ከፍተኛ ሊግ ሐ | ሀዲያ ሆሳዕና መሪነቱን በማስፋት ወደ ፕሪምየር ሊግ በሚያደርገው ግስጋሴ ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ሲካሄዱ ሀዲያ ሆሳዕና መሪነቱን ያሰፋበትን ድል አስመዝግቧል። ተከታዩ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ሽንፈት አስተናግዷል።

ካፋ ቡና ላይ በተጣለው ቅጣት ምክንያት ቦንጋ ላይ ሊካሄድ የነበረው የካፋ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ወልቂጤ ላይ ተከናውኖ ሆሳዕና 2-1 አሸንፏል። 08:00 ላይ በተጀመረው ጨዋታ ካፋዎች በ12ኛው ደቂቃ አሸናፊ ካሳ ባስቆጠረው ጎል 1-0 መምራት ቢችሉም አምበሉ ትዕግስቱ አበራ በ35ኛው ደቂቃ ሆሳዕናን አቻ አድርጓል። ጨዋታው ለረጅም ደቂቃዎች በአቻ ውጤት ዘልቆ በዚሁ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ላይ ተመስገን ይልማ ወሳኟን የማሸነፍያ ጎል ለሆሳዕና ማስቆጠር ችሏል። ድሉን ተከትሎም የአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ቡድን በ7 ነጥብ ልዩነት መምራት ሲጀምር ከ2008 በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስም በግስጋሴው ቀጥሏል።

ሻሸመኔ ከተማ 2-0 አርባምንጭ ከተማ
(በሚሊዮን ኃይሌ)

ከረፋዱ 4:00 ይደረጋል ተብሎ መርሀግብር ወጥቶለት የነበረው ጨዋታ ሻሸመኔ ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው በመጨቅየቱ ወደ 8:00 ተለውጦ ተከናውኗል። ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ የደጋፊዎች ረብሻ የተስተዋለ ሲሆን በአርባምንጭ ተቀያሪ ወንበር ላይ በነበሩ ተጫዋቾች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞከርም አስተውለናል። ይህን የተመለከቱት የአርባምንጭ የክለብ አመራሮች ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል እንዲመጣ ቢጠይቁም የእለቱ ኮሚሽነር ሻምበል ተስፋጽዮን ጨዋታው እንዲካሄድ አድርገዋል። በመጀመሪው አጋማሽ ሻሸመኔ ከተማዎች በአንፃራዊነት የተሻሉ ቢሆኑም የተጫዋቾች ሽኩቻ የበዙበት ሳቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ የጨዋታው መለያ ነበር። በተለይም ደግሞ ግብ ጠባቂው ሲሳይ ባንጫ ከጨዋታው ጅማሬ አንስቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ተጫዋቾችም ሆነ ደጋፊውን ለብጥብጥ ሲያነሳሳ ተመልክተናል። ወደ ግብ ቀድመው መድረስ የቻሉት ባለሜዳዎቹ አብርሀም ዓለሙ አክርሮ መቶ ፅዮን መርዕድ የተቆጣጠራት ኳስ የጥቃታቸው ጅማሬም ነበረች። በቀኝ መስመር አድልተው ሲጫወቱ የነበሩት እንግዳዎቹ ደግሞ ወርቅይታደስ አበበ ከቀኝ ወደ ግብ በቀጥታ መትቶ ሲሳይ ባንጫ የያዘበት የምትጠቀስ ሙከራ ነበረች። 31ኛው ደቂቃ ዝናቡ ኃይለ ከግራ መስመር ያሻገራትን ኳስ የአርባምንጩ ተከላካይ አካሉ አበራ ስህተት ታክሎበት አሸናፊ ባልቻ ግብ በማድረግ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። አርባምንጮች በአምበላቸው አማካኝነት በሜዳ ላይ እና ከሜዳ ውጪ እየተፈፀመ ያለው ድርጊት ተገቢ አይደለም የሚል ክስ አስመዝግበው የመጀመሪያው አጋማሽም በባለሜዳው ሻሸመኔ ከተማ መሪነት ተገባዷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሻሸመኔ ከተማዎች ወደ ግባቸው አፈግፍገው ተከላክለው በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ እድሎችን ለመጠቀም ሲሞክሩ በአንፃሩ እንግዳዎቹ ተጋጣሚያቸው በአማካይ እና ተከላካይ ስፍራ ክፍተትን በመንፈጉ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል በቀኝ መስመር ጥሩ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረውን ፍቃዱ መኮንን ትኩረት አድርገው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። ፍቃዱ መኮንን ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ስንታየሁ መንግስቱ ሰብሮ ገብቶ ሲሞከር ሲሳይ ባንጫ ተንሸራቶ ያወጣበት ኳስም አርባምንጮች አቻ የምታደርግ ሙከራ ነበረች። ከሻሸመኔ የግብ ክልል በረጅሙ የተሻማውን ኳስ መልካሙ ቦጋለ በጭንቅላቱ ገጭቶ ከሳጥን ውጭ ለነበረው ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ ሲያቀብል ስህተት በመስራቱ ግብ ልትሆን ስትል ፅዮን ወደኋላ ተመልሶ በመሮጥ እንደምንም አውጥቷታል።

75ኛው ደቂቃ ላይ የሻሸመኔው አጥቂ ዳንኤል ኃይሌ የአርባምንጩን የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች አካሉ አበራ በክርኑ በመማታት በፊት ጥርሱ ላይ ጉዳት አድርሶበታል። ተከላካዩም በሜዳ ላይ በእንባ በታጀበ ድምፅ ለዳኛው ስሞታ ያቀረበ ሲሆን የእለቱ ዋና ዳኛ ሀብታሙ መንግስቴ ዳንኤልን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል። በዚህም የተነሳ ሻሸመኔዎች ካርዱ ተገቢ አይደለም በሚል ክስ አስይዘው ጨዋታው ከአስራ አንድ ደቂቃዎች መቋረጥ በኃላ በድጋሚ ጀምሮ 90ኛው ደቂቃ ሙሉቀን ተሾመ በረጅሙ ከፈይሳ ከድር የተላከለትን ኳስ የአርባምንጭ የተከላካይ ክፍል ስህተትን ተጠቅሞ ግብ በማድረግ የግብ ልዩነትን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎ ጨዋታው በሻሸመኔ ከተማ 2-0 ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሻሸመኔ ከተማ ጥቂት ደጋፊዎች በአርባምንጭ ተጫዋቾች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክሩ የታየ ሲሆን በዚህም የተነሳ የአርባምንጭ ተጫዋቾች ለ45 ደቂቃ ከስታዲየሙ ቅጥር ጊቢ ሳይወጡ ቆይተው በፀጥታ ኃይል ታጅበው ወደመጡበት ተሸኝተዋል፡፡ የአርባምንጭ ተከላካይ የሆነው አካሉ በጥርሱ ላይ የደረሰበት ህመም ወደ ሌላ የአዕምሮ ክፍል እንዳይዛመት በሚል ለተሻለ ህክምና ማምራቱን ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተጫዋቹን በተመለከተችበት ወቅት ለማወቅ ችላለች፡፡

ሌሎች ጨዋታዎች

ወደ ሚዛን አማን ያመራዉ ስልጤ ወራቤ ቤንች ማጂ ቡናን 1-0 በሆነ ዉጤት አሸንፎ ሦስተኛ ደረጃውን አስጠብቋል። በጨዋታው ብልጫ የነበራቸው ቤንች ማጂዎች በአጥቂዎቹ ኤሪክ ኮልማንና ወንድማገኝ ኬራ አማካኝነት ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። በተለይ ወንድማገኝ ከረጅም ርቀት የሚመታቸው ኳሶች ለግብ የቀረቡ ቢሆኑም በግብ ጠባቂው ጥረትና በግቡ አግዳሚ ግብ ከመሆን ድነዋል። የመጀመሪያው 45 የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ ነፃ ሆኖ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፍሬው ኪዳኔ በ44ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ስልጤ ወራቤን አሸናፊ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።

ነቀምት ላይ ነቀምት ከተማ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል። የነቀምት ከተማን የድል ጎሎች በ7ኛው ደቂቃ ብሩክ ብርሃኑ፣ በ62ኛው ዳንኤል ዳዊት እንዲሁም በ88ኛው ደቂቃ ቴዎድሮስ መንገሻ ሲያስቆጥሩ ዳንኤል የግብ መጠኑን 11 በማድረስ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን ለብቻው መምራት ጀምሯል።

ቦረና ላይ ነገሌ ቦረና ከሺንሺቾ ባደረጉት ጨዋታ እንግዳው ቡድን ሺንሺቾ 2-0 አሸንፏል። ኤፍሬም ታምራት እና ብርሃኑ ወርዶሏ ግቦን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ቡታጅራ ላይ ጅማ አባቡናን ያስተናገደው ቡታጅራ ከተማ በ25ኛው ደቂቃ ሙሲድ እንድሪስ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡