ሴካፋ ሴቶች ዋንጫ | ከምድብ ሁለት ታንዛኒያ ማለፏን ስታረጋግጥ ደቡብ ሱዳን ድል ቀንቷታል

የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የምድብ ሁለት መርሀግብሮች ዛሬ ሲከወኑ አስተናጋጇ ታንዛኒያ ቡሩንዲን 4ለ0 በማሸነፍ ማለፏን ስታረጋግጥ ደቡብ ሱዳን የመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ድል አስመዝግባለች፡፡

8:00 ላይ ኢትዮጵያዊያኑ ዳኞች ፀሀይነሽ አበበ በዋና ዳኝነት፣ ወጋየው ዘውዴ እና ወይንሸት አበራ ደግሞ በረዳት ዳኝነት በመሩት የደቡብ ሱዳን እና ዛንዚባር ጨዋታ ደቡብ ሱዳን 5ለ0 በማሸነፍ የመጀመሪያውን የኢንተርናሽናል ነጥቧን አስመዝባለች፡፡ በመክፈቻው ሽንፈት ገጥሟት የነበረችው ደቡብ ሱዳን ፍፁም የጨዋታ ብልጫን በማሳየት ነው ተጋጣሚዋን ያሸነፈችው።

ለኬንያው ማኮላንደርስ ክለብ የምትጫወተው ፈጣኗ አጥቂ ኤሚ ላሱ በ24ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥራ ሀገሯን መሪ ስታደርግ ተከላካዩዋ ሱዚ አሪአምባ በጨዋታው ተደጋጋሚ ስህተት ስትፈፅም የነበረችው የዛንዚባር ግብ ጠባቂ ሀጅራ አብደላን መዘናጋት ተመልክታ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥራ 2-0 ለእረፍት ወተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ አሁንም በዛንዚባር የግብ ክልል ተደጋጋሚ ጫናዎችን ሲያሳድሩ የነበሩት ደቡብ ሱዳኖች 62ኛው ደቂቃ ላይ ተጭነው ሲጫወቱ የዛንዚባሯ የመሀል ተከላካይ ማዋጁማ አብደላ በራሷ ግብ ላይ አስቆጥራለች፡፡ 77ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ማንዮል ሪክ ወደ 4ለ0 ያመሩበት ተጨማሪ ግብ ስታስቆጥር የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረችው ኤሚ ላሱ ማሳረጊያውን አክላ ጨዋታው በደቡብ ሱዳን 5-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

10:00 ላይ በዚሁ ምድብ ታንዛኒያ ቡሩንዲን ገጥማ 4ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ አማካዩዋ ዶኒሳ ሚንጃ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፋ ቡድኗን መሪ በማድረግ ለእረፍት ያመራች ሲሆን ከእረፍት መልስም ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡ በሁለተኛው አርባ አምስት አሻ ሙሳ እና ማዋሀሚስ ኦማሪ አክለው ጨዋታው 4ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በዚህም መሠረት ታንዛኒያ ስድስት ነጥቦች እና አስራሶስት ንፁህ ግቦችን በመያዝ ማለፏን ስታረጋግጥ ቡሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን እኩል 3 ነጥቦችን የያዙ ሲሆን ዛንዚባር አስር የግብ ዕዳን በመያዝ ምንም ነጥብ አላስመዘገበችም ፡፡

ሁለተኛ የምድብ ሀ ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ ኬንያ ከ ጅቡቲ፣ ዩጋንዳ ከ ኢትዮጵያ ጋር ይገኛሉ፡፡

የደረጃ ሰንጠረዥ

# ምድብ 1 ተጫ  ልዩ ነጥብ 
1 ዩጋንዳ 1 +13 3
2 ኬንያ 1 +2 3
3 ኢትዮጵያ 1 -2 0
4 ጅቡቲ 1 -13 0
# ምድብ 2 ተጫ  ልዩ ነጥብ 
1 ታንዛንያ 2 +13 6
2 ቡሩንዲ 2 +1 3
3 ደቡብ ሱዳን 2 -4 3
4 ዛንዚባር 2 -10 0

*የዩጋንዳዋ አጥቂ ናሉኬንግ ጁሌት በ5 ጎሎች የከፍተኛ ግብ አግቢነት ደረጃውን ትመራለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ