“እስከ ዘጠነኛ ደረጃ ይዘን ለማጠናቀቅ እናስባለን” ሳምሶን አሰፋ

የዘንድሮ አመት የውድድር ጅማሮ ላይ ከመውረድ ስጋት የራቀ ይልቁንም የዋንጫ ተፎከካሪ የሚሆን ጠንካራ ቡድን ለመገንባት ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ተጨዋቾችን ያስመጣው ድሬዳዋ ከተማ እንደታሰበው ሳይሆን የውድድር አመቱ አጋማሽ ላይ ጥቂት ጨዋታዎችን አሸንፎ አመዛኙን በሽንፈት እና በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ በውጤት ቀውስ ውስጥ በመግባት እንደወትሮ ሁሉ ዘንድሮም ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ሆኖ ነበር። ሆኖም በሁለተኛው ዙር ባሳየው ከፍተኛ መሻሻል ለጊዜውም ቢሆን ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

በዚህ የቡድኑ ውጤታማ ጉዞ ውስጥ አብዛኛዎቹ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ የሚታወቀው አምበሉ ሳምሶን አሰፋ አንዱ ነው። ሳምሶን የክለቡ ወቅታዊ አቋም መስተካከል ሚስጥር ምን እንደሆነ ሲናገር ” የክለቡ የበላይ አመራሮች እና የክልሉ ከፍተኛ ባለስጣኖች ለክለቡ የሰጡት ከፍተኛ ትኩረት አንዱ ምክንያት ነው። ያረፍንበት ቦታ ሁሉ በመምጣት የሚሰጡን እገዛ እና ድጋፍ ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሮልናል። በሌላ በኩል ሁላችንም ተቀናጅተን ቡድኑን ለማትረፍ የነበረን የመጫወት ፍላጎት ጥሩ በመሆኑ እና በእያንዳዱ ጨዋታ ላይ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ያደረግነው ትግል ውጤታማ አድርጎናል። እንደሚታወቀው  በሁለተኛው ዙር ብዙ ጎል ባናስቆጥርም የገቡብን ጎሎች ሦስት ብቻ ናቸው። ይህ የመከላከል አቅማችን ከፍተኛ መሆኑ ማሳያ ነው። ለውጤቱ ማማር ሌላው የደጋፊዎቻችን አስተዋፆኦ የጎላ መሆኑ ነው። ውጤት አለመኖሩን ተከትሎ ትንሽ ሸሽቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ደጋፊው ወደ ሜዳ ተመልሶ በሚገርም ሁኔታ በየጨዋታው ወደ ሜዳ እየመጣ እየደገፈን ነው። ይሄ ለቡድኑ መሻሻል ዋነኛ ምክንያት ነው። ” ይላል።

አምስት ሳምንታት በቀሩት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማን በሜዳው እንዲሁም ሲዳማ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ ዓ.ዩን ከሜዳው ውጪ ይገጥማል። ግብ ጠባቂው እነዚህን ጨዋታዎች አስመልክቶ ሲያብራራ ” አሁን በቡድኑ ውስጥ ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህን የቡድኑን መንፈስ ጠብቀን ከዚህ በኋላ ባሉት አምስት ቀሪ ጨዋታዎች ከሜዳችን ውጪ ጠንካራ ቡድኖች የምናገኝ ቢሆንም ጥሩ ውጤት ይዘን ለመመለስ እንሰራለን። በሜዳችን የምናገኛቸው ደግሞ ላለመውረድ የሚጫወቱት ኤሌክትሪክን እና አርባምንጭን ነው። አሁን ያለው በሜዳችን ጨዋታ አሸንፎ የመውጣት ሪከርዳችንን ተጠቅመን አሸንፈን በመውጣት እነሱ ከደረጃቸው ዝቅ ሲሉ እኛ ከፍ የምንል በመሆኑ በሊጉ የመቆየት ዕድላችን ከፍተኛ ይሆናል። በዚህም እስከ ዘጠነኛ ደረጃ ይዘን ለማጠናቀቅ እናስባለን። ” በማለት ሀሳቡን አጠቃሏል።