬድ ሀሰን በዛው አቅጣጫ በጥሩ ሁኔታ ይዞ የገባውን ኳስ ሞክሮ ኢላማውን መጠበቅ ሳይችል ቀርቷል። ይልቁኑም ኢትዮጵያ ቡናዎች ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ አቡበከር ነስሩ ደረጄ አለሙ የኤልያስ ማሞን የቅጣት ምት ሙከራ ካዳነ በኃላ የተመለሰችን ኳስ አግኝቶ በማስቆጠር በድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በቀሩት ደቂቃዎች ወልዲያዎች ረጃጅም ኳሶችን በመጠል ቡናዎች ደግሞ ተቀይሮ በገባው አስቻለው ግርማ አማካይነት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ጨዋታው አሸናፊውን ሳይለይ ነበር የተጠናቀቀው። በመጨረሻም አላፊውን ቡድን ለመለየት የተሰጡትን የመለያ ፍፁም ቅጣት ምቶች ኢትዮጵያ ቡና በክሪዚስቶም ንታንቢ ፣ ሳሙኤል ሳኑሚ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ አስቻለው ግርማ እና መስዑድ መሀመድ አማካይነት ሲያስቆጥር የወልዲያ ሁለተኛ መቺ የነበረው አማካዩ ሐብታሙ ሸዋለም በመሳቱ  የአንዷለም ንጉሴ ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና አማረ በቀለ ግብ የሆኑ ፍፁም ቅጣት ምቶች ወልዲያን ከሽንፈት ሳያድኑት ቀርተዋል። ኢትዮጵያ ቡናም አርባምንጭ ከተማ እና ፋሲል ከተማን በመከተል ወደ ውድድሩ ሩብ ፍፃሜው የተቀላቀለ ሶስተኛው ክለብ ሆኗል።