ከፍተኛ ሊግ ሐ | መሪዎቹ ቡድኖች ነጥብ ጥለዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተከናውነው መሪዎቹ ቡድኖች ነጥብ ጥለዋል። ስልጤ ወራቤ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ እና ቤንች ማጂ ቡና ደግሞ ድል አስመዝግበዋል።

አርባምንጭ ከተማ 2-2 ነቀምት ከተማ

(በአምሀ ተስፋዬ)

ቅዳሜ በተደረገ የምድቡ ብቸኛ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከነቀምት ከተማ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ባለሜዳዎቹ ስንታየው መንግስቱ ባስቆጠረው ግብ መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን በ41ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል በሚል ቴክኒካል ክስ አስይዘው የመጀመሪያውን አጋማሽ በመሪነት አጠናቀዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ዳንኤል ዳዊት በ50ኛው ደቂቃ ለነቀምት ግብ አስቆጥሮ አቻ መሆን ሲችሉ በ81ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ውብሸት ሥዩም ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ነቀምትን ወደ መሪነት ቀይሯል። ሆኖም ከጎሉ በኋላ ከደጋፊ በተነሳው ረብሻ ጨዋታው ለ31 ደቂቃዎች ያህል ተቋርጦ ከተረጋጋ በኋላ ሊቀጥል ችሏል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ላይም ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል የእለቱ ዳኛ ቅጣት ምት ቢሰጡም ውሳኔቸውን በመለወጥ ፍፁም ቅጣት ምት አድርገውት ስንታየው መንግስቱ አስቆጥሮ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። 

ስለ ጨዋታው ሶከር ኢትዮጵያ የሁለቱን ቡድኖች አሰልጣኞች አናግራለች።

መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለጨዋታው 

ጨዋታው ጥሩ ነበር እኛ በመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ልዩነት ማስፋት የምንችልበት አጋጣሚ አግኝተን ነበር አልተጠቀምንበትም። እንዲሁም ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል። ይህንንም እግርኳስ በሚፈቅደው መንገድ ክስ አስይዘናል።

ስለተፈጠረው ነገር 

እውነት ነው። እነሱ ሁለተኛ ግብ ሲያስቆጥሩ ቅሬታ ከደጋፊ ተሰምቷል። ሆኖም ጨዋታው ቀጥሎ እኛ ጎል አግብተን አቻ መውጣት ችለናል።

ቾምቤ ገብረህይወት – ነቀምት ከተማ

ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ነበር። እኛ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ስናስቆጥር ህዝቡ ወደ ሜዳ ድንጋይ መወርወር ጀመረ። በዚህም ምክንያት ከ25 ደቂቃ በላይ ተቋርጧል። የነበረው ፀጥታ ኃይል ነገሮች ሲፈፀሙ በዝምታ ነበር የሚያዩት። የፀጥታ ኃይሉ እኔንም ወስደውኝ ነበር። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በተንቀሳቀስንበት ወቅት ስሜት ውስጥ እየገባህ እግርኳስን ማከናወን ከባድ ነው። አወዳዳሪው አካል ይህን ነገር በአግባቡ ሊቆጣጠር ያስፈልጋል።

በስፍራው የተገኙት የፋና ጋዜጠኞች 

በስፍራው የተከሰተው ነገር አላስፈላጊ ድርጊት ነው። ጨዋታው ለ31 ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር። የነበረው ኃይልም በቂ አልነበረም። ተጫዋቾች እና እኛ ማሐል ሜዳ ላይ የነበረን ሲሆን የማሐል ዳኛውም የተወረወረ ድንጋይም አግኝቶት ነበር፤ የከፋ ጉዳት አልደረሰበትም እንጂ። በስተመጨረሻ የመከላካያ ኃይል በመምጣቱ ትንሽ የተረጋጋው ጨዋታ ካለቀ በኋላ የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾችም ሆነ እኛም ከሜዳ የወጣነው ከ12:30 በኋላ ነው።

ስለ አርባምንጭ ሁለተኛ ጎል

ሁለተኛው ጎል ሲቆጠር ዳኛው ከመስመር ውጭ ነው በሚል የቅጣት ምት ሰጥተው የነበር ቢሆንም ረዳት ዳኛው 16 ክልል ውስጥ በመሆኑ ፍፁም ቅጣት ምት ነው በማለቱ ምክንያት ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ተለውጧል። 


ጅማ አባቡና 0-0 ነጌሌ ቦረና

(በቴዎድሮስ ታደሰ)

ጨዋታው ከሜዳ ላይ ጨዋታ ይልቅ የጅማ አባቡና ደጋፊዎች በቡድኑ ተጫዋቾች እና በአሰልጣኝ መኮንን ማሞ ላይ ቡድኑ እያሳየ ባለው አቋም ባለመሻሻሉ የሚያሰሙት ተቃውሞ ትኩረትን የሳበ ነበር፡፡ በጨዋታ ነገሌ ቦረናዎች ተከላክለው መጫወትን ሲመርጡ የአባ ቡና ተጫዋቾች በቅንጅት መጫወት እና በአግባቡ ኳስን መቀባበል እንኳን ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በመጀመርያው አጋማሽ በ8ኛ ደቂቃ ካርሎስ ዳምጠው ና በ 38ኛው ደቂቃ ካሚል ረሺድ ሙከራዎች ውጭ ይህነው ተብሎ የሚጠቀስ እቅስቃሴም ይሁን የጎል ሙከራ አልነበረም። 


ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ተሻሽለው ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም በ51ኛው ደቂቃ ላይ ካርሎስ ላይ በሰራው ጥፋት የነገሌው ናትናኤል ጌታሁን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ የተሰጠውን ቅጣት ምት ሮባ ወርቁ መቶት የነገሌው ግብ ጠባቂ እደምንም ያዳነበት ሙከራ ብቸኛው የዚህ አጋማሽ ሙከራ ነበር። ከዚህ በኋላም በሰው ቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ነገሌዎች ሙሉ ለሙሉ ወደ መከላከል ሲያመዝኑ ባለሜዳዎቹ አባ ቡናዎች ለረዥም ደቂቃዎች የነበራቸውን የቁጥር ብለጫ ሳይጠቀሙ አላማ የሌላቸው ረጃጅም ኳሶችን አብዝተው ታይተዋል። ጨዋታውም ከከፍተኛ ሊግ ደረጃ እጅግ ዝቅ ያለ አሰልቺ እእነረቅስቃሴ ታይቶበት  0-0 ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቅም በኋላም የአባ ቡና ደጋፊዎች ለረጅም ደቂቃዎች ከስታዲየሙ ሳይወጡ አሰልጣኙ እንዲለቁላቸው ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር።

ሌሎች ጨዋታዎች

(በአምሀ ተስፋዬ)

ሺንሺቾ ላይ በሳምንቱ እሁድ ተጠባቂ ከነበረው ጨዋታ አንዱ የነበረው ሺንሺቾ ከ ሀድያ ሆሳዕና ያደረጉት ጨዋታ ያለምንም ጎል ተጠናቋል። ከጨዋታው በፊት በዛ ያለ ተጫዎቾቻቸው በጉዳት ላይ እንደሚገኙ የገለፁት ሆሳዕናዎች ነጥብ በመጣላቸው መሪነታቸውን የሚያጠናክሩበትን እድል አምክነዋል። በዚህም ምክንያት የምድቡ መሪ ሆሳዕና ከተከታዩ አርባምንጭ የሚደርጉት ጨዋታ ከወዲሁ ተጣባቂ እንዲሆን አድርጎታል።

ቢሾፍቱ ላይ ካፋ ቡናን ያስተናገደው ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ 2-1 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ሦስት ነጥቦች ማሳካት ችሏል። ሚዛን አማን ላይ ቤንች ማጂ ቡና በጨዋታው መገባደጃ ላይ በዕውቀቱ ማሞ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ቡታጅራ ከተማን 2-1 ሲያሸንፍ ወራቤ ላይ ወራቤ ከተማ ከ ሻሸመኔ ያደረጉት ጨዋታ በወራቤ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *