የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 3-2 ደቡብ ፖሊስ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛው ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ደቡብ ፖሊስን 3-2 በሆነ ውጤት ካሸነፈበት የዛሬው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች እንደሚከተለው ሰጥተውናል፡፡

“ጎሎች ማስቆጠር ቻልን እንጂ እነሱ በተሻለ ሁኔታ  ተጫውተዋል” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ድሉ

“ጨዋታው ዛሬ በጣም ከብዶናል። ጎሎች ማስቆጠር ቻልን እንጂ እነሱ በተሻለ ሁኔታ  ተጫውተዋል፡፡ ዛሬ ስብስባችን ላይ ችግር ነበር፤ ሁለት ተጫዋቾች በአምስት ቢጫ ወጥተውብናል። አዲስዓለም እና ፍቅረየሱስ፤ በተለይ ደግሞ ዳንኤል እና ደስታ ቢኖሩ በሚገባ መስመራችንን እንጠቀም ነበር። ዛሬ የሁለቱ ያለመኖር የመስመር አጨዋወታችን እንዳንጠቀም አድርጎናል። ብልጫ መውሰድ ባንችልም የመጫወት ፍላጎታችን ጥሩ ነበር፡፡ የነሱ አጨዋወት ግን ከነሱ የተሻለ ሆኖ ነበር፡፡ ”

ስለ ምንተስኖት ተቀይሮ መውጣት እና የብሩክ ውጤታማ ቅያሪ

“የብሩክ ተቀይሮ መግባት ለውጤቱ አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በቀየርነው ሰዓት ነው ግቦቹ የተገኙት። አንድ አግብቶ አንድ ደግሞ አቀብሏል። ስለዚህ ይህን ስትመለከት ቅያሪው ጥሩ መሆኑን ትመለከታለህ፡፡ የምንተስኖት ሙሉ ለሙሉ ስንጠቃ የነበረው በሱ በኩል ነው። አንድ ተጫዋቾች አቅሙን አውጥቶ መጫወት ካልቻለ ይቀየራል፤ በጣም ጠብቀነዋል። ኳስን ይነጠቅ ነበር፤ ይሳሳት ነበር። ሳንቀይረው የጠበቅንበት ምክንያት ልምድ ያለው ነው ብለን እንጂ ወጣት ተጫዋቾች አሉን። ከተሳሳተ ደግሞ መቀየሩ ግድ ነው። ”

“ዛሬን አሸነፈን ቢሆን ኖሮ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የማንገባባቸው ነገሮችን እንፈጥር ነበር” ዘላለም ሽፈራው – ደቡብ ፖሊስ

ስለ ጨዋታው

” ጨዋታው ለኛ ጥሩ አልነበረም። ነጥብ ጥለናል፡፡ ሀዋሳን አሸነፈን እንወጣለን የሚል እምነት ነበረን። ሜዳ ላይ የታየው ግን ያ አይደለም፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የኛ ቡድን ትንሽ ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ተመርተን አቻ ሆነን እረፍት ወጥተናል፡፡ ነገር ግን የሚቆጠሩብን ጎሎች በጣም በቀላሉ ነው፡፡ የመከላከል አቅማችንም እንደወትሮው አይደለም። እንደ አጠቃላይ ዛሬ በጣም ደካማ እንቅስቃሴ ነበር የነበረው። ጎሎች አስቆጥረናል፤ ግብ ሊሆኑ የሚችሉትንም አግኝተናል። እነዛን ግን መጠቀም አልቻልንም፡፡ ይህ ደግሞ የአጨራረስ ድክመት እንደነበረብን ያሳያል፡፡ ዛሬን አሸነፈን ቢሆን ኖሮ አስቸጋሪ ሁኔታወች ውስጥ የማንገባባቸው ነገሮች እንፈጥር ነበር፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *