የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች

በከፍተኛ ሊግ የተወሩ አዳዲስ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ጅማ አባ ቡና

አምና ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወርዶ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ እየተሳተፈ የሚገኘው ጅማ አባቡና በውድድር ዘመኑ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን እያሳለፈ ቢሆንም በምድብ ለ ከመሪው ደቡብ ፖሊስ በሶሥት ነጥቦች ርቆ በ2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ በጥሩ አቋም ላይ ቢገኝም በፋይናንስ ረገድ እየተፈተነ ይገኛል።

የክለቡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በደጋፊዎቻቸው በደረሰባው ተቃውሞ ስራ ማቆማቸውን ተከትሎ የክለቡ ህልውና አጠያያቂ ሆኗል። በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ የተጫዋቾቹን ደመወዝ በወቅቱ መክፈል ሲሳነው እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ የፋይናንስ ቀውስ እደገጠመው ከክለቡ አካባቢ የተገኙ አንዳንድ ምንጮች ገልፀዋል። ይህ በእዲህ እንዳለ የቡድኑ ተጫዋቾች በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝተው የ3ወር ደመወዝ እና ቃል የተገባላቸው ማበረታቻ ክፍያዎችም እንዳልተከፈላቸው ለክለቡ ፅህፈት ቤት በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም አመቱን በሙሉ መፍትሔ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል። የውድድር ዘመኑ እየተጠናቀቀ እንደመሆኑ ለቀጣይ ጊዜያትም ሊያስታውሳቸው የሚችል ሰው እንደሌለ ለፌዴሬሽን አቤቱታቸውን ማስገባታቸውንም ጨምረው ገልፀዋል። 

አሁን በደረሰን መረጃ ፌዴሬሽኑ በአንድ ሳምንት ውስጥ ቢያንስ የሁለት ወር ደሞዛቸው እንዲከፈል ለክለቡ ማስጠንቀቂያ  ተሰጥቷል። (በቴዎድሮስ ታደሰ)

ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያ ሆሳዕና በ2010 ለሶስተኛ ጊዜ የአሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል። በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ እዮብ ማለን የቀጠረው ሆሳዕና የአሰልጣኙ ወደ አርባ ምንጭ ማምራትን ተከትሎ አሰልጣኝ ኢዘዲን አብደላን ቢቀጥርም አብሮ መዝለቅ ሳይችል ቀርቷል። ባለፉት ሳምንታት አሰልጣኝ ፍለጋ ላይ የነበረው ክለቡ በመጨረሻም የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና፣ መድን እና ጅማ አባጅፋር አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናን ቀጥሯል። አሰልጣኝ ክፍሌ ዘንድሮ ፌዴራል ፖሊስን ሲመሩ ቆይተው ነበር።  (በአምሀ ተስፋዬ)

የተገቢነት ክስ እና የፌዴሬሽኑ ለውሳኔ መዘግየት

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 23ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ ከ ፌዴራል ፖሊስ ባደረጉት ጨዋታ የተጫዋች ተገቢነት ክስ ያስያዙት ፌደራል ፖሊሶችክሳቸው በ3ቀን ውስጥ መልስ መለረስ ማግኘት ባለመቻሉ ቅሬታቸውን ለወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር በግልባጭ ጭምር በማስገባት አሰምተዋል።

ውዝግብ የማያጣው ከፍተኛ ሊግ ለውሳኔዎች መዘግየቱ የቅሬታዎች መነሻ ሲሆን በተደጋጋሚ ይስተዋላል። ለአብነትም ከፌዴራል ፖሊስ ቅሬታ በተጨማሪ ኢኮስኮ እና አዲስ አበባ ከተማ በተጫዋች ተገቢነት በተሰጣቸው መልስ ይግባኝ ቢጠየቁም መልስ ሳይሰጣቸው መቆየታቸው ፣ የወልቂጤ እና የካፋ ቡና ጨዋታ ከ3 ሳምንታት በፊት ተቋርጦ እስካሁን ውሳኔ አለማግኘቱ ፣ ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ወሳኝ ጨዋታ የሆነው የደሴ እና የካ ጨዋታ መቼ እንደሚደረግ ሳይታወቅ ሁለት ሳምንት መቆጠሩ የሚጠቀሱ ናቸው። (በአምሀ ተስፋዬ)

መርሐ ግብር 

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የከፍተኛ ሊግ ውድድር ክፍል ሊጉን በፍጥነት ለመጨረስ በማሰብ በአንድ ቦታ ላይ ለማካሄድ ሀሳብ አቅርቦ  የክለቦችን ምላሽ ሲጠባበቅ ቆይቶ ባገኘው ምላሽ በገሚሱ ተቀባይነት ሲያገኝ በገሚሱ ደግሞ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት አሁን ባለው አካሄድ በመቀጠል ቡድኖች በየ5 ቀናት ልዩነት ውድድር እንዲያደርጉ ፕሮግራሙን ለመከለስ ማሰቡ ታውቋል። አሁን ባለው መርሐ ግብር መደበኛው ውድድር የሚጠናቀቀው ነሀሴ 30 ነው። (በአምሀ ተስፋዬ)

ፌዴራል ፖሊስ 

ከአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር የተለያየው ፌደራል ፖሊስ ምክትሉ ኢብራህም መሐመድን እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ በዋና አሰልጣኝነት ማስቀጠሉ ታውቋል። አሰልጣኝ ኢብራሂም ቡድኑን ከመውረድ ስጋት የማላቀቅ ፈተናን በቀሪው የውድድር ዓመት ይጋፈጣሉ። (በአምሀ ተስፋዬ)

ተዋወቁት

ሙሉ ስም – መሐመድ ናስር

ትውልድ ቦታ – ወልቂጤ

ዕድሜ – 20

የመጫወቻ ቦታ – አጥቂ

ቁመት – 1.72

የሚጫወትበት ክለብ – ሀላባ ከተማ

ከልጅነቴ ጀምሮ እግርኳስን እወድ ነበር። እድሜዬ ከፍ እንዳለ በሰፈራችን ወዳለው ፕሮጀክት ገብቼ በመስራት ከቆይታ በኋላ ወልቂጤ ወደሚገኝ ሌላ ፕሮጀክት ወደሚያሰሩት አሰሪዎች ጋር ተቀላቅያለው። በደቡብ ፕሮጀክት ምርጥ ሶስት ጊዜ ተመርጬም ተጫውቻለው። እኔ ገና ልጅ ነኝ በርትቼ መስራት ነው የምፈልገው ፤ ትልቅ ቦታ መጫወት እፈልጋለው። የሀገሪቱንም ማልያ ለብሼ የመጫወት ፍላጎት አለኝ። በህይወቴ ከጎኔም ባትኖር ለእናቴ ትልቅ ምስጋና አለኝ። አሁን ላይ ክለቤ ሀላባን ወደ የፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ጠንክረን እየሰራን ነው። እዚ ከመጣውም በኋላ ጠቃሚ ትምህርት አግኝቻለው። (በአምሀ ተስፋዬ)