ከፍተኛ ሊግ ሀ | ሰበታ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ የሚያደርገውን ጉዞ አሳምሯል

በአምሀ ተስፋዬ እና ሚካኤል ለገሰ


የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሙሉ እሁድ ተካሂደው ሰበታ ከተማ መሪነቱን ሲያሰፋ ለገጣፎ ሽንፈት አስተናግዷል።

ሰበታ ላይ ሰበታ ከ ገላን ባደረጉት ጨዋታ ሰበታ 1-0 አሸንፎል። በሜዳው ያለመሸነፍ ጉዞውን ያጠናከረው ሰበታ ከተማ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ጫላ ድሪባ ባስቆጠረው ግብ አሸናፊ መሆን ችሏል። ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ለሶከር ኢትዮጵያ “ጨዋታው ብርቱ ፏክክር ታይቶበታል ተጋጣሚያችን ጠንካራ ነው። ድሉ ቡድናችን ላይ ትልቅ መነቃቃት የፈጠረ ነው። በቀጣይ ያሉትን ጨዋታዎች በማሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ነው እቅዳችን። ” ብለዋል።

ወደ አክሱም የተጓዘው ለገጣፎ በአክሱም ከተማ የ2-1 ሽንፈት ገጥሞታል። በ20ኛው ደቂቃ ላይ ነጋሲ ኃይሌ አክሱምን ቀዳሚ የምታደርግ ግብ አስቆጥሮ በአክሱም መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩ ሲሆን ከዕረፍት መልስ ለገጣፎ ለገዳዲ በበላይ ግብ አቻ መሆን ቢችልም በ84ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ቀሬ የአክሱምን የአሸናፊነት ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውም በአክሱም 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጎፋ ሜዳ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቡራዩ ከተማን አስተናግዶ ሐብታሙ ረጋሳ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል። በዘንድሮ ውድድር አመት ደካማ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ቡራዩ 11ኛ ሽንፈቱን አስተናግዶ በወራጅ ቀጠናው ተቀምጧል።

ወሎ ላይ ወሎ ኮምቦልቻ ከወልዲያ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ በጀመረ በአራተኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ጥላሁን ኮምቦልቻን መሪ ሲያደርግ በ70ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ ነጋሽ ለወልዲያ አቻነቱን ግብ አስቆጥሯል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ ፌዴራል ፖሊስን የገጠመው ደሴ ከተማ 1-0 በማሸነፍ በመልካም የውጤት ጉዞው ቀጥሏል። ለአንድ ስዓት ዘግይቶ በተጀመረው ጨዋታ በ37ኛው ደቂቃ ላይ በድሩ ኑርሁሴን ብቸኛዋን የደሴ ከተማ ጎል አስቆጥሯል።

ግርጌ ላይ የሚገኘው አውስኮድ በሜዳው አቃቂ ቃሊቲን ገጥሞ 1-0 አሸንፏል። እንደ አየር ንብረቱ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ደቂቃዎች እየቆጠሩ በሄዱ ቁጥር ጥሩ ፍክክር ታይቶበታል። በ9ኛው ደቂቃ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት የመሃል ሜዳ ተጨዋቹ ሐቁምንይሁን ገዛኸኝ አሻምቶት ሚካኤል ጆርጅ በግምባሩ በሞከረው ኳስ አውስኮዶች የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። በቀኝ መስመር በኩል ማጥቃት ፈልገው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ረጅሙን አጥቂ ሚካኤል ጆርጅን ኢላማ ያደረጉ የአየር ላይ ኳሶች በመላክ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በዚህም በ12ኛው ደቂቃ አለሙ ብርሃኑ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ሚካኤል በግምባሩ ለማስቆጠር ጥሮ መክኖበታል። ይህንን ሙከራ ያደረገው ሚካኤል በ17ኛው ደቂቃ ከርቀት የተሻገረለት ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮ ግብ ለማስቆጠር ሲጥር ጥፋት ተሰርቶበት አውስኮዶች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱን ሐቁምንይሁን ገዛኸኝ መቶ ግብ ጠባቂው ታምራት አምክኖበታል።

ከደቂቃ በኋላ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ አቃቂዎች የግብ ክልል የደረሱት ባለሜዳዎቹ በግምባር በሞከሩት አስደንጋጭ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ነበረ። በመሃል ሜዳው ብልጫ የተወሰደባቸው አቃቂ ቃሊቲዎች ተረጋግተው መጫወት ተስኗቸው ኳሶችን በተደጋጋሚ ሲያበላሹ ታይቷል። አቃቂዎች የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ በማድረግ ወደ አውስኮዶች የግብ ክልል የደረሱት በ20ኛው ደቂቃ ነበረ። በዚህ ደቂቃ ጌትነት ታፈሰ ያሻገረውን የቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ሲተፋው ያገኘው ሱልጣን ከድር ግብ ለማስቆጠር ሲመቻች የአውስኮድ አምበል ልደቱ በፍጥነት በመገኘት ኳሱን አውጥቶታል። ይህንን ሙከራ ካደረጉም በኋላ ወደ ራሳቸው የሜዳ ክፍል ተጠግተው ሲጫወቱ የነበሩት ተጋባዦቹ በ25ኛው ደቂቃ ሳሙኤል አባተ በሞከረው የግምባር ኳስ ግብ ለማስተናገድ እጅጉን ተቃርበው ነበረ። የባለሜዳዎቹ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያ ሆኖ ሲጫወት የነበረው ሚካኤል በ34ኛው ደቂቃም ከሳሙኤል የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀም ቡድኑን መሪ ለማድረግ ተቀርቦ ነበረ። ያገኙትን የግብ እድሎች መጠቀም የተሳናቸው አውስኮዶች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በፈጠሩት ሌላ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ መሪ ለመሆን ጥረው ነበረ።

ቁልፍ የተጨዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ፍክክር አስመልክተዋል። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ተዳክመው የነበሩት ተጋባዦቹ አቃቂዎች በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአንፃራዊነት ጠንክረው ተንቀሳቅሰዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ወስደው የነበሩት አውስኮዶች ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በአምስተኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። ሳሙኤል ከመስመር ላይ መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ኤርሚያስ ኃይሌ ተቀይሮ በገባ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ግብ ካስተናገዱ በኋላ የተነቃቁት አቃቂዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫናዎችን ከየአቅጣጫው ሲሰነዝሩ ታይቷል። በዚህም በ63ኛው ደቂቃ የአውስኮድ ተጨዋቾች የተሳሳቱትን ኳስ ተጠቅሞ ሳምሶን ተሾመ ከርቀት ጥሩ ሙከራ አድርጎ መክኖበታል። እራሳቸውን ለመልሶ ማጥቃት አጋልጠው ሲጫወቱ የነበሩት አቃቂዎች በ67ኛው ደቂቃ በተሰነዘረባቸው አስደንጋጭ የመልሶ ማጥቃት ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተቃርበው ነበረ። ከአራት ደቂቃ በኋላ ወደ አውስኮዶች የግብ ክልል የደረሱት አቃቂዎች ከግራ መስመር አሻምተው ሳምሶን በግምባሩ በሞከረው ሙከራ አቻ ለመሆን ጥረዋል። የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችን በጥብቅ መከላከል የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ ግብ ሳይቆጠርባቸው አሸንፈው ወጥተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: