የአሰልጣኞች ገጽ | አብርሀም ተክለሃይማኖት (ክፍል አንድ)

የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ በሚዳስሰው በዚህ ገፅ አሰልጣኝ አብርሀም ተክለሃይማኖትን ይዘንላችሁ ቀርበናል። ከ30 ዓመታት በላይ በአሰልጣኝነት ያሳለፉት እና በአሁኑ ወቅት የህፃናት ማሰልጠኛ ማዕከል በመመስረት የታዳጊዎች ስልጠና ላይ ከተሰማሩት አሰልጣኝ አብርሀም ጋር ዘለግ ያለ እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ቆይታ ያደረግን ሲሆን በዛሬው የክፍል አንድ መሰናዷችን አሰልጣኙ ካሳተሟቸው ሁለት መፅሀፍት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እያነሳን ቆይታ እናደርጋለን።


በ2005 ዓ.ም ” እግርኳሳችን ወዴት? “፣ በ2010 ዓ.ም ደግሞ ” እግርኳሳችን እና የኋሊት ርምጃው ” የተሰኙ ርዕሶች ያላቸው ሁለት መጽሃፍት አሳትመሃል፡፡ ሦስተኛውን መጽሃፍህም እንዲሁ ከአምስት ዓመት በኋላ እንጠብቅ?

★ አይመስለኝም፤ በቅርቡ ይሆናል ብዬ ነው የምጠብቀው፡፡ አሁን አምስት ዓመት የሚያስጠብቅ ጊዜ የለንም፤ እግርኳሱ ወደኋላ እየተመለሰ፣ የባሰ ላኋ-ቀር እየሆነ የሄደበት ሁኔታ ስላለ ኅብረተሰቡ በመጠኑም ቢሆን ግንዛቤ እንዲያገኝ፣ ከስሜት ወጥቶ ረጋ ብሎ ነገሮችን እንዲያይና አንብቦ እንዲረዳ በሚል ሃሳብ በቅርቡ ሦስተኛው መጽሃፍ ይወጣል፡፡ 

እግርኳሱ ብዙ ችግሮች አሉበት፤ ዋናውና ትልቁ ችግር ደግሞ አመራርን (Leadership) የሚመለከተው ነው፡፡  በዚህ ችግር ዙሪያ መፍትሄ ካልተገኘ ቴክኒኩ ቢሻሻልና ፋይናንሱ ቢያደድግ እንኳ ትርጉም የለውም፡፡ ጥሩ አመራር፣ ራዕይ ያለው አመራር፣ በስትራቴጂ የሚያስብ አመራር ካላገኘን እግርኳሳችን ወደ የትም መላወስ አይችልም፤ እድገት የሚባል ነገርም አይታሰብም፡፡ 

ከአንደኛው መጽሃፌ በተሻለ ሁለተኛውን መጽሃፍ ጽፌያለሁ፤ ሦስተኛው ደግሞ ከሁለተኛውም ትንሽ ከረር ያለ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ጉዳዩ ሃገራዊ ነው፤ የግለሰቦች አይደለም፤ እግርኳሳችን “ባለቤት ያጣ እግርኳስ” እየሆነ በሄደበት ሁኔታ እኛ ባለሙያዎች መጮህ አለብን፤ ምክንያቱም በሙያው የመጀመሪያ ተጠቃሚም፥ ተጎጂም እኛ ነን፡፡ እኛ ዝም ካልን አድርባይነት ይሆንብናል፤ እሱ ደግሞ የትም አያደርሰንም፡፡ እኛ ተጎድተን እግርኳሱ ቢድን የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንጻር መጽሃፉን ቀደም ብዬ ለመጻፍ እያሰብኩ ነው፡፡ 

በእርግጥ አልጀመርኩትም፤ ነገርግን ሐሳቦች አዘጋጅቻለሁ፤ የተለያዩ ጽሁፎች አሰባስቤያለሁ፤ ስለዚህ እነዚህን ግብዓቶች አስተካክዬ ለህዝቡ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በእርግጥ ብዙ አንባቢ የለም፤ እኛ ሃገር እግርኳስ በስሜት የመሆኑ ነገር ይበዛል፡፡ ስንመራም በስሜት፣ ስንደግፍም በስሜት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ያው እስኪሰክን ድረስ መጎዳት ይኖራል፤ በተላይ መጽሃፍ ስታሳትም ትጎዳለህ፡፡ ኃላፊነቱ የሃገር እስከሆነ ድረስ መስራት የግድ ነው፥ ስለዚህ እኔም ቀደም ብዬ ለመጻፍ ነው የማስበው፡፡

ከአስር ዓመት በፊት በኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ ላይ በአምደኝነት ስትጽፍ የሰበሰብካቸው ጥሩ ጥሩ መልዕክት የሚያስተላልፉ ጽሁፎች ለመጀመሪያ መጽሃፍህ ግብዓት ሆነውሃል፡፡ በቀጣይ ለምታሳትመው መጽሃፍስ በዚህ መልኩ ያሰብከው ነገር አለ?

★ በዚህ በኩል እንኳ ለወቅታዊው የእግርኳሳችን ችግሮች መፍትሄ ይሆናሉ ብዬ ከማስባቸው ሃሳቦች ለመነሳት ነው ያቀድኩት፡፡ አሁን የእግርኳሳችንን ውድቀት ህዝብም መንግስትም የተረዳው ይመስለኛል፡፡ ዘንድሮ በጣም ያማረርንበት ዓመት ነው፡፡ ያየነው እግርኳስ ሳይሆን ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ እርስበርስ መካሰስ፣… ነበር፡፡ ውድድሩ ሰላማዊ መድረክ መሆኑ ቀርቶ ጦርነት ሆኗል ማለት ይቻላል፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሰው ህይወት እስከ መጥፋት የተደረሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ <ሲሪየስ> የሆኑ ጉዳዮች የሚካተቱበት ይሆናል መጽሃፌ፡፡ 

ቀደም ተብሎ በተጻፉት በተለይ በመጀመሪያው መጽሃፍ ላይ ሽንፍንፍን አድርጌ ይበልጡን ወደ ሙያው የሚያደሉ ሐሳቦችን ነበር ያነሳሁት፤ በሁለተኛው ደግሞ በክለብ፣ በቴክኒክ ኮሚቴነት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያየኋቸውን አስተዳደራዊ ችግሮች- በኢንስትራክተርነት ደግሞ አስተማሪ ለመሆን ሰዎች በ<Merit> እና <Performance> ሳይሆን በቅርበት ወደ ውጪ የሚላኩበትን መንገድ በግልጽ አውጥቻለሁ፡፡ 

አሁን-አሁን የክለቦችን አካሄድ ሳይ የሚያስቀድሙት የምንወዳት የምንላትን ኢትዮጵያ ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ሆኗል፡፡ ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ እግርኳስ የመጨረሻ መታያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውጤታማ መሆንና አለመሆን ላይ ነው፡፡ አንድ መቶ ሚሊየን ህዝብ የሚደሰተው በብሄራዊ ቡድን ውጤታማነት እንጂ በአንድ ክለብ ዋንጫ መውሰድና አለመውሰድ አይደለም፡፡ ክለቦች ለዚህ ድል የሚያበቃቸውን ሥርዓት ካልፈጠሩ ብሄራዊ ቡድኑ ተጠቃሚ አይሆንም፤ እኔ እያየሁ ያለሁት ደግሞ ክለቦች የሚሰሩት ብሄራዊ ቡድኑን የሚያፈርስ ሥራ እንደሆነ ነው፡፡ ካወቁትና ከገባቸው የክለቦች ጥንካሬ የብሄራዊ ቡድን ጥንካሬ ነው፡፡ ክለቦች ላይ ጥሩ ሥራ ሳይሰራ ብሄራዊ ቡድን ላይ የሚመጣ ዕድገትም ለውጥም አይኖርም፡፡ እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ላይ ብዙ ለማተኮር እፈልጋለሁ፡፡

ትክክለኛ መረጃዎችን ተመርኩዘህ በግልጽ ኮስተር ያሉ ጉዳዮች (Serious Issues) ላይ የሰላ ትችት ማቅረብህ መጽሃፎችህ እንዳይነበቡ አድርጓል?

 ★ ምናልባት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገርግን በእግርኳሳችን ጉዳዮች በግልጽ መነጋገሩ ግድ ነው፡፡

መጽሃፎችህ የተለመዱና የህይወት ታሪክ ላይ የሚያተኩር ይዘት ያላቸው አለመሆናቸው የመነበብ ዕድላቸውን ቀንሶታል? በጠበቅኸው ልክስ ተነበውልሃል?

 ★ እንደጠበቅሁት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ስሜታችን ያመዝንብናል፤ የኢትዮጵያ እግርኳስም መስከን ይቀረዋል፤ ገና አልሰከነም፡፡ ደጋፊው፤ መሪው፣ መንግስትም ራሱ ሰክነው ችግሩን ያዩት አልመሰለኝም፡፡ መንግስት እግርኳሱ ላይ ብዙ ገንዘብ ያፈሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ ያሉትም ” እምቢ ካላችሁ እናቆመዋለን፡፡” ነው፡፡ እንደዚያ አይደለም፡፡ ችግሩ በደንብ መጠናት ነው ያለበት፡፡ ይህ ሁሉ ገንዘብ የሚፈስበትን እግርኳስ በማስቆም አይደለም መፍትሄ የሚመጣው፡፡ ይህ ሁሉ ህዝብ የሚደግፈው እግርኳስ በጥቂት ሰዎች ድክመት፣ ብልሹ አሰራር፣ የአመለካከት ልዩነት “እናቆመዋለን፡፡” ማለት አይቻልም፡፡ 

እንዲህ አይነት መጽሃፎች ተነባቢ እንዲሆኑና ችግሮችን በአግባቡ ለመረዳት ሰው መስከን አለበት፡፡ እኔ ‘ሰዉ ለምን አላነበበም?’ አልልም፡፡ እንስሳዋ ‘እኔ ከሞትኩ…’ እንዳለችው መሆን የለብንም፡፡ ‘የእኔ ክለብ ካላሸነፈ ሌላው ገደል ይግባ፡፡’ መባል የለበትም፡፡ እኔ ካልቻልኩ “ለሚቀጥለው ዓመት ተሻሽዬ እቀርባለሁ፡፡” ብዬ ማሰብ ነው ያለብኝ እንጂ ከዚያ ውጪ መሆን ተገቢ አይደለም፡፡ ወዴት እየሄድን እንዳለን እንኳ አናውቅም፤ ክለቦች ያን ሁሉ ሚሊየኖች ወጪ እያደረጉ እነርሱም መዳረሻቸውን አያውቁትም፡፡ መጨረሻው ምንድን ነው? ትርፉስ? ኢንደስትሪውስ? ይህ ዘርፍ ኢንደስትሪ ነው፤ ትርፋማነት ግድ ይላል፤ አለበለዚያ እድገት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ወዴት እየተኼደ እንዳለ የታወቀ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እንዲሁ ‘የአፍሪካ ዋንጫ እንሳተፋለን፤ የአለም ዋንጫ እንሳተፋለን፡፡’ ነው? ከዚያስ? ህዝቡ ምንድነው ጥቅሙ? ህዝብ’ኮ የሚያገኘው የመንፈስ እርካታ ነው፤ በሃገር የመኩራት ስሜት ነው፡፡ ይህን እንኳ መች ሰጠነው? የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዎች ቁጥር ሃያ አራት ደርሶም እኛ የለንበትም፡፡ እኛ’ኮ ለአፍሪካውያን ብዙ ነን፤ ብዙ ነገር የሰራች ሃገር ነው ያለችን፡፡ በመስራችነትና በጀማሪነት ከሆነ አዎ ከአራቱ አንዱ ነን፡፡ ካፍን በፕሬዚዳንትነት ያገለገለ ባለሙያ የነበረን ነን፡፡ አሁንስ? የለንም! ይህንን ውድቀታችን ረጋ ብሎ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ መደማመጥ መቻል አለብን፡፡ አሁን ሁሉም ተናጋሪ፣ ሁሉም ተንታኝ ሆኗል፡፡ 

እኔ የፃፍኩት “ይነበባል፡፡” ብዬ አልገምትም፡፡ ከተነበበ ይነበብ- እኔ ግን ከውስጤ ይውጣልኝ፡፡ ሁለቱንም መጽሃፎች ከማውጣቴ በፊት ኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ ላይ ስጽፍ ጽሁፎቼ አጫጭር ስለሆኑ አንባቢ ነበረኝ፡፡ አንብበው የሚደውሉልኝ፣ ሲያገኙንም የሚነግሩኝ ሰዎች ነበሩ፡፡ መጽሃፍ ሲሆን ግን ያ ሁሉ ቀረ፡፡ የማንበብ ልማዳችን በተለይም በእግርኳሱ አካባቢ ደካማ በመሆኑና የተጫዋቾች ህይወት ታሪክ ከማንበብ በዘለለ “የኢትዮጵያ እግርኳስ ችግር ምንድን ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ጥቂት ነው፡፡ ቢነበብም-ባይነበብም እኔ ውስጥ ያለው ነገር ተቀብሮ መቅረት የለበትም፡፡ አንድ ቀን ያስታውሱኝ ይሆናል ብዬም አስባለሁ፡፡

ምርምርና ጥናት አድራጊዎች፣ ምሁራኖች፣ ስፖርቱ ውስጥ የሚሰሩ የቴክኒክ ባለሙያዎች፣… በይበልጥ መጽሃፍትን አንብበው፣ ሔሰው፣ አስተያየት ሰጥተውና ችግሮችን ተረድተው የመፍትሄ አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መደበኛው ተመልካች ብዙውን ጊዜ ውጤቶችና አጫጭር ዜናዎች ላይ ያተኩራል፡፡ በተመልካቹ እና በእግርኳሱ ባለ ድርሻ አካላት መካከል የሚታየው ልዩነት እየጠበበ ይሆን?

★ በጣም እንጂ! መጽሃፉን አንብበው አስተያየታቸውን እንዲሰጡኝ ብዙ ሰዎችን ጋብዣለሁ፡፡ ‘ተሳስቼ ሊሆን እችላለሁ፤ ሰው ነኝ- የመሰለኝን ጽፌያለሁ፡፡ ነገር ግን አንድም ምሁር ተብዬ ” እንዲ ቢሆን…” ብሎ ያለኝ የለም፡፡ ከዚህ ተነስቼ እኮ ነው ‘ ቢነበብ-ባይነበብ ከእኔ ብቻ ይውጣልኝ፡፡’ ብዬ የምናገረው፡፡ በቅርቡ አንድ የክለብ ሊቀመንበር (አቶ አብነት ገ/መስቀል) መጽሃፌን አንብበው ስፖርትን በቅርበት ለሚከታተሉት የባህልና ስፖርት ምክትል ሚኒስትሩ አቶ ሃብታሙ መጽሃፌን ከሰጧቸው በኋላ  ” አቶ አብርሃም ይህን መጽሃፍ ጽፏል፤ እስቲ አነጋግረው፡፡” ተባብለው ይመስለኛል ምክትል ሚኒስትሩ ደወሉልኝና ተገናኘን፡፡ “እንዴት ጻፍከው?” ጠየቁኝ፤ አብራራሁላቸው፤ ሁለተኛ መጽሃፌን ስሰጣቸውም በጣም ገረማቸው፡፡ ” ስፖርትን እየመሩማ የስፖርት መጻህፍትን ማንበብ አለብዎት፡፡” አልኳቸው፡፡ እኔ የእርሳቸው ምላሽ አስደንቆኛል፡፡ ከብዙ ሰዎች ያላገኘሁትን አስተያየት ከእርሳቸው አግኝቻለሁ፡፡ ” ይህማ መማሪያ ሰነድ ነው፡፡ ለጥናት ይረዳል፡፡” ብለውኛል፡፡

በነገራችን ላይ ምሁሩ ራሱ ተራ ተመልካች ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ” ችግራችን ይሄ ነው፤ ስለዚህ በዚህ መንገድ እንሂድ፡፡” ማለትም አልቻለም፡፡ ባለሙያው ገንዘብ የማግኘት ሩጫ ላይ ነው፡፡ ነገርግን ገንዘቡ ነገ እንደሚጠፋ ማወቅ አለባቸው፤ እግርኳሱ እድገት የሚያሳይ ካልሆነ’ኮ መጨረሻው መቆም ነው የሚሆነው፡፡ መንግስት በግልጽ ተናግሯል፤ ” ለውጥ ከሌለው አቆመዋለሁ!” እስከማለት ተተደርሷል፡፡ ሙሉ በሙሉ ባይቆም እንኳ እየቀነሰ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ በጥያቄው በጣም እስማማለሁ፤ እኔ እንዲያውም ‘በሙያው ዘርፍ ያልተሰማራው ተራው ሰው ሳይሻል አይቀርም፡፡’ ባይ ነኝ፡፡ በስፖርቱ አካባቢ ያሉ ምሁራን በየስብሰባው ‘ጥናት አቀረብን!’ ይላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በጥልቀት የሚያዩት አይመስለኝም፡፡ በየጊዜው ብዙ ጥናቶች ይሰራሉ፤ በቅርቡም በሚኒስቴር መስሪያ ቤትና በስፖርት ኮሚሽኑ አማካኝነት አንድ-ሁለት ጥናቶች ተሰርተዋል፡፡ በአቶ ኢሳያስ የሚመራው አዲሱ የፌዴሬሽን አስተዳደርም  ብዙ ወጪ የተደረገበት ጥናት አሰርቷል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ጥናቶች መጨረሻ ምንድን ነው? ተግባረዊ የሆነ ነገር እኮ የለም፡፡ ጭራሽ ወደ ባሰ አዘቅት እየገባን ነው፡፡ ሙያው ውስጥ የሌለው እግርኳስ አፍቃሪ ከምሁሩ አንጻር የተሻለ ግንዛቤ፣ አስተሳሰብና አመለካከት አለው፡፡ ‘የሃገሪቱን ስፖርት እንዴት እናሳድግ?’ በሚለው ጉዳይ ምሁሩ ግራ የተጋባ ይመስለኛል፤ ለሙያተኛው እድል የመስጠትም ችግር ይስተዋላል፡፡ 

ምሁራኑ “እኔ የተማርኩ ነኝ፤ ከእኔ በላይ የለም፡፡” ይላሉ፡፡ እኛ ሙያተኞቹ ደግሞ “እግርኳሱ ውስጥ ኖረናል፤ እዚያ ከባቢ ውስጥ ብዙ ስለቆየን ችግሩን በቀላሉ እንረዳለን፤ ምንጩንም አብጠርጥረን እናውቀዋለን፤ ከሌላው ሰው አንጻር መፍትሄውን ለማበጀትም እኛ እንቀርባለን፡፡” እንላለን፡፡ እኛ ኳስ ሜዳ ነን፥ ምሁራኑ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ናቸው፡፡ እና ታዲያ ችግሩን ያለ ጥናትና ምርምር በቀላሉ ተረድቶ መፍትሄ መስጠት የሚችለው አካል የትኛው ነው? እኛ ነን፡፡ የእኔ መጽሃፍ እነዚያ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡ ከብሄራዊ ሊግ እስከ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በዘለቀው የረጅም ዓመት ተመክሮዬ ያጋጠሙኝን ችግሮች ጠንቅቄ አውቃቸዋለሁ፡፡ በኢንስትራክተርነት በአፍሪካ ብዙ ሃገራት ዞሬ አስተምሬያለሁ፤ በዓለምአቀፍ ደረጃም በርካታ ሥልጠናዎችን ተካፍያለሁ፤ ነገርግን ዲግሪ የለኝም፡፡ ዲግሪ ስለሌለኝ ግን አላውቅም ማለት አይደለም፡፡ ይሄ እስካሁንም መታረቅ ያልቻለ ጉድለታችን ነው፡፡ 

ሙያተኛው ሰፊና የካበተ ልምድ አለው፤ ይህንን ባለልምድ የመፍትሄ አካል ማድረግ የተሻለ ነው፡፡ ምሁሩ ያጠናው ስፖርት ሳይንስ ሊሆን ይችላል፤ የእግርኳሱን ጓዳ ጎድጓዳ ሳያውቅ  ነባራዊውን የተግባር ተመክሮ ሳያካትት ‘በጥናትና ምርምር ብቻ ለችግሩ ዕልባት አገኝለታለሁ፡፡’ ካለ ተሳስቷል፡፡ እኔ ደግሞ ውስጡ ስዋኝ ኖሬያለሁ፤ “ዋናዬ ትክክል ነው፤ ትክክል አይደለም፡፡” እሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ችግሩ ውስጥ ዋኝቻለሁ፤ ምሁሩ ደግሞ ከውጭ ሆኖ ተመልክቶታል፡፡ ‘የምሁራኑ ሚና ከተመልካች ያልተናነሰ ነው፡፡’ ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡ ከብዙ ምሁራኖች ጋር እነጋገራለሁ፤ ‘ግቡ፤ ደፍራችሁ ተናገሩ፡፡’ እላቸዋለሁ፡፡ ጥናቶቻቸው በአብዛኛው የ<ቢሆን> ይዘት አለው፡፡ “…እንዲህ ቢሆን፤ … እንዲህ ቢሆን፤ … እንዲህ ቢሆን” ብቻ ነው፡፡ 

በመጀመሪያው መጽሃፍህ የእግርኳስ ደረጃችን ላይ የሚስተዋለውን የአመለካከት ችግር በተመለከተ ” ትልቁ ድክመታችን ምንም ሳይኖረን ትልቅነት እንዳለን አድርገን ማሰባችን ነው፡፡” የሚል አስተያየትህን አስፍረሃል፡፡ እውነት በእግርኳሳችን ይህን ያህል የመመጻደቅ ሁኔታዎች ይታያሉ?

 ★ ትልቁ ችግራችን በሌለና በተፈበረከ ታሪክ ሳንሆን “ነን!” እያልን መኖራችን ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ውጤታማ ሆነን ሊሆን ይችላል፤ እንደ ቡድን፣ እንደ ሃገር ግን ስኬታማ አልነበርንም፡፡ አንድ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አገኘን፤ ከዚያ በኋላ ግን የለንም፡፡ ከትንንሽ ሃገራት ጋር እንኳ ማጣሪያዎችን ለማለፍ የተቸገርንባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ይህን ስል እኔንም የዚያ ታሪክ ተጠቃሽ አካል አድርጌ እንጂ ” እነ እገሌ፥ እነ እገሌ” ለማለት አይደለም፡፡ እውነታው ግን መነገር አለበት፡፡ እስቲ በእግርኳስ ትልቅ ያደረገን ምንድን ነው? የአቶ ይድነቃቸው የካፍ ሊቀመንበርነት ለእርሳቸውም ሆነ ለሃገር ትልቅ ስኬት ነበር፡፡ ጥሩ ስም ማስጠሪያም ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአለም የጤና ድርጅት መሪ በመሆናቸው ሁላችንም እንኮራለን፤ ነገርግን በጤና ሃገሪቱ ያመጣችው ለውጥ ታች ነው፡፡ እግርኳሳችንም እንደዚሁ ሞቶ እያለ ‘ትልቅ ነበርን፡፡’ ብዬ ለመናገር አልደፍርም፡፡ አንድ ጊዜ ዋንጫ ወስደናል፥ አዎ! በምስራቅ አፍሪካ እንኳ የበላይነታችንን ሳናሳይ ‘የአፍሪካ የበላይ ነበርን፡፡’ ብሎ ለመናገር መሞከር ራስን ማታለል ነው፡፡

“ኳስ ድሮ ቀረ!” የሚለው የቁጭት ንግግር ታዲያ ከየት የመጣ ነው?

 ★ ይህ አባባል ዝምብሎ ራስን ከፍ ለማድረግ የሚሰጥ አስተያየት ነው፡፡ ግለሰቦች ራሳቸውን አግዝፈው ማየት ሲፈልጉ “… ኳስ በእኛ ጊዜ ቀረ፡፡” ይላሉ፡፡ ይህንን ለማለት ያበቃቸው ውጤታማነት የትኛው ነው? የአለም ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳትፈን አናውቅም፤ የአፍሪካ ዋንጫም ላይ ጥሩ የተንቀሳቀስነው ያኔ ገና በድሮው ፎርማት፣ ሃገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ሳይወጡ በነበረበት ዘመን ነው፡፡ አሁን ምንም የለንም፤ ‘አለም በሰለጠነበት ሰዓት እኛ የታለን?’ ነው ጥያቄው፡፡ ትናንት በቃ ትናንት ነው፥ ማየት ያለብን የዛሬውን ነው፡፡ በታሪክ ተቸክሎ መኖር አይጠቅመንም፡፡ ትናንት የተሻለ ነበርን፤ አቶ ይድነቃቸውን ያህል ታላቅ ባለሙያ ነበሩን፤ ዛሬስ? የትናንት  ታሪካችን ለዛሬ ካልጠቀመን እድገት እንዴት ይመጣል? እኔ ‘አልጠቀመንም፡፡’ አላልኩም፤ ደ’ሞ በሌላ እንዳይተረጎም፡፡ ሃቅ እንነጋገር፤ ስለ እውነት እናውራ፤ ችግራችንን ይፋ እናውጣ፡፡ በእግርኳስ ኋላ ቀርተናል-ትክክል፡፡ ስለዚህ ‘እንዴት ነው ትልቅ የምንሆነው?’ ሌሎች ሃገራት ከሰሩት በላይ መስራት አንችልም? ይቻላል፡፡ እውነትን አፍረጥርጦ ማውጣት እንደ ውድቀት የማየት በሽታ አለብን፡፡ ይህንን ደዌ ለማዳን መታገል ይኖርብናል፡፡ ውጤት አልባ ትልቅነት አለ እንዴ? ውጤት’ኮ ነው መመዘኛችን፡፡ ደረጃችንን እንይ እስቲ- ከ150 በታች እኮ ነን፡፡ የሌለንን ታላቅነት እየፈጠርን ራሳችንን ማሞኘት አይኖርብንም፡፡

በሃገራችን ክለቦች በተለይ የወጣት ቡድን አሰልጣኞችን ሲመድቡ፣ ሲመርጡና ሲቀጥሩ “… ስላገለገለ እንርዳው፡፡” ከሚል መነሻ እንደሆነ <እግርኳሳችን ወዴት?> መጽሃፍህ ላይ አንስተሃል፡፡ ቅጥሩን የሚከውኑ ኃላፊዎች ከማገልገል ያለፈ መስፈርት የሚኖራቸው በምን መልኩ ነው?

 ★ ወቅታዊ ብቃት ላይ ማተኮር የግድ ይላል፤ ሥልጠና ላይ የ’እንርዳው’ ሹመት ሊኖር አይገባም፡፡ እግርኳስ ቅጽበታዊ ውጤት የሚታይበት ሥራ ነው፡፡ የበጎ-አድራጎት ቦታ አይደለም፤ ስለዚህ በውድድር ልቀህ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ጥሩ አስተሳሰብ ያየዘ፣ የበለጠ ዝግጅት ያደረገ፣ የተሻለ የማሸነፍ ሥነ ልቦናዊ አቅም ያለው፣….. ወጣት አሰልጣኝ መርጦ ቦታውን ለእርሱ መስጠት-በቃ፡፡ ሙያዊ ብቃትና ወቅታዊ ውጤት የሹመት መሥፈርቶች ይሆናሉ፡፡ እግርኳስ በ’ነበረ!’ አይሰራበትም፤ ትናንት ዋንጫ አስገኝተህ ዛሬ የምትባረርበት የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ ለቀደመ ግልጋሎት ወይም አበርክቶ በሌሎች መንገዶች መተሳሰብ ይቻላል፡፡

ተጫዋቾቻችን የእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመናቸውን ሲያገባድዱ ራሳቸውን ለታዳጊና ተተኪ ቡድኖች (B, C እና ከዚያ በታች) አሰልጣኝነት ብቁ አድርጎ የመገኘት ዝግጁነት ስለሚጎድላቸው ይሆን “የአገልግሎት ሹመት” የተለመደው?

★ የአመራር ጥራት ችግር ነው፡፡ የሃገሪቱ እግርኳስ ራስ ምታት ክለቦች ናቸው፡፡ እነርሱ ጥርት ያለ ሥራ ከሰሩ ፌዴሬሽኑ የማይሰራበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ የክለቦች የእግርኳስ ሥራ ምን ይመስላል? የቀድሞ ውለታቸው ብቻ ታስቦ ዝግጁና ብቁ ላልሆኑ አሰልጣኞች የ<C> እና የ<B> ቡድኖችን መስጠት አስነዋሪም-አሳፋሪም ውሳኔ ነው፡፡ እግርኳሱን እያቀጨጩ ካሉት ተግባራት መካከልም አንደኛው ነው፡፡ ተተኪዎችን ማፍራት ከፍተኛ እውቀት ይጠይቃል፤ ለታዳጊዎቹ እግርኳስን ከማጫወት አልፎ ቀጣይ ህይወታቸውን የመቅረጽ ከባድ ኃላፊነት አለበት፡፡ <ፕሮፌሽናል> የመሆን ህልም ካላቸው ያን ህልም የሚያሳኩበትን መንገድ ማሳየት፣ የ<ፕሮፌሽናሊዝም>ን ጽንሰ-ሐሳብ ፈትፍቶ ማስረዳት፣ የነባራዊውን ህፃናት የአስተዳደግ ሁኔታ ማጤን፣ ሌሎች በርካታ ነገሮች ይጠበቁበታል፡፡ ኳስ ስለተጫወተ ብቻ ‘አሰልጣኝ ላድርገው!’ ካልክ ሰልጣኞቹን ትጎዳለህ፡፡ ልክ ችግኝ ተክለህ ግን ደግሞ ኮትኩተህ ያለማሳደግ ሒደት እንደማለት ይሆናል፡፡ ችግኙን ካልተንከባከብከው ጠማማ ሆኖ ያድጋል፤ አልያም ደርቆ ይቀራል፡፡ እግርኳስም እንደዚያ ነው፡፡ በዓለም እግርኳስ በ<Youth Development> ላይ የሚሰሩት ትልቅ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አሰልጣኞች ብዙ ዓመት ከወጣቶች ጋር ያሳለፉ ናቸው፡፡ በ’ነበረ’ ላይ ተመስርተህ ‘ቴክኒሺያን ነበር፡፡’፤ ‘አሪፍ ተጫዋች ነበር፡፡’፤ ‘ረጅም ዓመት አገልግሏል፡፡’፤ ….. እነዚህን መስፈርቶች ብቻ ይዘን የምንሰራበት ሁኔታ አያዋጣንም፡፡ ክለቦች ከእንዲህ ዓይነቱ አሰራር ሥርዓት መራቅ አለባቸው፤ የቡድን አመራር፣ የአሰልጣኞች አመዳደብ፣ የአሰለጣጠን ሒደቶች፣… በአግባቡ ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል፡፡

ብዙውን ጊዜ የእግርኳሱን አስተዳደራዊ ችግሮች በሰፊው ታነሳለህ፡፡ የመፍትሄው አካል ሆኖ የመሥራቱ ሃሳብስ የለህም? 

★ እሱን አስባለሁ፤ ክለቦች ውስጥ ገብቼ በዕለት ተዕለት የእግርኳስ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቼ መሳተፍ አልፈልግም፤ ነገርግን ከ<Manager>ነት ይልቅ <Technical Advisor> መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ትልቁ ምኞቴ አካዳሚውን ማሳደግ ነው፡፡ የትግራይ ክልል ለዚህ የአካዳሚ ሥራ የሚውል መሬት ሰጥቶኝ ለመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፖዛልም አቅርቤ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እገኛለሁ፡፡ በዚህ ዘርፍ በመቐለ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎችም በሰፊው መሳተፍ እፈልጋለሁ፡፡ “አንድ ትልቅ ክህሎት የሚወጣው ከብዙ ሚሊዮን ወጣቶች ነው፡፡” የሚል ዕምነት አለኝ፤ ስለዚህ በ<Youth Development> ላይ እንጂ በክለብና በብሄራዊ ቡድን የሙሉ ጊዜ ሥራ ብዙም አይታየኝም፡፡ አሁን መሰረት የመጣል ሥራ ላይ አተኩሬያለሁ፡፡

በየዕለቱ በሚሰሩ የእግርኳስ ሥራዎች ራስህን ካለመወጠርህ አኳያ ከቀድሞው በተሻለ ሰፋ ያለ ጊዜ አለህ ተብሎ ይታሰባልና-መጽሃፍ ከመጻፍ ባለፈ ሃሳቦችህ ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆኑ በሚዲያዎች ላይ ከመሳተፍ አንጻርስ ያቀድከው ነገር አለ? 

★ ይሄ ትልቁ ነጥብ ነው፡፡ ከእንደእናንተ አይነቱ አካል ጋር መሥራትን የሚጠይቅ ይመሥለኛል፡፡ በቅርቡ አንድ ጋዜጣ በየሳምንቱ ጽሁፎችን እንዳቀርብለት ጋብዞኝ ነበር- አልተመቸኝም-ተውኩት፡፡ ትግራይ ውስጥ እግርኳስ እጅጉን እያበበ ይገኛል፡፡ በዚህ ሒደት ወዴት እንደሚያመራ አይታወቅም፤ ስለዚህ እዚያ አካባቢ የመሥራት ትልቅ እቅድ አለኝ፡፡ እንዲያውም መቐለ ላይ በቴሌቪዥን ለመሥራት አስቤ ነበር-ከማሰብ አልፌም በተግባር የሞከርኩበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ በደንብ ሳስበው የሚጠበኝ መሰለኝ፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ እናንተ ገለልተኛ እንደሆናችሁ አውቃለሁ፤ የማንም ደጋፊም አይደላችሁም፡፡ ብዙ ጋዜጠኞች እኛን አይፈልጉም፤ ይልቅም ራሳቸው እኛን መሆን ይፈልጋሉ፡፡ የባለሙያ ጥቅም በሚገባ አልታወቀም፤ ስለዚህ እድል አታገኝም፡፡ ባለሙያውም ነገ የሚያጠቃው አካል እንዳለ ስለሚያውቅ ደፍሮ አይወጣም፡፡ እኔ ግን ከዚህ በኋላ ነጻ ነኝ፤ ማንም አያጠቃኝም፤ ያን ለማድረግ ቢፈልግም በምንም አያገኘኝም፡፡ ካገኘኝም በህግ ፊትለፊት መነጋገር እችላለሁ፤ ክለብም ውስጥ የለሁም፤ ክለቤ አይጎዳም፡፡ ድሮ ፌዴሬሽን ከተናገርክ በዳኛ ክለብህ ይጠቃል፤ ውጤትህም ይቀለበሳል፡፡ ከዚያ ፍራቻ አንጻር ብዙዎች አይናገሩም ነበር፡፡ እኔ ያ አያስፈራኝም፤ የምፈራው የኢትዮጵያ እግርኳስ ከዚህም በባሰ እንዳይወድቅ ነው፡፡ እንዲያውም አንድ ወዳጄ “የሆነ ድረገጽ አለና-ለምን እዚያ ላይ አትጽፍም?” ብሎኛል፡፡ ‘አላውቀውም፡፡’ አልኩት፡፡ ከእናንተ ጋር ግን ከዚህ በኋላ እንፈላለጋለን፡፡ የፈለግሁትን መጻፍ እችላለሁ፤ ችግር የለም፡፡ በነገራችን ላይ በየቀኑ የመጻፍ ልማድ አለኝ፡፡ ለምን አስር መስመር ብቻ አትሆንም እጽፋታለሁ፤ ከዚያ ደግሞ አንድ ቀን ተመልሼባት እንደገና አስፍቼ እጽፋለሁ፡፡ በዚያ መልኩ በየጊዜው እየከተብኩ የማስቀምጣቸው ጽሁፎች አሉ፡፡ ሐሳቤ ይህ ስለሆነ እንስማማለን፡፡

ይቀጥላል…