ሪፖርት | ስሑል ሽረ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአደንኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ሽረ ላይ በመጀመርያ ጨዋታው ስሑል ሽረ ወላይታ ድቻን አስተናግዶ ያለ ግብ ጨዋታውን ፈፅሟል።

ሽረዎች በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ አምና በከፍተኛ ሊግ የነበሩ ስድስት ተጫዋቾችን ከአምስት አዳዲስ ተጫዋቾች ጋር በመቀላቀል ወደ ሜዳ ሲገቡ ወላይታ ድቻዎችም በተመሳሳይ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን በመጀመርያ አሰላለፍ ተጠቅመዋል።

እንግዳዎቹ የጦና ንቦች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ፍፁም የሜዳ ላይ ብልጫን አሳይተዋል። የግብ እድሎችን በመፍጠሩ ረገድም ከባለሜዳው የተሻሉ ነበሩ ። በ12ኛው ደቂቃ ላይ በአምበሉ ተክሉ ታፈሰ አማካኝነት የግብ ሙከራ ሲያደርጉ ከዚህች ሙከራ በኃላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ስሑል ሽረዎች በ17ኛው ደቂቃ ከቀኝ የግብ መስመር በልደቱ ለማ አማካኝነት የግብ አጋጣሚን ቢያገኙም የድቻው ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት አውጥቶበታል። በ23ኛው ደቂቃ ላይ ኢብራሂማ ፎፋና ለሰይድ ሁሴን የሰጠውን ኳስ ሰይድ ወደ ግብ ቢመታም ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወታበታለች አሁንም ከቀኝ ማዕዘን ኣከባቢ በረጅሙ የተሻማውን ኳስ ልደቱ ለማ ደርሶ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ ውስጥ ቢልከውም የዲቻው ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት እንደምንም ግብ ከመሆን አድኖታል።

በሒደት የወሰዱትን ብልጫ ማስቀጠል ያልቻሉት ድቻዎች በ39ኛው ደቂቃ ላይ በወጣቱ የመሀል አማካይ ቸርነት ጉግሳ ሁለት ጊዜ አስደንጋጭ የግብ እድል ቢፈጥሩም ግብ ጠባቂው በሰንደይ ሮቲሚ ጥረት ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት አጥቂው ሰዒድ ሁሴን በወላይታ ድቻ የግብ ክልል ተጠልፏል በሚል ፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል በሚል ሽረዎች ክስ አስመዝግበው ጨዋታው ሊቀጥል ችሏል ።

ከእረፍት መልስ ጫና ፈጥረው ግብ ለማግኘት የተንቀሳቀሱት ስሑል ሽረዎች ሲሆኑ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ደግሞ ድቻዎች ብልጫ ያሳዩበት ነበር። 54ኛው ደቂቃ ላይ ልደቱ ለማ ከርቀት የተሻማለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ሞክሮ ከአግዳሚው በላይ ሲወጣበት በ57ኛው ደቂቃ የመጀመርያውን የተጫዋች ቅያሪ ደሳለኝ ደበሽን በሰለሞን ገ/መድህን ካደረጉ በኋላ ይበልጥ ጨዋታውን ተቆጣጥረው መጫወት ችለዋል። ድቻዎችም ተቀይሮ በገባው ፀጋዬ አበራ አማካኝነት ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይ በ76ኛው ደቂቃ ፀጋዬ አበራ ከሙባረክ ሽኩር ያገኛትን ኳስ ወደ ግብ መቶ በስሑል ሽረ ተከላካዮች ተጨርፋ እንደምንም ወደ ውጪ የወጣችው ሙከራ ወላይታ ድቻን ቀዳሚ ልታደርግ የተቃረበች አስቆጪ ሙከራ ነበረች።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩ ወላይታ ድቻዎች ተጭነው በመጫወት የስሑል ሽረ ተከላካዮች ሲያስጨንቁ ተስተውለዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ ከርቀት የመታውን ጠንካራ ኳስ ሰንደይ ሮቲሚ ሲያድንበት በስሑል ሽረ በኩል በጭማሪ ደቂቃ ላይ ኪዳኔ አሰፋ ከወላይታ ድቻ ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ታሪክ በአስደናቂ ብቃት ያዳነበት የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

ጨዋታው ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎ በታሪክ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ያደረገው ስሑል ሽረ የመጀመርያ ነጥቡን ማሳካት ችሏል።

የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ | LINK