ጳውሎስ ጌታቸው ከባህር ዳር ከተማ ጋር ለመቆየት መስማማታቸውን ክለቡ አስታወቀ

ከትላንት በስተያ ከተደረጉ የ22 ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የባህር ዳር ከተማ እና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ 3-3 አቻ መጠናቀቁ ይታወሳል። በጨዋታው 2-0 ሲመሩ የነበሩት የጣናው ሞገዶቹ በስምንት ደቂቃ ልዩነት ሶስት ጎሎች ተቆጥሮባቸው እስከ 81ኛው ደቂቃ ድረስ ሲመሩ ቆይተዋል። በተለይ በዚህ ሰዓት በስታዲየሙ የተገኘው ደጋፊ በተጨዋቾቹ እንቅስቃሴ እና በአሰልጣኙ የተጨዋች ቅያሪ ደስተኛ ባለመሆን ድምፁን ሲያሰማ እንደነበር ታዝበናል። ይህንን ተከትሎ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ጳውሎስ ከክለቡ በራሳቸው ፍቃድ መልቀቃቸውን ለሚዲያዎች መግለፃቸውን እና ረቡዕ እለት የመልቀቂያ ደብዳቤ እንደሚያዝገቡ መዘገባችን ይታወሳል።

ይሁንና ዛሬ አመሻሽ አዲሶቹ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ከተጨዋቾቹ ጋር በአካል እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ ማክሰኞ ማታ ካመሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ለማወቅ ችለናል። በስብሰባው በርከት ያሉ ጉዳዮች መነሳታቸውን የገለፁልን የክለቡ የቦርድ አመራሮች በተለይ ከአሰልጣኙ ጋር ረዘም ያለ ድርድር እንደተደረገ አረጋግጠውልናል። በዚህም መሰረት እስከ ዛሬ ድረስ የልቀቁኝ ደብዳቤ በይፋ ለክለቡ ያላስገቡት አሰልጣኙ እንዲመለሱ እንደተደረገ ተገልጿል።

በስብሰባው ከአሰልጣኙ ጉዳይ ውጪ የተለያዩ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን በተለይ ቡድኑ ከሜዳ ውጪ ሲጫወት የሚያስመዘግበውን ውጤት ለማስተካከል ውይይት እንደተደረገ ለማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡