የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አዲስ ቻምፒዮን አግኝቶ ተጠናቀቀ

የ2011 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ ሲከናወኑ አዳማ ከተማ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ቻምፒዮን በመሆን ዋንጫውን ተረክቧል።

09:00 ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማን ጥሩነሽ ዲባባን ያገናኘው ጨዋታ በአዳማ 6-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በፈጣን እንቅስቃሴ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ባለሜዳዎቹ አዳማዎች በተደጋጋሚ በፊት አጥቂዎቻቸው አማካኝነት የሚፈጥሩት ጫና የበረታ ሲሆን ጥሩነሽ ዲባባዎች የአዳማን ጥቃት ለመመከት ከመጣር በቀር የሚጠቀስ እንቅስቃሴ ማሳየት አልቻሉም። ገና በ5ኛው ደቂቃ ሰናይት ቦጋለ ያስጣለችላውን ኳስ ወደ ፊት ገፍታ እክርራ መትታ በግብ ጠባቂዋ ጥረት ሲከሽፍ በድጋሚ በ9ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት በድጋሚ ሞክራ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወጥቷል።

ጨዋታው በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ቀጥሎ ባለሜዳዎች አዳማዎች ከኋላ ጀምሮ አደራጅተው በመምጣት የሚፈጥሩት የማጥቃት መንገዳቸው ለጥሩነሽ ዲባባ ተከላካዮች ፈታኝ የነበረ ሲሆን ተጋጣሚያቸውም ግቡን ሳያስደፍር መቆየት የቻለው ለ20 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 21ኛው ደቂቃ ላይ ነፃነት ፀጋዬ ያሻማችውን ኳስ የአዳማን ቀዳሚ ግብ ሴናፍ ዋቁማ በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራለች። ከግቡ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች በሎዛ እና ገነት ኃይሉ አማካኝነት ልዩነቱን የማስፋት እድል አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

በአጋማሹ የመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች መዘናጋት የታየባቸው የጥሩንነሽ ተከላካዮች ሶስት ግቦችን አስተናግደዋል። 41ኛው ደቂቃ ላይ ከአልፊያ ጃርሶ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ሴናፍ ዋኩማ በቀኝ እግሯ የምትመታ አስመስላ ወደ ግራ በማዞር የመታችው ኳስ ከመረብ አርፎ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ሎዛ አበራ በግምት 25 ሜትር ላይ አክራ የመታቹ ኳስ የግቡ የግራ መረብ ላይ አርፎ ልዩነቱ ወደ ሶስት ከፍ ሲል ከሰናይት የተላከውን ሰንጣቂ ኳስ ተጠቅማ በድጋሚ ሎዛ አበራ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ግብ አስቆጥራ የመጀመኣው አጋማሽ በአዳማ 4-0 መሪነት ተጠናቋል።

የአዳማዎች የበላይነት በድጋሚ በታየበት ሁለተኛ አጋማሽ 58ኛው ደቂቃ ላይ የጥሩነሽ የተከላካይ ክፍል ስህተት በፈጠረው አጋጣሚ ተጠቅማ ሎዛ አበራ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል አስቆጥራለች። በ77ኛው ደቂቃ በጨዋታው ድንቅ ብቃቷን ያሳየችው ሰናይት ቦጋለ ከሰርካዲስ ጉታ የተመቻቸላትን አጋጣሚ በግራ እግሯ አክርራ መትታ የግቡ መረብ ላይ በማሳረፍ የግቡን ብዛት ወደ ግማሽ ደርዘን ከፍ አድርጋዋለች።

በቀሩት 13 ደቂቃዎች አዳማዎች ጨሳታውን አቀዝቅዘው በመልሶ ማጥቃት የጎል አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ሲሆን የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በአዳማ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ማህሌት ድርሻ መትታ አምክናለች። ጨዋታውም በባለ ሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች 6-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።.

አዳማዎች ድሉን ተከትሎ በ58 ነጥቦች የ2011 የውድድር ዘመን ቻምፒዮን መሆን ችለዋል። በዚህም ሊጉ ከተጀመረበት 2005 ወዲህ ደደቢት እና ንግድ ባንክ ሲፈራረቁበት በነበረው ሊግ ከሁለቱ ክለቦች ውጪ ዋንጫውን ያነሳ የመጀመርያ ቡድን ሆነዋል። ከአዲስ አበባ ክለቦች ውጪ ዋንጫውን ያነሳ የመጀመርያው ክለብም ሆኗል።

እንደ ዋንጫው ሁሉ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብር አዲስ ተጫዋች አግኝቷል። የአዳማዋ ሴናፍ ዋቁማ በ21 ጎሎች ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ ከሎዛ አበራ አራት ተከታታይ ዓመታት ኮከብነት በኋላ የመጀመርያዋ ጫዋች ሆናለች። በሁለተኛው ዙር ወደ ሊጉ የተመለሰችው ሎዛ አበራ ደግሞ በአስደናቂ ሁኔታ 17 ጎሎች በማስቆጠር ከረሒማ ዘርጋው እና መዲና ዐወል በመቀጠል አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ አጠናቃለች።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአዳማ የወጣቶች ስፖርት ቢሮ እና የአዳማ ስፖርት ክለብ አመራሮች በተገኙበት በተከናወነው የሽልማት መርሐ ግብር አቶ ኢሳይያስ ጂራ ዋንጫውን ለአምበሏ ናርዶስ ጌትነት እና ሁለተኛ አምበል አልፊያ ጃርሶ አስረክበው የመርሐ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በ2005 ሲጀመር ደደቢት አራት፣ ኢትዮጵየ ንግድ ባንክ ሦስት፣ አዳማ ከተማ አንድ ጊዜ ቻምፒዮን መሆን ችለዋል።

ሌሎች መርሐ ግብሮች

በዕለተ ቅደሜ ሁለት ሌሎች መርሐ ግብሮች ተከናውነው የዋንጫ እድሉ በአዳማ ከተማ ነጥብ መጣል ላይ ተመርኩዞ ወደ አዲስ አበባ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአልፊያ ጃርሶ እና ረሒማ ዘርጋው ጎሎች 2-0 በመርታት ለተከታታይ አራተኛ ዓመት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ጥረት ኮርፖሬትን 4-0 አሸንፏል። ሀዋሳዎች ለአዳዲስ ፊቶች የተሰላፊነት ዕድልን በሰጡበት በዚህ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ፍፁም የጨዋታ ብልጫን ማሳየት ቻሉ ሲሆን 2ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ ላይ የተሰጠን ቅጣት ምት መሳይ ተመስገን በረጅሙ ወደ ግብ ስትልክ የጥረቷ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና ለመያዝ ስትሞክር ከእጇ በማምለጡ ዓይናለም አደራ  አግኝታ ለነህሚያ አበራ አመቻችታላት ነህሚያ በማስቆጠር ሀዋሳን በጊዜ መሪ ማድረግ ችላለች። 32ኛው ደቂቃ ላይ የጥረቷ አጥቂ ምስር ኢብራሂም እና የሀዋሳ ግብ ጠባቂ ትዕግስት አበራ በሀዋሳ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ ለማግኘት ሲጥሩ በተፈጠረ ግጭት በሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ ትዕግስት አበራ ላይ የምላስ መዋጥ እና በአንገቷ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ገጥሟት በሜዳ ላይ ራሷን ስታ የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻ በህክምና ባለሙያዎች ጥረት ልትተርፍ ችላለች። ለተጨማሪ ህክምና በሚልም ወደ ሆስፒታል በአምቡላንስ አምርታለች። በተደጋጋሚ ኳሶችን ስታበክን እና በግብ ጠባቂዋ ታሪኳ ሲመለስባት የነበረችው መሳይ ተመስገንም ሁለተኛ ግብ ለሀዋሳ አስቆጥራ እረፍት ወጥተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አሁንም ብልጫ የነበራቸው ሀዋሳዎች ቢሆንም ጥረቶችን ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወቱ ረገድ ተሽለው ታይተዋል፡፡ 47ኛው ደቂቃ ላይ ከመሳይ ተመስገን ያገኘችውን ኳስ መቅደስ ተሾመ አስቆጥራ የሀዋሳን መሪነት ወደ ሦስት ስታሳድግ 60ኛው ደቂቃ በግሩም አጨራረስ መሳይ ተመስገን ለራሷ 2ኛ ሀዋሳን ደግሞ ወደ 4-0 ድል ያሸጋገረች ግብ ልታስቆጥር ችላለች። ጨዋታውም 4-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ (ቴዎድሮስ ታከለ)



© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡