ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

ሽረ እና ወልዋሎን የሚያገናኘው ሌላው የሳምንቱ ጨዋታ ቀጣዩ የቅድመ ዳሰሳ ትኩረታችን ነው።

የሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ማሳካት የቻሉት እና ከዋና አሰልጣኛቸው ጋር የተለያዩት ስሑል ሽረዎች ነገ 09፡00 ላይ ከወልዋሎ ዓ /ዩ ጋር ይገናኛሉ። በገብረኪሮስ አማረ እየተመሩ ከበታቻቸው የሚገኘው ደደቢትን በሰዒድ ሀሰን ብቸኛ ግብ መርታት የቻሉት ስሑል ሽረዎች 9ኛው ሳምንት ላይ በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፉበት ጨዋታ በኋላ ሽንፈት ሳይገጥማቸው መቀጠልም ችለዋል። ድሉን ተከትሎም ከወራጅ ቀጠናው በመውጣት ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ማለት የቻሉ ሲሆን ነገም ውጤት ከቀናቸው ይበልጥ ከአደጋው ክልል የመራቅ ዕድል ይኖራቸዋል። ሁለት ተከታታይ የ1-0 ሽንፈት የደረሰባቸው ወልዋሎዎች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን የአሰልጣኛቸው ፀጋዬ ኪዳነማርያም መልቀቂያ ማስገባትም በሳምንቱ ከተሰሙ ዜናዎች መካከል ነበር። ከሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ለማለት እና ከሜዳ ውጪ ካሉባቸው ችግሮችም ለማገገም ከሽረው ጨዋታ ውጤት ይዘው መመለስ አስፈላጊያቸው ይሆናል። ይህን ማድረግ ከቻሉም ከአቻ ውጤት በቀር አስታናግዶ ከማያውቀው የሽረ ስታድየም በሦስት ነጥብ በመመለስ የመጀመሪያ ክለብ ይሆናሉ።

በጉዳት ላይ የከረሙ ተጫዋቾቹ ወደ ሜዳ እየተመለሱለት የሚገኘው ስሑል ሽረ አማካዩ ሰለሞን ገብረመድህንም ቢያገግምለትም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን ሳሙኤል ተስፋዬ ግን ከጉዳት መልስ ለጨዋታው ብቁ ሆኖ ቡድኑን እንደሚያገለግል ይጠበቃል። ሽረዎች በደደቢት ላይ ያስመዘገቡት ድል የመጀመሪያ እና ብቸኛ እንደመሆኑ የሚጨምርላቸው በራስ መተማመን በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከዚህ ባለፈ በመከላከያው ጨዋታ መምራት መቻሉ እንዲሁም ዳግም ከተመራ በኋላ አቻ መሆኑ እንዲሁም በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ግቦችን አለማስተናገዱ ካሳለፈው የውጤት ዝቅታ አንፃር ሲታይ መጠነኛ መነቃቃት ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል።

በወልዋሎ በኩልም ኤፍሬም ኃይለማርያም ከጉዳት የሚመለስ ሲሆን ኤፍሬም አሻሞ እና ዋለልኝ ገብሬ በጉዳት አፈወርቅ ኃይሉ ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር በተመለከተው ቀይ ካርድ ቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። በተለይም የኤፍሬም አሻሞ አለመኖር የቡድኑን የመጨረሻ የማጥቃት አቅጣጫ ወደ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ያደላ ሊያደርገው እንደሚችል ይታመናል። ይህም ግቦችን የማስቆጠር ችግር ያለባቸው ቢጫ ለባሾቹን ጥቃት ተገማች ሊያደርገው የሚችልበት ዕድል ሲኖር አማካይ ክፍል ላይም ከተጋጣሚያቸው አንፃር የቁጥር ብልጫ ሊወሰድባቸው መቻሉ ከሜዳቸው ውጪም ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ፊት በመግፋት መጫወት ምርጫቸው እንደመሆኑ ሌላኛው የሚያሰጋቸው ነጥብ ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– የነገው ጨዋታ ለሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

– ስሑል ሽረ በሜዳው ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች በሙሉ የአቻ ውጤት ነበር ያስመዘገበው። ከነዚህ ውስጥ አምስቱ ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ።

– በሰባት ጨዋታዎች ከሜዳቸው የወጡት ወልዋሎዎች ሦስት ጊዜ በሽንፈት ሲመለሱ ሁለት የአቻ እና ሁለት የድል ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል።

– ሁለቱ ቡድኖች ካደረጓቸው ጨዋታዎች ቁጥር አንፃር ከደደቢት በመቀጠል ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስቆጠሩ ሲሆን ወልዋሎ በስምንት ሽረ ደግሞ በስድስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል።

ዳኛ

– አዳነ ወርቁ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በሦስት ጨዋታዎች 11 የቢጫ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ሙሉጌታ ዓንዶም

ሳሙኤል ተስፋዬ – ደሳለኝ ደባሽ

ሰዒድ ሀሰን – ጅላሎ ሻፊ – ልደቱ ለማ

ኢብራሂማ ፎፋና

ወልዋሎ ዓ/ዩ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

ብርሀኑ አሻሞ – አስራት መገርሳ – አማኑኤል ጎበና

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – አብዱርሀማን ፉሰይኒ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *