ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዛሬ ከተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች አንዱ የነበረው የሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከተማ ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በሀዋሳ በኩል ባለፈዉ ሳምንት በወልዋሎ ከተረቱበት ጨዋታ አዲስዓለም ተስፋዬን በቅጣት በማጣታቸው በወንድማገኝ ማዕረግ ሲተኩ በአንፃሩ እንግዳዎቹ ፋሲሎች ሲዳማ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ የነበረውን የመጀመርያ አሰላለፍ ይዘው ገብተዋል።

በኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው በተመራው ጨዋታ ሀዋሳዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱ ቢሆንም በጊዜ ግብ ማስቆጠር የቻሉት ግን ፋሲሎች ነበሩ። በ5ኛው ደቂቃ የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ሰዒድ ሀሰን ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ሙጅብ ቃሲም የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብ በመቀየር  ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ 

ከግቡ መቆጠር በኋላም ተጭነው መጫወት የቻሉት ባለሜዳዎቹ አቻ ለመሆን ብዙ ደቂቃዎች አልፈጀባቸውም። በ14ኛዉ ደቂቃ በግራ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቸርነት አውሽ በጥሩ መንገድ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ወደ ግብነት ቀይሮ ሀዋሳ ከተማን አቻ አድርጓል፡፡ ከግቡ ሁለት ደቂቃዎች በኃላ እንዲሁም በ21ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቸርነት አውሽ ያመቻቸለትን ፍቅረየሱስ ከርቀት በመምታት አደንኛው ለጥቂት ወደ ውጪ ስትወጣበት ሌላኛውን ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኬ ሲተፋው በድጋሚ አዳነ ግርማ አግኝቶ ሞክሮ የፋሲል ተከላካዮች ተረባርበው  አውጥተውታል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ወደ መሪነት ለመሸጋገር ጥረት ያደረጉ ሲሆን በፋሲል ከነማዎች በኩል በ23ኛዉ ደቂቃ አጥቂዉ ኢዙ አዙካ ከርቀት በግራ እግሩ አክርሮ መትቶ ለጥቂት የወጣችበት እና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ 28ኛዉ ደቂቃ ላይ ከኢዙ አዙካ የተሻገረለትን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ጋር ደርሳ ግዙፉ ተጫዋች ሳይጠቀምባት የመከነችው ሲጠቀሱ ባለሜዳዎቹም 31ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ አዳነ ግርማ በጭንቅላቱ ሲያመቻችለት ዳንኤል ደርቤ አክርሮ መትቶ ሚኬል ሳማኬ ያዳነበት ይጠቀሳሉ።

ጨዋታው ቀጥሎ የመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጎሎች ተስተናግደዋል። 42ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ዓለሙ በጥሩ ሁኔታ የሰጠውን ኳስ ኢዙ አዙካ ወደ ግብነት ቀይሮ ዐፄዎቹን ወደ መሪነት ሲመልስ 44ኛዉ ደቂቃ ላይ አዳነ ግርማ ከዳንኤል ደርቤ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ የተከላካዮቹ ያሬድ ባዬ እና ከድር ኩሊባሊ ስህተት ታክሎበት ወደ ጎልነት ለውጦ ሀይቆቹ በድጋሚ አቻ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ግቡ ሲቆጠር አዳነ በተከላካዮቹ ላይ ጥፋት ፈፅሟል፤ ኳሱም የፌር ፕለይ ኳስ ነው በሚል ፋሲሎች ክስ አስመዝግበዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመርያው ጎሎችን ባያስመለክተንም በሁለቱም በኩል ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች የተስተናገዱበት ነበር። ዳንኤል ደርቤ በቀኝ የዐፄዎቹ የግብ ክልል ገፍቶ በመግባት ወደ ሳጥን የላካትን ኳስ አዳነ ግርማ ሞክሮ ጋር ሳማኬ ሲተፋው ወደ ዋናው ቡድን አድጎ ለመጀመርያ ጊዘ ጨወታ ያረገው መስፍን ታፈሰ ጋር ደርሳ በድጋሚ ሲሞክራት የወጣችበት በሀዋሳ በኩል የዚህ አጋማሽ የመጀመርያ ሙከራ ስትሆን 68ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ታፈሰ ሰለሞን በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር በድጋሚ የተገናኘው መስፍን ታፈሰ በቀላሉ ወደ ግብነት ለወጠው ሲባል ሚኬል ሳማኬ እንደምንም ያዳነበት ሌላው ጠንካራ ሙከራ ነው። ፋሲሎች በበኩላቸው 60ኛው ደቂቃ በቀኝ በኩል ወደ ግብ ክልል በሽመክት አማካነኝነት የተሻገረችውን ኳስ  ኤፍሬም ዓለሙ በቀጥታ መሬት ለመሬት አክርሮ መትቶ ሶሆሆ ሜንሳህ እንደምንም የያዛት ቀዳሚ እና ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።

ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ጨዋታው እንደ መጀመርያ አጋማሽ የግብ እድል ለመፍጠር እና አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት ለመለወጥ ሲያደርጉ የነበሩት ጥረት ውጤታማ ያልነበረ ሲሆን እንደ መልካም ነገር ከተጠቀሰ መስፍን ታፈሰ በመጀመሪያ ጨዋታው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማድረጉ ከበርካቶች አድናቆት ሲተቸረው ለተጫዋቾቹም በስታዲየሙ ባነር አሰርተው በመግባት ሲያበረታቱትም ተስተውሏል፡፡

ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 2-2 በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሀዋሳ ወደ አምስተኛ ከፍ ሲል ፋሲል በነበረበት አራተኛ ላይ ረግቷል ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *