ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

አራተኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ አዳማ ከተማን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በ1-1 አቻ ውጤት ተጠናቋል። አዳማ ከተማም ለስምንተኛ ተከታታይ ጨዋታ ድል ሳያስመዘግብ ወጥቷል።

ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ባለፈው ሳምንት ከስሑል ሽረ ያለ ግብ አቻ ከተለያዩበት ስብስብ ከነዓን ማርክነህን በአዲስ ህንፃ፣ ቡልቻ ሹራን በበረከት ደስታ ተክተው ሲገቡ እንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎች በአንፃሩ መሣይ አያኖን በፍቅሩ ወዴሳ፣ ዮሴፍ ዮሀንስን በአበባየሁ ዮሀንስ በመቀየር ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ፌዴራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ሚያዚያ 22 በአዲስ አበባ ስታድየም በመከላከያ እና በወልዋሎ ባደረጉት ጨዋታ የወልዋሎ ተጫዋቾች እና የቡድን መሪው ካደረሱበት ድብደባ በኋላ ወደ ዳኝነት ተመልሶ ጨዋታ ሲዳኝ ይህ የመጀመርያው ሲሆን ጨዋታውንም በጥሩ ሁኔታ መርቶ መጨረስም ችሏል።

በአዳማው አጥቂ ዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት በተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እጅግ ቀዝቃዛ እና ሳቢ ባልነበረው አጨዋወታቸው የተነሳ የጎል ሙከራ ለመመልከት 33 ደቂቃዎች መጠበቅ አስፈልጎ ነበር። የጎል ሙከራ በማድረግም ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ቀዳሚ ነበሩ። የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዮናታን ፍስሃ ተዘናግቶ አምስት ከሃምሳ ውስጥ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ በረከት ደስታ ከኋላው በፍጥነት መጥቶ በመጠንቅ ከግብ ጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ አገባው ተብሎ ሲጠበቅ በማይታመን ሁኔታ ያመከነው ኳስ ለአዳማ ጎል መሆን የምትችል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። ከዚህች ሙከራ በኋላ የተነቃቁት አዳማዎች ብልጫ በወሰዱበት አጋጣሚ 37ኛው ደቂቃ አዲስ ህንፃ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ዳዋ ሆቴሳ ወደ ፊት በመግፋት መሬት ለመሬት መቶ ጎል በማስቆጠር አዳማን መሪ ማድረግ ቻለ።

ከአንድ ደቂቃ በኋላ ከማዕዘን ምት ምኞት ደበበ በግንባሩ በመግጨት ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ተካ ወጣችበት አንጂ የአዳማን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ ባደረገች ነበር። ወደ ዕረፍት መዳረሻ አካባቢ መልካም እንቅስቃሴ የተመለከትን ቢሆንም ተጨማሪ ጎሎች ሳንመለከት የመጀመርያው አጋማሽ ተገባዷል።

ሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ቁጭ ብድግ የሚያደርግ ፍፁም ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ሲሆን በተለይ የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ አማካዩ አበባየሁ ዮሀንስን በዮሴፍ ዮሀንስ መቀየራቸው ተሳክቶላቸው ዮሴፍ በሚገባ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅም ሆነ ኳስ በማደራጀት ሲዳማ ቡናዎች ከእረፍት መልስ ብልጫ እንዲወሰወዱ አስችሏቸዋል።

አዳማዎች ብልጫ ቢወሰድባቸውም 56ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውጭ በቮሊ የመታው ኳስ በሚያስገርም ሁኔታ በግቡ አናት ላይ ለጥቂት የወጣበት፣ 64ኛው ደቂቃ  ሱራፌል ዳንኤል በቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ ያቀበለውን ለጎሉ አንድ ሜትር ርቀት ላይ የነበረው በረከት ደስታ በድጋሚ አገባው ሲባል ኳሱን ወደ ውጭ የሰደደበት አጋጣሚ የአዳማዎችን ጨዋታውን የመጨረስ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ጨዋታው በዚህ ሒደት ውስጥ ቀጥሎ ሐብታሙ ገዛኸኝ በአስገራሚ ዕይታ ከቀኝ መስመር በጥሩ ሁኔታ ብቻውን ቆሞ ለነበረው አዲስ ግደይ አሻግሮለት አዲስ ግደይ በግንባሩ በመግጨት ጎል አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናዎችን አቻ ማድረግ ቻለ። ይህች ጎል ለአዲስ በውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ጎል ሆናም ተመዝግባለች።

በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ሲዳማዎች በ75ኛው ደቂቃ በአዲስ ግደይ ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጎል ሙከራም ሆነ ጎል አይቆጠርበት እንጂ የሲዳማ ቡና  የበላይነት ጎልቶ የወጣ ሲሆን አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃ የሚያደርጉት የተጫዋቾች ቅያሪ ሁሉ ከደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ያስተናግዱ ነበር።

ዘጠናው ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ገዛኸኝ ሰዓት ለማባከን ሆን ብለህ ወድቀሀል በማለት የጨዋታው ዳኛ እያሱ ፈንቴ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውት ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ በሜዳው ተከታታይ ሁለት ጨዋታን በሽንፈት እና በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው አዳማ በሁለት ነጥብ አስራ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡናዎች አንድ አሸንፈው ሁለት አቻ ወጥተው በአምስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ጨዋታውን በመቆጣጠር፤ ሦስት ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድ በመስጠት ጨዋታውን አጠናቀዋል።


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ ፡LINK