ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማን ከደቡብ ፖሊስ ያገናኘው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ሀዋሳ ከተማ በ11ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ አዲስዓለም ተስፋዬ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንን በአምስት ቢጫ ካርድ በማሳረፍ አክሊሉ ተፈራ እና ምንተስኖት አበራን በአሰላለፉ ሲያካትት ደቡብ ፖሊሶች በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገደው ስብስባቸው የአራት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ በብርሀኑ በቀለ፣ ኤርሚያስ በላይ፣ የተሻ ግዛው እና በኃይሉ ወገኔ ምትክ አበባው ቡታቆ፣ ዮናስ በርታ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ እና ልዑል ኃይሌን ተጠቅመው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ 

ፌዴራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ እግሩ ላይ መጠነኛ ህመም ቢከሰትበትም ሙሉ የጨዋታውን ክፍለ ጊዜ ሳይቸገር በመራበት ጨዋታ ደቡብ ፖሊሶች የተሻለ አጀማመር ማድረግ ቢችሉም አመዛኙን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በቀጥተኛ ኳስ ወደ ኄኖክ አየለ በማድረስ ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ለማሳደር ያደረጉት ሙከራ ፍሬያማ አልነበረም። በእንቅስቃሴ በደቡብ ፖሊስ ብልጫ ቢወሰድባቸውም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠሩ ያልቸገሩት ሀዋሳዎች ደመየግሞ እንደተለመደው ወደ ጎን ሜዳውን በመለጠጥ ለታፈሰ ሰለሞን ክፍተት ለመፍጠር ያለመ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም የታፈሰ ተጣማሪዎቹ በተለይም ምንተስኖት አበራ በተደጋጋሚ የሚሰራው የቅብብል ስህተት በቀላሉ ሲከሽፍባቸው ተስተውሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ምንተስኖት በ28ኛው ደቂቃ በዳዊት ታደሰ ተቀይሮ ወጥቷል። 

አዳነ ግርማ እና ታፈሰ ሰለሞን በፈጠሩት መልካም አጋጣሚ ሀዋሳዎች የመጀመሪያ የግብ እድል ከፈጠሩ በኋላ ደቡብ ፖሊሶች አከታለው ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ልዑል ከሙሉዓለም ያገኛትን ኳስ ሞክሮ ለጥቂት ስትወጣበት፤ በ15ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ አዳሙ መሐመድ በግንባር ገጭቶ በሀዋሳ ተከላካዮች ስትመለስ ኄኖክ አግኝቷት በድጋሚ ገጭቶ ለጥቂት ወጥታበታለች፡፡ 

18ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ተሻምቶ የነበረን ኳስ አዳነ እና የፖሊስ ተከላካይ እኩል በጭንቅላት ገጭተውት ስትመለስ ከሳጥን ብዙ ሳይርቅ የቆመው ታፈሰ ሰለሞን አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቧ በኋላ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው መጫወት ሀዋሳዎች የቻሉት በእስራኤል እሸቱ እና አዳነ ግርማ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች በቀላሉ ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡ 

የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተነሳሽነታቸውን ጨምረው የተጫወቱት ደቡብ ፖሊሶች በረጅሙ በሚሻገሩ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት በ31ኛው ደቂቃ ላይ ሰምሮላቸዋል። በረጅሙ ከራሳቸው የግብ ክልል የተነሳችው ኳስ የተከላካዮች እና የሶሆሆ ሜንሳህን ያለመናበብ በአግባቡ በመጠቀም አጥቂው ኄኖክ አየለ ግብ አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል። ጎሉ ለኄኖክ ተከታታይ ሶስተኛ ግቡ ሆና ተመዝግባለች። 

ከግቧ በኃላ አጥቅቶ ለመጫወት ያለመን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ሀይቆቹ በታፈሰ ሰለሞን በተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርጉም ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም። እስራኤል እሸቱ ከአዳነ ግርማ አግኝቶ ያልተጠቀመባት ተጠቃሽ ስትሆን ኄኖክ አየለም በደቡብ ፖሊስ በኩል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ግልፅ አጋጣሚዎች አግኝቶ አምክኗል። 

ከእረፍት መልስ ሁለቱም ክለቦች ግብ ለማስቆጠር ያለመ የተጫዋችን ቅያሪን አድርገዋል። ሀዋሳ ከተማዎች በቀላሉ ለጥቃት ሲጋለጡ በነበሩበት የግራ መስመር ተከላካዩ ያኦ ኦሊቨርን በማስወጣት የመስመር አጥቂው ብሩክ በየነን ሲያስገቡ ከቅያሪው በኃላ ዳዊት ታደሰን ከአማካይ ቦታው ወደ ኋላ ተመልሶ በመጫወት በሶስት ተከላካዮች ለመጫወት ችለዋል፡፡ ከቅያሪው በኋላ የቀኝ መስመሩን በብሩክ በየን በሚገባ መጠቀም የቻሉት ሀዋሳዎች ተሳክቶላቸዋል፡፡ ገና አንድ ደቂቃ እንደተቆጠረም ወደ ፖሊስ የግብ ክልል በቶሎ በመድረስ አዳነ ግርማ ከመሀል ሜዳ ወደ ብሩክ ያሻገራትን ኳስ ብሩክ ወደ ሳጥን ዘልቆ ገብቶ ለታፈሰ ሰለሞን ሰጥቶት ታፈሰ በግሩም አጨራረስ ለራሱ እና ለቡድኑ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን ወደ መሪነት መልሷል። አሁንም ተጨማሪ ግብ ለማከል ጊዜ ያልወሰደባቸው ሀዋሳዎች 48ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪው ታፈሰ ሰለሞን ያሻገረለትን ኳስ ተቀይሮ በመግባት ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ብሩክ በየነ በግንባር በመግጨት የሀዋሳን መሪነት ወደ 3-1 ከፍ አድርጓል፡፡ 

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ፈጣን ቅያሪን ያደረጉት ደቡብ ፖሊሶች ልዑልን በየተሻ ግዛው በመቀየር የፊት መስመሩን ለማጠናከር ጥረት አድርገዋል፡፡ 53ኛው ደቂቃ አበባው ቡታቆ ከቅጣት ምት አክርሮ መትቶ ሶሆሆ ሲተፋው በቅርብ ርቀት የነበረው የተሻ አገባው ሲባል ወደ ውጪ ለጥቂት አምልጣዋለች፡፡ በ63ኛው ደቂቃ ደግሞ የሀዋሳው ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ ኳስ በግብ ክልል ውስጥ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አበባው ቡታቆ አስቆጥሮ ደቡብ ፖሊስን ወደ ጨዋታው እንዲመለስ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል። 

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሀዋሳዎች በእጃቸው የገባውን ውጤት ለማስጠበቅ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ለማድረግ ሲሞክሩ ታይቷል፡፡ እስራኤል እሸቱ ከርቀት መትቶ ዳዊት አሰፋ በሚገርም ብቃት ያወጣበት እንዲሁም ኄኖክ ድልቢ በተመሳሳይ የመታትን ጠንካራ ኳስ አግዳሚውን ነክታ የወጣችበት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሀዋሳ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *