ሪፖርት| ስሑል ሽረዎች ከመውረድ ሲተርፉ ጅማ እና ሀዋሳ ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ስሑል ሽረ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና ሀዋሳ ከተማ ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈዋል። ስሑል ሽረም በሊጉ መሰንበቱን አረጋግጧል

ወልዋሎ 1-2 ስሑል ሽረ

(ማቲያስ ኃይለማርያም)

04:00 ላይ በትግራይ ስታዲየም የተደረገው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር እና በርካታ የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። በአጋማሹ ተመጣጣኝ የሆነ የጨዋታ እንስቃሴ የታየ ሲሆን በሙከራ ደረጃ ሲታይ ግን የቢጫ ለባሾቹ ፍፁም ብልጫ የታየበት ነበር። ኤፍሬም አሻሞ ከርቀት ባደረገው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ቢጫ ለባሾቹ በፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና በአዶንጎ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር በተለይም ፕሪንስ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ያቃረበ ነበር። በአስራ ስምንተኛው ደቂቃ ላይም ወልዋሎዎች በሳጥኑ ቀኝ ጠርዝ ያገኙትን ቅጣት ምት ብርሃኑ ቦጋለ በማስቆጠር በጨዋታው መሪ መሆን ችለዋል።

በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ፍሰት ያለው ጨዋታ ከማሳየት አልፈው በርካታ ሙከራዎች ማድረግ ያልቻሉት ሽረዎች ግብ ማስቆጠር ባይችሉም ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች መፍጥር ችለዋል።
በተለይም ሳሊፍ ፎፋና ብሩክ ተሾመ ያሻማት ኳስ ተጠቅሞ መቷት የግቡን ቋሚ ለትማ የተመለሰች ኳስና ሃብታሙ ሸዋለም ፣ ያስር ሙገርዋ እና ሳሊፍ ፎፋና ለሶስት ጥሩ ቅብብል አድርገው ሃብታሙ ሸዋለም ያመከናት ኳስ ይጠቀሳሉ። በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉት ቢጫ ለባሾችም በመጨረሻው ደቂቃ በሪችሞንድ አዶንጎ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ የወረደ የፉክክር መንፈስ እና የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በሙከራዎች ያልታጀበ እና ለደቂቃዎች የቆየ የደጋፊዎች ስርዓት አልበኝነት የታየበት ነበር። ጨዋታው እንደተጀመረ ጥሩ የማጥቃት መንፈስ የነበራቸው ሽረዎች በአርባ ስድስተኛው ደቂቃ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር፤ ሆኖም ሳሊፍ ፎፋና ቢስማርክ አፕያ ከመስመር ያሻማለትን ኳስ በነፃ አቋቋም ብቻው ሆኖ አምክኖታል። ከዚ ውጭም ሳሊፍ ፎፋና ከሙገርዋ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራም ይጠቀሳል።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ሲታይ የወረደ እንቅስቃሴ ያደረጉት ቢጫ ለባሾቹ ምንም እንኳ በርካታ ዕድሎች ባይፈጥሩም በሰመረ ሐፍተይ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል ፤ አማካዩ ከአዶንጎ የተላከለትን ኳስ ከግብ ጠባቂው በላይ በመላክ ነበር ሙከራው ያደረገው ሆኖም ረጅሙ ግብ ጠባቂ በቀላሉ አድኖታል።

በሰባኛው ደቂቃ በቁጥር ሃያ የሚጠጉ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባታቸው ጨዋታው ከአስር ለበለጡ ደቂቃዎች እንዲቋረጥ ያደረጉ ሲሆን ሜዳው በፀጥታ ሃይሎች ከተረጋጋ በኃላ ጨዋታው ካቆመበት መቀጠል ችሏል። ጨዋታው ከተቋረጠበት ከጀመረ በኃላ ስሑል ሽረዎች በቢስማርክ አፕያ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል አጥቂው ከቀኝ የሜዳው ክፍል እየገፋ ወደ ሳጥን ገብቶ በመምታት ነበር ግቡን ያስቆጠረው። ግብ ካስቆጠሩ በኃላም ብዙ ሳይቆዩ በርካታ ዕድሎች ያገኙት ሽረዎች በሰባ አምስተኛው ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት አምክነዋል ፤ ፍፁም ቅጣት ምቱ በሳሊፍ ፎፋና ከተመታ በኃላ ተቀይሮ በገባው በበረከት አማረ ነበር የተመለሰው። በሰባ ስምተኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው ሰይድ ሐሰን ደሳለኝ ደባሽ ከመአዝን ያሻማውን ኳስ በግንባር በማስቆጠር ቡድኑን አሸናፊ ማድረግ ችሏል።

ሽረዎች ድሉን ተከትሎ፤ መከላከያ እና ደቡብ ፖሊስ ነጥብ በመጣላቸው ለከርሞ በሊጉ መሰንበታቸውን አረጋግጠዋል።

ባህር ዳር ከተማ 0-1 ጅማ አባ ጅፋር

(ሚካኤል ለገሰ)

በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታ በሙከራዎች እየተሟሟቀ ሄዶ ብርቱ ፉክክር ታይቶበተል። ገና በጅማሮው ግብ ማስቆጠር የፈለጉ የሚመስሉት ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ሰንዝረዋለወ። በሁለተኛው ደቂቃ እንግዳዎቹ ጅማዎች ዲዲዬ ሌብሪ አሻምቶ ኦኪኪ አፎላቢ በግምባሩ በሞከረው ሙከራ እንዲሁም በስምንተኛው ደቂቃ ማማዱ ሲዴቤ አክርሮ ወደ ግብ በመታው ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች ደግሞ በሶስተኛው ደቂቃ ጃኮ አራፋት ከአስናቀ ሞገስ የተቀበለውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ በመታው ጥሩ አጋጣሚ ወደ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ሲያስመለክት የነበረው ጨዋታው በ20ኛው ደቂቃ ግብ ሊያስተናግድ እጅግ ተቃርቦ ነበር። በዚህ ደቂቃ አሌክስ አሙዙ ለሀሪሰን ሄሱ የሰጠውን የኋልዬሽ ኳስ ሀሪሰን በአግባቡ መቆጣጠር ተስኖት ኳሱ ወደ ግብነት ሊቀየር ተቀርቦ ነበረ። በአንፃራዊነት ተጭነው ሲጫወቱ የነበሩት ጅማዎች በ26ኛው ደቂቃ አምበሉ ደረጄ መንግስቱ ኳስ በእጅ በመንካቱ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ማማዱ ሲዴቤ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ አቻ ለመሆን ወደ ግብ ያመሩት ባህር ዳሮች በጀኮ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ሰንዝረው መክኖባቸዋል። እየተቀዛቀዘ የሄደው ጨዋታው በጭማሪ ደቂቃ መሱዑድ መሐመድ ከሞከረው ሙከራ ውጪ የጠራ የግብ እድል ሳይስተናገድበት አጋማሹ ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ተጠናክረው የቀረቡት ባህር ዳሮች ከተገኘ የመሪነት ካልተገኘ ደግሞ የአቻነት ግብ ለማግኝት ጥረዋል። በዚህም ዳንኤል በ49ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት በሞከረው እንዲሁም በ50ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ለጃኮ አመቻችቶ ባቀበለው ነገር ግን ጃኮ ባልተጠቀመበት አጋጣሚ የጅማን መረብ ፈትሸዋል። ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ የተነቃቁት ጅማዎች በ69ኛው ደቂቀቀ ጥሩ እድል ፈጥረው ነበረ። በዚህ ደቂቃ ግብ ያስቆጠረው ማማዱ ሲዴቤ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ያገናኘውን ኳስ ከመሃል ሜዳ በረጅሙ ተቀብሎ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ወንድሜነህ ደርሶ አምክኖበታል።ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ኦኪኪ አፎላቢ ከወንድሜነህ ደረጄ ጋር በፈጠረው ግጭት ከሜዳ በቀጥታ በቀይ ካርድ ተሰናብቷል። ከቀይ ካርዱ በኋላ የቁጥር ብልጫ ያገኙት የጣናው ሞገዶቹ ከቁጥጥራቸው እየወጣ የነበረውን ብልጫ መልሰው አግኝተዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም ግርማ ዲሳሳ እና ዳንኤል ኃይሉ በሞከሯቸው ኳሶች ወደ ግብ ቀርበው ነበረ። ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ ጭማሪ ሰዓት ሲታይ ተቀይሮ የገባው እንዳለ ደባልቄ ላይ ጥፋት ተሰርቶ ባህር ዳሮች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱን በጨዋታው ብዙ የግብ እድሎችን ሲያመክን የነበረው ጃኮ አራፋት መቶት ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄይ አድኖበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በተጋባዦቹ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም በፕሪምየር ሊጉ እስካሁን በሜዳው ሽንፈት ሳይገጥመው የቆየው ባህር ዳር የመጀመርያ ሽንፈት አስተናግዷል።

ድሬዳዋ ከተማ 0-1 ሀዋሳ ከተማ

በተመሳሳይ ሰዓት ከተደረጉት ጨዋታዎች ቀደም ብሎ የተጀመረው ጨዋታ ግብ በማስተናገድ ረገድም ቀዳሚ ነበር። ገና በመጀመርያው ደቂቃ እስራኤል እሸቱ እንግዶቹን ቀዳሚ አድርጎ ቀሪውን ረጅም ክፍለ ጊዜ በማስጠበቅ ሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥቦች ይዞ ሊወጣ ችሏል። ያለፉት ዓመታት ከሜዳ ውጪ ድል ማስመዝገብ ሲሳነው የነበረው ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ በአራት ጨዋታዎች ድል ማሳካት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡