ደደቢት ኤፍሬም አሻሞን ከልምምድ አገደ

በ28ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር ከ ደደቢት በተገናኙበት ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር 3-0 ማሸነፉ ይታወቃል። በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄደው በዚህ ጨዋታ የደደቢቱ ኤፍሬም አሻሞ በ18ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱም የሚታወስ ነው። ዛሬ በተሰማው ዜና ደግሞ ድርጊቱ በጨዋታው እና በቡድኑ ላይ ጫና ለማሳደር ሆን ተብሎ የተፈፀመ መሆኑን ክለቡ ያመነ በመሆኑ ተጫዋቹን ለጊዜው ከማንኛውም ልምምድ ያገደው መሆኑ ተነግሯል።

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደ መስቀል ለሶከር ኢትዮጵያ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት። “ክለቡ ለሁሉም ጨዋታዎች ትኩረት የሚሰጥ ቢሆንም የበቀደሙ ጨዋታ በሌሎች ቡድኖች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት በተለየ መልኩ የቡድናችን ተጨዋቾች በትኩረት እና በከፍተኛ ዲሲፕሊን እንዲጫወቱ የተነገራቸው ሆኖ ሲያበቃ ኤፍሬም አሻሞ በዕለቱ ጨዋታ ላይ ምንም እዚህ ግባ በማይባል ምክንያት ሆን ብሎ ከዕለቱ ዳኛ ጋር በፈጠረው ሰጣ ገባ እና ዳኛውን ለምኖ ለመውጣት በሚባል ደረጃ ቀይ ካርድ ተመልክቷል። ይህ ድርጊቱ በዕለቱ ጨዋታ እና በቡድኑ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። ስለዚህ ድርጊቱን ሆን ብሎ የፈፀመው መሆኑን ክለቡ ስላመነ ለጊዜው ከዛሬ ጀምሮ ከልምምድ እንዲታገድ ያደረግን ሲሆን በቀጣይ ደግሞ የክለቡ አስተዳደር ተነጋግሮ የገንዘብ እና ሌሎች ተጨማሪ ቅጣቶችን የሚያስተላልፍበት ይሆናል።” ብለዋል።