ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ ባህር ዳር ከተማ

ሌላኛው የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት የመቐለ እና ባህር ዳር ተስተካካይ መርሐ ግብር ይሆናል።

ከአምስተኛው ሳምንት የተዘዋወረው የመቐለ 79 እንደርታ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ነገ 09፡00 በትግራይ ስታድየም ይካሄዳል። የሊጉን መሪነት የተረከቡት መቐለዎች ከድሬዳዋ በ2-1 ድል ከተመለሱ በኋላ ነው ባህር ዳርን የሚያስተናግዱት። ጨዋታው ሰባት ተከታታይ ድሎችን ነማስመዝገብ ድንቅ ጉዞ እያደረጉ የሚገኙት መቐለዎች የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት ከመጨረስ ባለፈ የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋት የሚረዳቸው በመሆኑ ወሳኝነቱ የጎላ ነው። በነዚህ ሳምንታት የቡድኑ ጠንካራ ግስጋሴ ውስጥ በሁሉም ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ድንቅ ብቃት ላይ መገኘትም ሌላ ትኩረትን የሚስብ ጉዳይ ሆኗል። መቐለ 70 እንደርታ ነገ በሜዳው በሚያደርገው በዚህ ጨዋታ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች ባይኖርም ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ አቼምፖንግ አሞስ ፣ ሐይደር ሸረፋ እና አሸናፊ ሃፍቱን ጉዳት ላይ የሚገኙ በመሄኑ ለቡድኑ ግልጋሎት አይሰጡም።

ከሁለት ተከታታይ የሜዳ ላይ ጨዋታቸው በኋላ ወደ መቐለ የሚያመሩት ባህር ዳሮች የመጨረሻ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ስሑል ሽረን ከረቱበት ጨዋታ ውጪ በቅርብ ሳምንታት በአቻ ውጤቶች እየተቀዛቀዘ የመጣውን አቋማቸውን እንደአጀማመራቸው ሁሉ በድል ለመዝጋት ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በመጀመሪያ የውድድር ዓመት በንፅፅር መልካም ጊዜን እያሳለፉ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ ውጤት ከቀናቸው ወደ አራተኝነት ከፍ የማለት ዕድልም አላቸው። ባህር ዳር ከተማ የመስመር አጥቂው ግርማ ዲሳሳን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ ሲያጣ በቋሚነት ተከታታይ ጨዋታዎችን ሲጫወት የቆየው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ደግሞ በጨዋታ መደራረብ ምክንያት ከስብስቡ ውጪ በማድረግ ወደ መቐለ ተጉዟል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– አምና ሊጉን የተቀላቀለው መቐለ 70 እንደርታ እና ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ባህር ዳር ከተማ የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

– መቐለ 70 እንደርታ በትግራይ ስታድየም ሰባት ጨዋታዎችን አድረጎ ስድስቱን በድል ሲወጣ በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል፡፡ ከስድስቱ ድሎች አራቱ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የተመዘገቡ ናቸው።

– ከሜዳው ውጪ በአንድ ጨዋታ ብቻ ግብ ሳያስቆጥር የወጣው ባህር ዳር ከተማ ከሰባት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ብቻ ሽንፈት ሲገጥመው ከቀሪዎቹ ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦችን አሳክቷል።

ዳኛ

– እስካሁን መቐለን አንድ ጊዜ ባህርዳርን ደግሞ ሁለት ጊዜ ያጫወተው ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በስድስት ጨዋታዎች 27 የቢጫ ካርዶች እና አንድ የቀይ ካርድ መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፍሊፔ ኦቮኖ

ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – ዮናስ ገረመው

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ያሬድ ከበደ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሐሪሰን ሄሱ

ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ዳንኤል ኃይሉ – ዳግማዊ ሙሉጌታ – ኤልያስ አህመድ

ወሰኑ ዓሊ – ጃኮ አራፋት – ፍቃዱ ወርቁ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *