ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ነገ በአዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል በሚደረገው የሊጉ አስረኛ ሳምንት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በዘጠነኛው ሳምንት ድል የቀናቸው አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ነገ 09፡00 ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ይገናኛሉ። አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈት በኋላ ደቡብ ፖሊስን እና መከላከያን በመርታት ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ መጠጋት ችሏል። በመከላከያው ጨዋታ ያስቆጠራቸው ግቦች ብዛትም ከግብ ዕዳ እንዲወጣ አስችለውታል። አዳማ ከተማን በሜዳው የማሸነፍ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ውጤት ለማግኘት የሚጫወተው ድሬዳዋ ከተማም እንደተጋጣሚው ሁሉ መነቃቃት እየታየበት ይገኛል። ቡድኑ በፋሲል ከተሸነፈ በኋላ በሜዳው በደቡብ ፖሊስ ነጥብ ቢጥልም ከሶዶ በአቻ ውጤት መመለሱ እና የባህር ዳርን ያለመሸነፍ ጉዞ መግታት መቻሉ  ለድሬዳዋ መልካም ውጤት ነው። የሁለቱ ቡድኖች የአሸናፊነት መንፈስ ላይ መገኘትም ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር እንዲታይበት አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

በነገው ጨዋታ ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ የተመለሰው ዐመለ ሚልኪያስ እንዲሁም የመስመር አማካዩ በረከት ደስታ ለአዳማ ከተማ የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን  ሱራፌል ጌታቸው እና ኤፍሬም ዘካሪያስ ግን አሁንም ከጉዳት አለማገገማቸው ታውቋል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል በጉዳት ላይ የሚገኘው ብቸኛ ተጫዋች ራምኬል ሎክ ነው። ከዚህ ውጪ የስምንት ጨዋታዎች ቅጣት የተላለፈበት ላይቤሪያዊው አጥቂ ኢታሙና ኬይሙኒም ይህ ጨዋታ ያልፈዋል።

አዳማ ከተማ በመከላከያ ላይ ያስቆጠራቸው ግቦች የአጥቂዎቸን በራስ መተማመን እንደሚጨምርለት ዕሙን ነው። ይህንን ጨዋታ በሜዳው እንደማድረጉም ከመስመር አማካዮቹ በሚነሱ ኳሶች በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አካሄድን በመምረጥ ለዳዋ ሁቴሳ የግብ ዕሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክር ይጠበቃል። በዚህ ውስጥ ግን የመስመር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል ቅርፅ ያለው ድሬዳዋ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በተለይም ሚኪያስ ግርማ እና ረመዳን ናስር ወደ መስመር ተከላካዮቻቸው በመቅረብ አዳማ በነዚህ ቦታዎች ላይ የሚኖረውን አደገኝነት ለመቀነስ የሚጥሩ ይሆናል።

ዋነኛ አጥቂውን በጉዳት ምክንያት የማይጠቀመው ድሬዳዋ ከፊት አዲስ ጥምረትን መፍጠር ይጠበቅበታል። ሁለቱ የፊት አጥቂዎችም መሀል ለመሀል ከሚመጡ ኳሶች ይልቅ የመከላከል ኃላፊነት ሊጫናቸው ከሚችሏቸው የመስመር አማካዮቻቸው ጋር የሚፈጥሩት የቅብብል መስመር ወሳኝ ሊሆን ይችላል።  አማካይ ክፍል ላይ ግን በቦታው ድንቅ ብቃት እያሳየ የሚገኘው ከንዓን ማርክነህ የቁጥር የበላይነትን ሊይዝ ለሚችለው አዳማ አጠቃላይ የማጥቃት ሂደት ማዕከል እንደመሆኑ ቡድኑን የበላይ የማድረግ ዕድሉ የሰፋ ነው። ነገር ግን በተለይም ከሌሎቹ አማካዮች ጋር የሚኖረው ግንኙነት ከድሬው የተከላካይ አማካይ ፍሬድ መሸንዲ ጋር ከባድ ፍልሚያ እንዲያደርግ የሚያስገድድው ይሆናል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 14 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ ግማሹን በድል አጠናቋል ፤ ድሬዳዋ አራቱን አሸንፏል። 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 15 ፣ ድሬዳዋ 10 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

– አዳማ ላይ 7 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 5 አሸንፎ በ2 ጨዋታዎች አቻ ሲለያዩ ድሬዳዋ አሸንፎ አያውቅም።

– አዳማ ከተማ የሜዳ ጨዋታዎቹን በሽንፈት ቢጀምርም ሁለተኛውን አቻ ተለያይቶ የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በድል አጠናቋል።

– ድሬዳዋ ከተማ ከሜዳው በወጣባቸው ሦስት ጨዋታዎች ድል ባይቀናውም ሁለት ነጥቦችን ይዞ ተመልሷል።

ዳኛ

– እስካሁን በሁለት ጨዋታዎች አስራ ሰባት የቢጫ ካርዶችን አሳይቶ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠው ቢኒያም ወርቅአገኘው ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱራፌል ዳንኤል  – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ቴዎድሮስ በቀለ

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ

ቡልቻ ሹራ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሁቴሳ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሃንስ

ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ –  ምንያህል ይመር – ረመዳን ናስር

ሐብታሙ ወልዴ – ኃይሌ እሸቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *