ኢትዮጵያውያን በውጪ | እዮብ ዛምባታሮ ወደ ሴሪአው ክለብ ተመልሷል

ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በውሰት ወደ ሴሪ ሲ ክለብ ፓዶቫ አምርቶ ከቡድኑ ጋር ቆይታ ያደረገው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የመስመር ተከላካይ ወደ እናት ክለቡ አታላንታ ተመልሷል።

በግራ እና በቀኝ የመስመር ተከላካይ ቦታዎች መጫወት የሚችለው ይህ የ21 ዓመት ተጫዋች ከፖዶቫ መልስ ወደ ኔራዙሪዎቹ ቢቀላቀልም በቡድኑ ዝርዝር ሳይካካተት ቀርቷል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በጣልያን ሁለተኛው እና ሦስተኛ የሊግ እርኮኖች የተጫወተው ይህ ተጫዋች በአታላንታ ተስፋ ከሚጣልባቸው ታዳጊዎች አንዱ ነው።

በእ.ኤ.አ 1998 በአዲስ አበባ የተወለደው እዮብ በዘጠኝ ዓመቱ ለዛምባታሮ ቤተሰብ በጉዲፈቻ ተሰጥቶ ወደ ጣልያን ካመራ በኃላ በኦራቶርዮ እና ፍርቶሶ ታዳጊ ቡድኖች ተጫውቶ ነው አታላንታ አካዳሚን የተቀላቀለው። በፓዶቫ የመጀመርያ ዓመቱ ቡድኑ የሴሪ ሲ ምድብ ‘B’ አሸናፊ ሆኖ ወደ ሴሪ ቢ ሲያድግ የቡድኑ አባል የነበረው እዮብ በ2018 ከቡድኑ ጋር የሴሪ ሲ ሱፐርኮፓ አሸናፊ ሆናል።

በዛምባታሮ ቤተሰብ ከእዮብ በተጨማሪ በአታላንታ ታዳጊ ቡድን ግብጠባቂው አክሊሉ ዛምባታሮ ይገኛል። ከዚህ በፊት በሴሪ ዲ ክለቦች ኢንቬርኖ እና ዩኤስዲ 1913 ሰርጂኖ ካልችዮ የተጫወተው የ19 ዓመቱ ግብ ጠባቂ በዚ የውድድር ዘመን ከውሰት መልስ ወደ አታላንታ ታዳጊ ቡድን ተቀላቅሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ