ጅማ አባ ጅፋር የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተጋጣሚውን አውቋል 

የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ድልድል በዛሬው እለት በኮንፌዴሬሽኑ መቀመጫ ካይሮ ይፋ ሲደረግ ከቻምፒየንስ ሊጉ በአል አህሊ ተሸንፎ የወደቀው ጅማ አባ ጅፋር ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት በሚደረገው ጨዋታ ከሞሮኮው ሀሳኒያ ዩኤስ አጋዲር ጋር ተደልድሏል። 

ከቻምፒየንስ ሊጉ አደንኛ ዙር የወደቁ 15 ክለቦችን በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው አንደኛ ዙርን ካለፉ ክለቦች ጋር የሚያገናኘው ይህ ዙር ወደ ምድብ ድልድሉ የሚገቡ ክለቦችን ይለያል። የኢትዮጵያው ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋርም ከሞሮኮው ሀሳኒያ አጋዲር ጋር ተደልድሏል። የመጀመርያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ እሁድ ጥር 5 ቀን 2011 የሚደረግ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ አጋዲር ላይ ከአንድ ሳምንት በኋላ የሚከናወን ይሆናል።

በ2017/18 የቦቶላ ፕሮ 3ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ወደ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ያመራው ሀሳኒያ ዩኒየን ስፖርት ዲ’አጋዲር በዚህ ውድድር በታሪኩ ለሦስተኛ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን በአንደኛው ዙር የሴኔጋሉ ጄኔሬሽን ፉትን በአጠቃላይ ውጤት 2-1 በማሸነፍ ነበር ወደ ሁለተኛው ዙር ያለፈው። በአርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ሚጌል አንሄል ጋሞንዲ የሚመራው ክለቡ በዘንድሮው የሀገሪቱ ሊግ (ቦቶላ ፕሮ) ጥሩ አጀማመር በማድረግ ከ11 ጨዋታዎች 20 ነጥቦች ሰብስቦ ከዋይዳድ ካዛብላንካ በ3 ነጥቦች በማነስ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሙሉ ድልድል 

ጎር ማሒያ (ኬንያ) ከ ኒው ሰታር ዱዋላ (ካሜሩን)

አህሊ ቤንጋዚ (ሊቢያ) ከ ሁሴይን ዴይ (አልጄርያ)

አል ሒላል (ሱዳን) ከ ሙኩራ ቪክትሪ (ሩዋንዳ)

ንካና (ዛምቢያ) ከ ሳን ፔድሮ (አይቮሪኮስት)

ኮተን ስፖርት (ካሜሩን) ከ አሳንቴ ኮቶኮ (ጋና)

ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) ከ ካይዘር ቺፍስ (ደቡብ አፍሪካ

ስታደ ማሊየን (ማሊ) ከ አትሌቲኮ ፔትሮሌኦስ (አንጎላ)

ራጃ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) ከ አፍሪካ ስታርስ (ናሚቢያ)

አርኤስ በርካኔ (ሞሮኮ) ከ አኤስሲ ጃራፍ (ሴኔጋል)

ሴፋክሲየን (ቱኒዚያ) ከ ቫይፐርስ (ዩጋንዳ)

ዛማሌክ (ግብፅ) ከ አይአር ታንገር (ሞሮኮ)

ኬሲሲኤ (ዩጋንዳ) ከ ኦቶሆ ዲ ኦዮ (ኮንጎ ሪፐብሊክ)

ባንቱ (ሌሶቶ) ከ ሬንጀርስ (ናይጄርያ)

አል ናስር (ሊቢያ) ከ ሳሊታስ (ቡርኪናፋሶ)

ጅማ አባ ጅፋር (ኢትዮጵያ የ) ሀሳኒያ አጋዲር (ሞሮኮ)