ዳኞች ክፍያ ባለመፈፀሙ ቅሬታ አሰሙ

በፕሪምየር ሊጉ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ለዳኞች ሊከፈል የሚገባው ክፍያ መዘግየቱን ተከትሎ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በ2011 የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ለዳኞች የሚፈፀመው ክፍያ ዙሪያ የአሰራር ለውጥ ማድረጉ ይታወሳል። ነገር ግን አሁን አሁን የገንዘብ ክፍያው በጊዜው አለመፈፀሙ በዳኞች ዘንድ ቅሬታን እያስነሳ ይገኛል። በተለይም በአንደኛው ዙር መገባደጃ ላይ በነበረው የዳኞች እና ታዛቢዎች ስብሰባ ላይ የታደሙ አካላት በክፍያ ሁኔታ ላይ ጥያቄ ሲያነሱ ተደምጠዋል። ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዳኞች ለሶከር ኢትዮዽያ እንደተናገሩት ክፍያቸው ከዛሬ ነገ ይሰጣችኋል እየተባሉ ከ15 ቀናት በላይ እንዳለፋቸው ያስረዳሉ። ለጨዋታዎች በሰላም መጠናቀቅ የግል ጥረታቸውን ጨምረው በመስራት ላይ እንደሚገኙ የሚገልፁት ዳኞቹ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሪሽን የበላይ አካላቶች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ችግሩ የመነጨው ከባንክ ስርዓት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተናግረዋል። ኃላፊው በየሳምንቱ በሁሉም የሊግ እርከኖች የሚደረጉ ጨዋታዎች በርካታ መሆን የተከፋይ ዳኞችን ቁጥር እስከ 300 የሚያደርሰው በመሆኑ ክፍያውን በቶሎ ለመፈፀም በፌዴሬሽኑ በኩል ዝግጁነቱ ቢኖርም ከባንክ ሲስተም መቆራረጥ ጋር ተያይዞ መዘግየቱ ሊፈጠር እንደቻለ አብራርተዋል።

ከዚህ ቀደም የከፍተኛ ሊግ እና የብሔራዊ ሊግ ዳኞች በተመሳሳይ ‘ገንዘብ ሊከፈለን አልቻለም’ በማለት ቅሬታቸውን አሰምተው ከቀናት መዘግየት በኋላ ፌዴሬሽኑ ክፍያውን የፈፀመ ሲሆን አሁንም ችግሩ ከስር መሰረቱ አለመወገዱ እንዲሁም በፍጥነት አለመፈፀሙ ጉዳዩ ቀጣይነት እንዳይኖረው የሚያሰጋ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡