ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ ፋሲል ከነማ


በነገው ዕለት ከሚደረጉት ሶስት ጨዋታዎች አንዱ የሆነው እና ሊጉን በሁለተኛነት የሚከተለው ፋሲል ከነማ ወደ መቐለ አቅንቶ የሚያደርገው ተጠባቂ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በሁለተኛው ዙር ካሳዩት መጠነኛ መነሳሳት በኃላ በተለያዩ የሜዳ ውጭ ችግሮች ምክንያት ውጤታቸው የወረደው እና ያለፉትን ሶስት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደው በፕሪምየር ሊጉ የመቆየት ተስፋቸውን ያመነመኑት ደደቢቶች ተጋጣሚያቸው በጥሩ መነቃቃት የሚገኘው ፋሲል ከነማ እንደመሆኑ በአጨዋወታቸው ላይ በርካታ ለውጥ አድርገው ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለተኛውን ዙር በ 4-2-3-1 አጨዋወት ጀምረው ጋናዊ አጥቂያቸው ፉሴይኒ ኑሁ በቅጣት ካጡበት ጨዋታ በኋላ ከድሬዳዋ፣ ጅማ አባጅፋር እና ወልዋሎ ባደረጓቸው ጨዋታዎች አጨዋወታቸው ወደ 4-4-2 ቀይረው የነበሩት ሰማያዊዎቹ አጥቂያቸው ቅጣቱ ጨርሶ ለጨዋታ ዝግጁ በመሆኑ አጨዋወታቸው ወደ ቀደመው የተጫዋቾች አደራደር ምርጫቸው ሊቀይሩ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ እንደሆነ ይታመናል። ደደቢቶች በዚህ ጨዋታ የፉሴይኒን ግልጋሎት ማግኘታቸው መልካም ዜና ቢሆንም መድኃኔ ብርኃኔን በቅጣት አያሰልፉም።

ባለፈው ሳምንት የመቐለ 70 እንደርታን መሸነፍ ተጠቅመው ከመሪው ጋር የነበራቸው ልዩነት በማጥበብ የዋንጫ ፉክክሩን ይበልጥ አጓጊ ያደረጉት ዐፄዎቹ ይሄን ጨዋታ ማሸነፍ ለሰዓታትም ቢሆን ከመሪው መቐለ ጋር ያላቸው ልዩነት እንዲያጠቡ ስለሚያደርጋቸው እና ይበልጥ ጫና እንዲፈጥሩ ስለሚያስችላቸው ይህን በአግባቡ ለመጠቀም አልመው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዋነኝነት በኳስ ቁጥጥር ተመስርተው የተጋጣሚን አቀራረብ ተከትለው መሃል ለመሃል በኤፍሬም ዓለሙ እና ሱራፌል ዳኛቸው እንዲሁም በሁለቱም መስመሮች ለማጥቃት የሚሞክሩት ዐፄዎቹ በዚህ ጨዋታ የሚያጠቁበትን መንገድ ለመገመት አዳጋች ቢሆንም ተጋጣሚያቸው ደደቢት ለመስመር ጥቃቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚጫወት ቡድን እንደመሆኑ እና የፈጣሪ አማካዮቻቸው ብቃት በየጨዋታው መጎልበት መሃል ለመሃል የሚደረጉት የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ምርጫው ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠቁማል። በተቃራኒው ሽመክት ጉግሳን ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ደግሞ የመስመር አጨዋወታቸውን ሚዛናዊ ሊያደርገው ይችላል።

ከዚ በተጨማሪ ሃዋሳ ላይ ከተቆጠረባቸው ሁለት ግቦች እና ሜዳቸው ላይ በደቡብ ፖሊስ ከተቆጠረባቸው አንድ ግብ ውጭ በአምስት ጨዋታዎች ግባቸው ሳያስደፍሩ የወጡት ዐፄዎቹ ተጋጣሚያቸው በዓመቱ ጥቂት ግብ ያስቆጠረ እና ጠንካራ የሚባል የአጥቂ ክፍል የሌለው ቡድን እንደመሆኑ ከባለፉት ጨዋታዎች በተሻለ የተከላካይ ክፍላቸው ወደ መሃል ሜዳው በማስጠጋት ያጠቃሉ ተብሎ ይገመታል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ አምስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለት ሁለት ጊዜ ተሸናንፈው አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ግብ በማስቆጠሩም በዕኩል አራት ግቦች ለነገው ጨዋታ ደርሰዋል።

– ደደቢት በትግራይ ስታድየም ላይ ባደረጋቸው 13 ጨዋታዎች ሁለት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ሲያስመዘግብ በሌሎቹ ተሸንፏል።

– ፋሲሎች ከጎንደር ወጥተው ባደረጓቸው 11 ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ ሦስት ጊዜ ድል አድርገው በሌሎች ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፈዋል።

ዳኛ

– ደደቢትን ከመቐለ እና ጅማ እንዲሁም ፋሲል ከነማን ከሀዋሳ እና መከላከያ ጋር ያጫወተው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሰምነው ይህን ጨዋታ ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው አስር ጨዋታዎች አንድ የፍፁም ቅጣት ምት እና አንድ የቀጥታ ቀይ ካርድ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ 33 የማስጠንቀቂያ ካርዶችንም መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-2-3-1)

ሙሴ ዮሐንስ

ዳግማዊ ዓባይ – ዳዊት ወርቁ – አንቶንዮ አቡዋላ – ሄኖክ መርሹ

ያብስራ ተስፋዬ – ኤፍሬም ጌታቸው

አቤል እንዳለ – ዓለምአንተ ካሳ – እንዳለ ከበደ

ፉሴይኒ ኑሁ

ፋሲል ከነማ ( 4-3-3)

ሳማኬ ሚኬል

አምሳሉ ጥላሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – ሰዒድ ሐሰን

ኤፍሬን ዓለሙ – ሐብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡