ሲዳማ ቡና ቀሪ የሜዳ ላይ መርሀ ግብሩን ሀዋሳ ላይ ያደርጋል

በ28 እና 29ኛው ሳምንት በተከታታይ በሜዳው የሚያደርገው ሲዳማ ቡና ጨዋታዎቹን በሀዋሳ እንደሚያከናውን አስታውቋል።

በፕሪምየር ሊጉ በ32 ነጥቦች 10 ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በቀጣይ ከሚያደርጋቸው ሶስት ጨዋታዎች መካከል በ28ኛው ሳምንት መቐለ ከተማን በ30ኛው ሳምንት ደግሞ መከላከያን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ ስታድየም ከይርጋለም ወደ ሀዋሳ ቀይሯል። ክለቡ በ27ኛው ሳምንት ድሬዳዋን አስተናግዶ 1-0 ያሸነፈበትን ጨዋታ የፍቼ ጨምበላላ በዓልን ምክንያት የማድረግ ሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ማድረጉ የሚታወሰ ሲሆን አሁን ደግሞ ከደጋፊ ማህበሩ በተነሳ ጥያቄ ምቹ በሆነ ሜዳ ላይ መጫወት አለበት በሚል ነው ጨዋታወቹ ወደ ሀዋሳ የዞሩት፡፡

ክለቡ በመደበኛነት እየተጠቀመበት የሚገኘው የይርጋለም ሁለገብ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳው እና የተመልካች መቀመጫው ምቹ አለመሆንን ተከትሎ እድሳት የሚያስፈልገው በመሆኑ በቀጣዩ የውድድር ዘመንም ጭምር የሜዳውን ጨዋታዎች ወደ ሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታድየም ለማዞር እንዳሰበም ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ቅርበት ካላቸው ሰዎች ማረጋገጥ ችላለች።