አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡድኑ እየተሻሻለ ስለመሆኑ ይናገራል

ኢትዮጵያ ቡናን በክረምቱ የተረከበው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከዛሬው የጅማ አባጅፋር ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሰጠው ድህረ ጨዋታ አስተያየት ስለቡድኑ መሻሻልና ተያያዥ ጉዳዮች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

ስለ ቡድኑ መሻሻል

“አዎ በእኔ እምነት ቡድኑ በጥሩ መልኩ እየሄደ ነው። በእንደዚህ አይነት ጫና ውስጥ ያለውን ነገር ጠብቀው መሄዳቸው በራሱ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ሁላችንም እንደምናውቀው ራሳቸውን ገልፀው ለመጫወት ፈሪዎች ናቸው፤ ተጫዋቹ በቀላሉ በሚድያ በተመልካች ብሎም በሁሉም የሚደበደብ ነው፤ ስህተቶቻቸውን አንቀበላቸውም። ስለዚህ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ጫናውን ተቋቋመው ለመጫወት እያደረጉ ያሉት ጥረት ጥሩ እየሄድን ስለመሆናቸን የሚገልፅ ነው።”

ስለ ቡድኑ ክፍተቶች

“በዛሬው ጨዋታ እንደድክመት ማቅረብ ከተቻለ የተሳቱት ኳሶች ናቸው። የተጋጣሚያችን ቡድን ተጫዋቾች አብዛኛዎቹ ወደ ራሳቸው ሜዳ ተጠግተው ሲከላከሉ ነበር። በዚያ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም የግብ እድሎችን ግን መፍጠር ተችሏል።”

ቡድኑ በሂደት ስላሳየው መሻሻል

“እስከ አሁን እየሄድን ያለንበት መንገድ ጥሩ ነው ፤ የምንገጥማቸው ቡድኖች በሙሉ ከሌላው ቡድን ጋር እንደሚጫወቱት አይደለም ከእኛ ጋር ሲሆን የሚጫወቱት። ለዚህም ነው ልጆቹ በጫና ውስጥ ነው እየተጫወቱ የሚገኙት። በጫና ውስጥ ሆነንም እያደረግናቸው ባለናቸው ጨዋታዎች በሙሉ ለእኔ ጥሩዎች ናቸው።”

ስለቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ተጋላጭነት

” ይህ የግድ የሚሆንና ወደፊትም የሚቀጥል ነገር ነው፤ በተቃራኒ የሜዳ ክፍል ተጨማሪ ተጫዋቾችን ጨምረህ መጫወት የምትፈልግ ከሆነ ቦታህን መግፈት የግድ ነው። ያለበለዚያማ ቦታህን መክፈት የማትፈልግ ከሆነ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ተጋጣሚ ክልል መላክ አትችልም፤ ተጨማሪ ሰዎችን የማትልክ ከሆነ ደግሞ በተቃራኒ የሜዳ ክፍል ጫና ፈጥረህ መጫወት አትችልም። በዚህ ሂደት የተከፈቱ ቦታዎች መገኘታቸው የግድ ነው። ይህን ለማረም አንደኛ ስህተቶች መቀነስ ሁለተኛ ስህተት ከተሰራ በኋላ የተከፈቱትን ቦታዎች ቶሎ ለመዝጋት ጥረት ማድረግ ነው። የተከፈቱ ቦታዎች ሲገኙ ነው የተቃራኒ ቡድን መልሶ ማጥቃትን ለማስጀመር የሚሞክረው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ