ወልቂጤ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሷል

በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ መቀላቀል የቻለው ወልቂጤ ከተማ ደግአረገ ይግዛውን በአሰልጣኝነት ከሾመ በኋላ ወደ ዝውውር እንቅስቃሴ በመግባት ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሷል።

በረከት ጥጋቡ ክትፎዎቹን ለመቀላቀል የተስማማ የመጀመሪያው ተጫዋች ነው። በአማካይ ስፍራ የሚጫወተው የቀድሞው የአማራ ፓሊስ ተጫዋች በ2009 ክለቡን በመልቀቅ ለሁለት የውድድር ዓመታት በኢኮስኮ ቆይታን ያደረገ ሲሆን አሁን ደግሞ የቀድሞ አሰልጣኙን ተከትሎ ወደ ወልቂጤ አምርቷል።

ሌላኛው ክለቡን የተቀላቀለው ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ ነው። ከሱሉልታ ከተማ ወደ ወላይታ ድቻ አምርቶ መልካም የውድድር ዓመታትን ካሳለፈ በኃላ በ2010 ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራው ቁመተ መለሎው ተከላካይ ዘንድሮ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ የቋሚነት ዕድል አግኝቶ መጫወት ችሎ ነበር።

ወልቂጤ ሁለቱን ተጫዋቾች ከነገ በስቲያ በሚከፈተው የዝውውር መስኮት በይፋ እንደሚያስፈርም ሲጠበቅ በርካት ያሉ ተጨማሪ ተጫዋቾች ወደ ክለቡ ለማምጣት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡