አዳማ ከተማ የቀድሞውን ምክትል አሰልጣኝ ወደ ክለቡ መልሷል

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲሱ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም እየተመራ እስከ አሁን አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለውና በወትሮው ጥንካሬው ላይ የማይገኘው አዳማ ከተማ  የቀድሞው ረዳት አሰልጣኙ አስቻለው ኃይለሚካኤልን ወደ ክለቡ የአሰልጣኞች ስብስብ በድጋሚ መልሷቸዋል።

የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እና ተገኔ ነጋሽ ረዳት በመሆን ላለፉት አምስት ዓመታት ሲሰሩ የቆዩትና በክረምቱ የአሰልጣኝ ተገኔን መነሳት ተከትሎ አብረው ለመሰናበት ተገደው የነበሩት አሰልጣኝ አስቻለው በድጋሚ የአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም ረዳት በመሆን ወደ ክለቡ ተቀላቅለዋል። የአሰልጣኙ መምጣት ክለቡ ካለበት ውጤት እንዲያገግም እና ልምዳቸውን ለመጠቀም በማሰብ መሆኑን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ ከሆነ አሰልጣኙ በነገው እለት በይፋ ወደ ክለቡ የሚቀላቀሉ ሲሆን በክረምቱ የአሰልጣኝ ሲሳይ ረዳት ሆነው የተሾሙት ደጉ ዱባለ በስራቸው የሚቀጥሉ ይሆናል። በተያያዘም የአሰልጣኝ ቡድኑ ውስጥ የነበሩት ኤፍሬም እሸቱ ወደ ቀድሞ ስራቸው የታዳጊ ቡድን ወርደው እንዲሰሩም ተደርጓል።

አዳማ ከተማ በአምስተኛው ሳምንት ከተረታና በደረጃ ሰንጠረዡ 15ኛ ላይ ከተቀመጠ በኃላ የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም ላይ የክለቡ ደጋፊዎች ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡