ደቡብ ፖሊስ ስድስት ወጣት ተጫዋቾችን አስፈረመ

አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረው ደቡብ ፖሊስ በዛሬው ዕለት ከአሰልጣኙ ጋር ከዚህ ቀደም የሰሩ ወጣት ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

ዳግም ተፈራ ለደቡብ ፖሊስ ፊርማውን ያኖረ ተጫዋች ነው፡፡ ይህ ግብ ጠባቂ ከሀዋሳ ከተማ የታዳጊ ቡድን የተገኘ ሲሆን በዋናው ቡድን ውስጥም መጫወት ችሏል፡፡ በአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተካቶ የተጫወተው ይህ ተጫዋች በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በዲላ ከተማ ካሳለፈ በኋላ ከቀድሞው አሰልጣኙ ተመስገን ዳና ጋር በደቡብ ፖሊስ አብሮ ለመስራት ከስምምነት ደርሷል፡፡

መስፍን ቡዜ ሁለተኛው ለቢጫ ለባሾቹ ለመጫወት ፊርማውን ያኖረ ግብ ጠባቂ ነው። እንደ ዳግም ሁሉ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሚመራው የሀዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን መጫወት የቻለው ይህ ግብ ጠባቂ ከቀድሞው አሰልጣኙ ጋር በድጋሚ ተገናኝቷል፡፡

ሦስተኛ ፈራሚው ሚካኤል ልዑልሰገድ ነው፡፡ በተመሳሳይ በሀዋሳ ከተማ የወጣት ቡድን ኳስን በመጫወት የጀመረው ይህ ፈጣን የቀኝ ተከላካይ እና የመስመር አጥቂ ተጫዋች በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የአሰልጣኝነት ዘመን ወደ ሀዋሳ ዋናው ቡድን ቢያድግም በውሰት ያለፈውን አንድ ዓመት በስልጤ ወራቤ እና ሀዲያ ሆሳዕና ካሳለፈ በኃላ ከቀድሞው አሰልጣኙ ጋር በደቡብ ፖሊስ ተገናኝቷል፡፡

ያሬድ መሐመድ ሌላው አዲሱ የደቡብ ፖሊስ ተጫዋች ሆኗል፡፡ በቀኝ መስመር የአጥቂ ስፍራ ላይ የሚጫወተው ይህ ተጫዋች በተመሳሳይ በሀዋሳ ታዳጊ ቡድን ውስጥ ስኬታማ ጊዜን ካሳለፈ በኃላ ዓምና ወደ ደደቢት አምርቶ ተጫውቶ ዳግም ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር አብሮ የመስራት ዕድልን አግኝቷል፡፡

የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ታዲዮስ አንበሴ ፖሊስን ከተቀላቀሉት ውስጥ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሱት ተጫዋቾች ሁሉ በሀዋሳ ተስፋ እና ዋናው ቡድን ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ በዲላ ከተማ እና ጅማ አባቡና ተጫውቷል፡፡

የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሆነው የኋላሸት ሰለሞን ደቡብ ፖሊስ የተቀላቀለ ስድስተኛው ተጫዋች ነው፡፡ ከዲላ ከተማ ፕሮጀክት የተገኘው የኋላሸት ዓምና በኢኮስኮ ቆይታ አድርጓል።

በቀጣይ ቀናት በርከት ያሉ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም የሚጠበቀው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ዘንድሮ በሊጉ በወጣቶች የተደራጀ ቡድን ለመገንባት እንደሚሰራ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ