ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ተጫዋቾች አስፈርሟል

በ2009 የክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ ሲያመጣ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ ዘንድሮ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን ወደ ቡድኑ ካመጣ በኋላ በዝውውሩ ከአምናው የተለየ የዝውውር አካሄድን በመከተል በከፍተኛ ሊግ ተጫዋቾች ላይ ትኩረት እያደረገ ይገኛል። ክለቡ እስካሁን ሦስት ተጫዋቾችን ያሳደገ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ታውቋል።

ሳሙኤል ዮሀንስ ክለቡን በአንድ ዓመት መቀላቀሉ ተረጋግጧል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጣት ቡድን ካደገ በኋላ ቡድኑ በወረደበት 2009 ላይ በግሉ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ሳሙኤል የተጠናቀቀው የውድድር ዓመትን በከፍተኛ ሊጉ ክለብ አውስኮድ አሳልፏል። በመስመር ተከላካይ እና አማካይ ስፍራ ላይ መጫወት የሚችለው ሳሙኤል ለአሰልጣኝ ዮሀንስ አማራጭ እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

ገናናው ረጋሳ ሌላው የድሬዳዋ ከተማ አዲስ ፈራሚ ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን አጥቂ ባህር ዳር ከተማን ለቆ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ያመራ ሲሆን ከአንድ ዓመት የክለቡ ቆይታ በኋላ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያው ክለብ አምርቷል።

ድሬዳዋ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ለ6 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ዜጋ ተጫዋቾች የሙከራ እድል ሰጥቷል። በዝግጅቱ ወቅት አሰልጣኙን የሚያሳምኑ ተጫዋቾችም ቡድኑን ይቀላቀላሉ።