ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛውን ድል አሳክቷል

ኢትዮጵያ ቡና በሱሌይማን ሎክዋ እና አልሃሰን ካሉሻ ግቦች ደደቢትን 2-0 በመርታት ነጥቡን ወደ ስድስት ከፍ አድርጓል።

በዝናብ ታጅቦ በጀመረው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች በመቐለ 70 እንደርታ ከተሸነፈው ስብስባቸው ክዌክ ኢንዶህን በዳዊት ወርቁ ፣ አብዱልዓዚዝ ዳውድን በመድሃኔ ብርሃኔ ፣ አክዌር ቻሞን በሙሉጌታ ብርሃነ ሲቀይሩ ወደ 23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ባቀኑት የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ ምትክ ደግሞ አብርሃም ታምራትን እና ዳግማዊ አባይን ተክተዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ድሬዳዋን ካሸነፈው ስብስባቸው ሚኪያስ መኮንንን በሱሌይማን ሎክዋ ቀይረዋል።


የመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር እና ጥቂት የጎል ሙከራዎችን ያስመለከተን ነበር። ሙሉጌታ ብርሃነ ከቅርብ ርቀት ያገኘው ኳስ መቶ ዋቴንጋ በአስደናቂ ብቃት ባዳነበት ሙከራ የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ደደቢቶች ተጭነው በመጫወት በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጽያ ቡና ግብ ክልል ቢደርሱም ይህ ነው የሚባል ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ሲሞክሩ የታዩት ቡናዎች ቀስ በቀሰ ወደ ጨዋታው በመግባት ከደደቢት የተሻለ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተለይም ሳምሶን ጥላሁን አክርሮ የመታት ቅጣት ምት ውሃ የቋጠረው የሜዳው ክፍል ላይ አርፋ ግብ ጠባቂው አዳነ ሙዳንን ብታልፍም ኤፍሬም ጌታቸው ተንሸራቶ ያዳናት እና አቡበከር በግንባሩ ገጭቶ ያመከናት ኳስ ለግብ ከቀረቡት የቡድኑ ሙከራዎች ነበሩ። ከዚህ ውጪ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት መጫወቻ ሜዳው ውሃ ቋጥሮ የተሳካ ቅብብል ማድረግ ያቃታቸው ሁለቱም ቡድኖች እንደቡድን ተደራጅተው ሳይጫወቱ ነበር ወደ ዕረፍት ያመሩት።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ አጥቅተው ለመጫወት ድፍረት የነበራቸው ደደቢቶች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም አለምአንተ ካሳ የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ያገኛትን ኳስ መቶ የግቡ ቋሚ የመለሰለት አጋጣሚ በደደቢት በኩል የምታስቆጭ ሙከራ ነበረች። በደደቢት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ እንዲሁም በቡናዎች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታው በመጀመርያው አጋማሽ ስኬታማ የሆነ የማጥቃት ሂደቶች ማሳካት ያልቻሉት ቡናዎች በአቡበከር ነስሩ በተሰለፈበት መስመር ተጠቅመው የተሻለ ተንቀሳቅሰው ብዙም ሳይቆዩ ጨዋታው የሚመሩበት አጋጣሚ አግኝተዋል። ሱሌይማን ሉክዋ ከርቀት ተመታ የግቡን አግዳሚ ለትማ የተመለሰችው ኳስ በግርግር መሃል ወደ ግብ በመላክ ነበር ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ያደረገው።

ደደቢቶች ግብ ካስተናገዱ በኋላ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያሳያሉ ተብሎ ቢጠበቅም መድሃኔ ብርሃኔ ከርቀት መቷት ከግቡ በላይ ከወጣችው ሙከራ ውጭ ይህን ነው የሚባል አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም። በአንፃራዊነት ከደደቢት የተሻለ የተጠና የማጥቃት አጨዋወት የተገበሩት ቡናዎች በ77ኛው ደቂቃ ላይ አልሃሰን ካሉሻ ከመሃል ሜዳ የተሰነጠቀችለትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂ በላይ ከፍ አድርጎ ባስቆጠራት ግብ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች በእጃቸው የገባው መሪነት ለማስጠበቅ የተከላካይ ቁጥራቸውን በመጨመር ውጤት ለማስጠበቅ የተጫወቱት ቡናዎች ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 2-0 አሸንፈው ወጥተዋል። በዚህም ከመቐለ ጋር በስድስት ነጥቦች በሊጉ አናት ተቀምጠዋል።

የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ | LINK