የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 ደቡብ ፖሊስ


በአዲስ አበባ ስታድየም ከ10፡00 ጀምሮ የተከናወነው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደቡብ ፖሊስ ጨዋታ ያለግብ ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች እንዲህ ብለዋል።

“ክለቡን ወደ ፊት ለማራመድ እና ለክለቡ ጥቅም ስል ማድረግ አለብኝ ብዬ የማስበውን ነገር አደርጋለው።” ስትዋርት ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

“በጨዋታው የበላይ ነበረን ፤ ግብ ማስቆጠር ግን አልቻልንም። በልምምድ ላይ ወደ ግብ በመሞከር ፣ በአጨራረስ ፣ በማሻማት እና በሌሎች ላይም ብዙ እንሰራለን ሜዳ ላይ ግን ምንም ማድረግ አልቻልንም። አንዳንድ ተጫዋቾች በራስ መተማመናቸውን አጥተዋል። ሌሎች ደግሞ የደጋፊውን ጫና መቋቋም አልቻሉም። ይደነግጣሉ ፣ ስሜታዊ ይሆናሉ ፤ የተሳሳቱ ውሳኔዎችንም ይወስናሉ። ዞሮ ዞሮ እኔ ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለብኝ አምናለው። ስለዚህ ክለቡን ወደ ፊት ለማራመድ እና ለክለቡ ጥቅም ስል ማድረግ አለብኝ ብዬ የማስበውን ነገር አደርጋለው።”

ድካማ ጎኖቻቸው

“ግብ ማስቆጠር አልቻልንም። አስር የሚሆኑ የማዕዘን ምቶች እና የቅጣት ምቶች አግኝተናል ፤ ሦስት እና አራት የሚሆኑ ቀላል አጋጣሚዎችንም አምክነናል። በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ቅብብላችን ጥሩ አይደለም ፣ ወደ ውስጥ የምንገባ ይመስላል ከዛ ቅብብሎቻችን እና ተሻጋሪ ኳሶቻችን ጥራት በቂ አይሆንም ወይንም ኳሶችን እንቀማለን። የብዙ ተጫዋቾች በራስ መተማመን ወርዷል። የደጋፊው ስሜት ሲቀዛቀዝ ስሜታዊ ይሆናሉ ፤ ውሳኔዎቻቸውም ይዛባሉ። በአጠቃላይ በድኑ መጥፎ ቦታ ላይ ነው የሚገኘው። ብዙ ጉዳቶች አሉብን በዚህ ላይ የምንጨምረው ተጫዋች የለም። ያሉትን ሁሉንም ተጫዋቾች ሞክረናል ፤ ግን የትኛውም ተጫዋች በትክክል መልሱን ማግኘት አልቻለም። ይህ አሳዝኖኛል ፤ ክለቡ ወደፊት እንዲራመድ ነገ ማድረግ ያለብኝን አደርጋለው።”

“ቡድኔ ጥሩ ነው የተጫወተው ፤ እንደፈለግኹትም ሆኗል” ገብረክርስቶስ ቢራራ – ደቡብ ፖሊስ

ስለጨዋታው

“የምንጫወተው ትልቅ ታሪክ እና ልምድ ካለው ቡድን ጋር በመሆኑ ቢያንስ በመልሶ ማጥቃት አሸንፈን ለመውጣት ፤ ካልሆነ ደግሞ አቻ ለመውጣት ነበር ዕቅዳችን። ይህንን ብናሳካም ባደረግነው ጨዋታ አቻ መውጣታችን ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም ከዕረፍት መልስ በሙሉ በልጠን ተጫውተናል። የሳትናቸው ጎሎችም የሚያስቆጩ ናቸው። ቡድኔ ጥሩ ነው የተጫወተው ፤ እንደፈለኩትም ሆኗል። በአዲስ አበባ ከፍታ ይሄን ያህል መንቀሳቀሳችን ትልቅ ነገር ነው።”

መከላከል ላይ ስለማተኮራቸው

“የቅዱስ ጊዮርጊስን አጨዋወት እና መቼ ግብ እንደሚያስቆጥር አይተናል። በአብዛኛው ከዕረፍት መልስ ግብ አያስቆጥሩም። ስለዚህ እስከ ዕረፍት በጥንቃቄ መጫወት ስለፈለግን ነው እንጂ ሌላ ጉዳይ አይደለም።”

ጠንካራ ጎኖች

“በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ነበርን ፤ በመከላከሉም የተሻልን ነበርን። መከላከላን ጥሩ ባንሆን ኖሮ ከመስመር በሚነሱ ኳሶቻቸው እንቸገር ነበር። ስለዚህ በመከላከሉ ጥሩ ነበርን ፤ ከፈጠርናቸው ዕድሎች አንፃርም በመልሶ ማጥቃቱም ጥሩ ነበርን ማለት እችላለው።”

የመውረድ ስጋት ?

“ስድስት ጨዋታ ብዙ ነው። በአንድ ጨዋታ ብዙ ለወጥ በሚታይበት ሁኔታ የምንሰጋበት ምክንያት የለም። እርግጠኞች ነን እንደምንድን። በተጫዋቾቼ እተማመናለው ይህን ቃሌን መጨረሻ ላይ ታዩታላችሁ አንፈራም ምንም የሚያወርደን ነገር የለም።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡