ስለ አፈወርቅ ኪሮስ ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

ብዙዎች “ለእግርኳስ የተፈጠረ ሰው ነው” ይሉታል። እግሩ ላይ ኳስ ሲገባ የሚያምርበት እና ለአንድ ክለብ ከሃያ ዓመት በላይ የዘለቀ ስኬታማ ቆይታ ያደረገው፤ የመብራት ኃይል ክለብ ምልክት ተደርጎ የሚወሰደው የዘጠናዎቹ ድንቅ ሁለገብ ተጫዋች አፈወርቅ ኪሮስ ማነው ነው?

ኢትዮጵያዊ ማልዲኒ እያሉ ይጠሩታል። ከመብራት ኃይል D ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ የዘለቀ ስኬታማ ዓመታቶችን አሳልፏል። ገና በብላቴና ዕድሜው ወላጅ አባቱ አቶ ኪሮስ ከፍተኛ ድጋፍ ታክሎበት መብራት ኃይል የD ታዳጊ ቡድን በመቀላቀል የእግርኳስ ህይወቱን ጅማሮውን አድርጓል። በጊዜው የመብራት ኃይል አሰልጣኝ የነበረው ጋሽ መንግስቱ ወርቁ ከዋናው ቡድን አሰልጣኝነቱ በተጓዳኝ ታዳጊዎችን የመመልመል ስራ ይሰሩ ስለነበር በ1979 ዓ/ም ከ2000 ልጆች መሀል እርሱ እና ወንድሙ ጨምሮ 25 ተጫዋቾች የመብራት ኃይል ታዳጊ ፕሮጀክት እንዲቀላቀሉ ሆኗል። እንዲህ ብሎ የጀመረው የአፈውርቅ ኪሮስ እና የመብራት ኃይል ቁርኝት የሌላ ክለብ ማልያን ሳያጠልቅ ለአንድ ክለብ ታምኖ ከመልካም ስብእና ጋር በስኬት እንደተወደደ ጣፋጭ የሆኑ ከሀያ ዓመት በላይ መዝለቅ የቻለ ድንቅ ጊዜን አሳልፏል።

ከእርሱ ጋር በመብራት ኃይል ቤት አብረው ከተጫወቱት መካከል አንዋር ያሲን (ትልቁ) አፈወርቅ ኪሮስን እንዲህ ይገልፀዋል። “ለፈለግከው አጨዋወት መጠቀም የምትችለው ተጫዋች ነው። ረጅም ኳስ፣ አጭር ኳስ ልጫወት ካልክ አፈወርቅ ኪሮስን መጠቀም ትችላለህ። በተለይ ረጅም ኳስ አጠቃቀሙ፣ የቅጣት ምት ችሎታው በአጠቃላይ ልዩ ተስዕጦ ያለው ተጫዋች ነው”። ይለዋል።

አፈወርቅ ከመብራት ኃይል ጋር በዋንጫ የታጀቡ በርካታ የስኬት ዓመታትን አሳልፏል። በዋናነት 2 የሊግ፣ 1 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና፣ 1 የጥሎማለፍ እንዲሁም 3 የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ከቡድኑ ጋር አንስቷል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከ1988 እስከ 1995 ድረስ በተጫወተበት ዘመን በ1994 ከሀገር ውጭ የሴካፋን ዋንጫን ለመጀመርያ ጊዜ ባነሳው ቡድንው ውስጥ ሁለተኛ አንበል በመሆን የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር።

ለአንድ ክለብ መዝለቅ የቻለው አፈወርቅ በብዙዎች የሚወደድ ምርጥ ተጫዋች መሆኑን ከልጅነት እስከ እውቀት ኤልፓን ከልቡ የሚደግፈው ዳንኤል ብስራት አፈወርቅን እንዲህ ይገልፀዋል። “እሱን በአጭሩ መግለፅ በጣም ይከብዳል። አፈወርቅ የማልያ ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ ምሳሌ መሆን የሚችል፤ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጭ ፍፁም ምስጉን የነበረ፤ በወጥ አቋም ለክለቡ ባለው ፍቅር መስዋዕትነት የከፈለ ሁለገብ ተጫዋች ነው። በእኛ በኤልፓ ደጋፊዎች ዘንድ ሁሌም የሚታወስ ድንቅ ተጫዋች ነበር። ”

በጨዋታም ሆነ በልምምድ ወቅት ቀልድ የማያውቅ፣ የሚሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ የሚወጣ፣ በክለቡ ውስጥ የሚመጡ ታዳጊዎችን ከልምዱ ሳይሳሳ እያካፈለ የሚያበረታታ፣ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀሙ እጅግ የተሳካ እንደሆነ ብዙዎች የሚመሰክሩለት አፈወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከ1988 እስከ 1995 ድረስ ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን በተጫወተበት ዘመን በተለይ በ1994 ከሀገር ውጭ የሴካፋን ዋንጫን ለመጀመርያ ጊዜ ባነሳው ቡድንው ውስጥ የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር። በ1987 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመዘዋወር ከጫፍ ደርሶ የነበረ ቢሆንም በመጨራሻ ዝውውሩ ሳይሳካ የቀረበትን ሁኔታ በአንድ ክለብ ታምኖ እንዲጫወት እንደመልካም አጋጣሚ እንደሚቆጥረው ይናገራል።

የመብራት ኃይልን የልብ ደጋፊ ከመሆን ጀምሮ ክለቡን ፕሬዝደንትነት እስከመምራት የደረሱት አቶ ኢሳያስ ደንድር አፈወርቅ ኪሮስ የተለየ ተጫዋች መሆኑን እንዲህ ይናገራሉ። ” እርሱ ለእግርኳስ የተፈጠረ ለሚወደው ኤልፓ በተለየ ሁኔታ ከሜዳ ውስጥም፣ ከሜዳ ውጭም ሟች የነበረ ወደ ክለቡ ለሚመጡ ታዳጊዎች እንደ ወንድም የሚንከባከብ የፍቅር ሰው የነበረ። ለክለቡ መሆን የሚገባውን ሁሉ ሳይሳሳ የሰጠ፣ በጣም ዲሲፒሊንድ የሆነ፣ አቋሙ ሳይዋዥቅ ረጅም ዓመት የተጫወተ፣ ለአንድ ክለብ የታመነ ለብዙዎች ምሳሌ መሆን የሚችል ልዩ ስብዕና ያለው እጅግ የተለየ ምርጥ ተጫዋች ነው።”

አፈወርቅ ኑሮውን በአሜሪካ ካደረግ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን በዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ ተጫዋቾች አምዳችን ከሚኖርበት ሀገር በስልክ አግኝተነው ይሄን አካፍሎናል።

“በመጀመርያ አስታውሳችሁ ለቃለ መጠይቅ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ። ኤልፓ ውስጥ የነበሩኝ ስኬቶች በርካታ ናቸው። በዋናነት ገና እንደገባው ብዙም አስተዋፅኦ ሳይኖረኝ ይመስለኛል አንድ ጨዋታ ተሰልፌ ተጫውቼ 1985 ላይ ኤልፓ ከ32 ዓመታት በኋላ ዋንጫ ሲያነሳ የቡድኑ አባል ነበርኩ። ከዛ በኋላ ብዙ ዋንጫዎችን አንስቻለው። ሊጉ በአዲስ መልክ ሲጀመር በ1990 የመጀመሪያውን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስቻለሁ። ከሁሉም ግን ለኔ ትልቅ ቦታ ያለው በ1993 የሳካነው ዋንጫ ነው። ሁሉንም ዋንጫዎች እና የግል ክብሮች ነበር ያሳካነው። 1993 የኤልፓ ዓመት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ያን ጊዜ መቼም አልረሳውም። በዛ ሰዓት አምበል ነበርኩ፤ ቡድኑን እመራ ነበር። ብዙ መስዕዋትነትም ከፍለናል። ቡድኑ ስብስቡ በጣም ጥሩ ነበር ለመሰለፍ ብዙ ፉክክርም ነበር። ስኬቱ እንዲመጣም ይሄ ነገር አስተዋፅዖ ነበረው።

“በዚህ ዘመን ቢሆን አደርገው ነበር። ያኔ አላደረኩትም ብዬ የማስበው እኔጃ በጊዜው እኔ የተቻለኝን ያቅሜን ሁሉ አድርጊያለው ብዬ ነው የማስበው የሚያስቆጨኝም ነገር የለም።

“በአንድ ክለብ እስከ እግርኳስ ማብቂያ ጊዜ መዝለቅ በጣም ከባድ ቢሆንም መጀመሪያም ኳስ ስጀምር የኤልፓ ሰራተኛ ልጆች በሚል ፕሮጀክት ተጀምሮ ነበር እና በዛ ፕሮጀት ውስጥ ገብቼ እጫወት ነበር። ያንን ያደረጉትም ‘አባቶቻቸው እዚህ በመሆናቸው ክለቡን ለረጅም ጊዜ ሊያገለግሉ ይችላሉ’ ከሚል አንፃር ነው። በዛ ምክንያት ተጀመረ። በወቅቱ ጋሽ መንግስት ወርቁ ነበር ክለቡን የሚያሰለጥነው ፤ እኛንም በጎን የመለምል ነበር። ከ2000 ልጆች 25 ልጆች ተመለመልን ፤ እኔና ወንድሜም መካተት ቻልን። እኔንም አምበል አድርጎኝ ነበር። ነፍሱን የማረው መንግስቱ አሁን በህይወት የለም። መጀመሪያ የተመለመልኩት በእሱ ነበር። እየተጫወትኩም በሂደት እያደኩ ከD እስከ A ደረስኩኝ። 1987 ላይ ወደ ጊዮርጊስ ለመዘዋወር ጫፍ ደርሼ ተመለስኩ። ያ መሆኑ አሁን በጣም ያስደስተኛል በምወደው ክለብ መለያ ብቻ ተጫውቼ ማሳለፌ የተለየ ስሜት አለው። ምንም የቀረብኝም ነገርም የለም።

“በታዳጊዎች ላይ ስላለኝ መልካም አርያዓነት… እኔ ባደኩበት ዘመን ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። ታዳጊዎች ብዙ ዕድል በማያገኙበት ሰዓት ነበር እኛ ያደግነው። የወቅቱ የእግርኳሱ ከባቢ ውስጣችን ፍርሀት ይፈጥር ነበር። እና ያን ነገር አልፌ ከወጣሁ በኋላ ለሚመጡት ታዳጊዎች ያ ስሜት ውስጣቸው እንዳይፈጠር እና እንዳይሰማቸው ብዙ ጥረት አደርግ ነበር። እንደ ታላቅ ወንድም ነበር የምመክራቸው። እነሱም እግዚአብሔር ይስጣቸው የምለውን ይሰሙኝ እና ያከብሩኝ ነበር ፤ እኔም እንደዛው።

“በብሔራዊ ቡድን ለሰባት ዓመታት ተጫውቼያለሁ። መጥፎም ጥሩም ጊዜያትን አሳልፊያለሁ። ሩዋንዳ ላይ የሴካፋን ዋንጫ ስናነሳ ሁለተኛ አምበልም ነበርኩ። ያም ትልቅ ስኬት ነው ለኔ። የመሬት ስጦታም ተሰጥቶን ቤት ሰርቼ እንደማስታወሻ ተቀምጧል። ትልቅ ትውስታዬ ነው። ከሀገር ውጪ ዋንጫ ያነሳ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነበር። ለየት ያለ ስሜት ነበረው።

“የቆሙ ኳሶች አጠቃቀሜን በተፈጥሮ ያገኘሁት ነው ብዬ ነው የማስበው። ከልጅነቴ ጀምሮ የቆሙ ኳሶች ላይ ጎበዝ ነበርኩ። ከልምምድ በፊት እና በኋላ ረጃጅም ኳሶችን መምታት የቆመ እንጨትን አልሞ መምታት ነገሮችን እሞክር ነበር። ያ ያ ነገር የነበረኝን ችሎታ አዳብሮልኛል። ልምምዱ ችሎታዬን ይበልጥ እንዳጎለበት ረድቶኛል።

“ሁለገብ ተጫዋች የመሆኔ ሚስጢር እኔ ይበልጥ መሀል ላይ ስጫወት ነው ምቾት የሚሰማኝ። ወደ ኋላ የተመለስኩት በጋሽ ሀጎስ ምክንያት ነው። ነፍሳቸውን ይማረው ጋሽ ሀጎስ አንዋር ሲራጅ ከሀገር ውጪ ወደ ኦማን ለመሄድ በሂደት ላይ ሆኖ ወደ ዝግጅት ከሄድን በኋላ ወደዛ ሲሄድ ምርጫ ስላልነበራቸው ቁጭ ብለን ለሁለት ሰዓት ያህል አወሩኝ እና ‘ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለው ወደ ኋላ ተመልሰህ ይሄን ቦታ ሙላ’ ሲሉኝ እኔም ለእሳቸው ትልቅ አክብሮት ስለነበረኝ የእሳቸውን ቃል ተቀብዬ ወደ ኋላ ተመለስኩ እና በዛውም ቤታዬ አደረኩት እና ለረጅም ጉዜ ስኬታማ ሆኜ ተጫወትኩበት። አሰልጣኞች በሚፈልጉት ቦታ ላይ እንድጫወት ሲያዙኝ ወደ ኋላ አልልም በዚህም ግራ መስመር ላይም በተለያዩ ቦታዎች ለመጫወት ችያለው።

“እኔ በህይወቴ የተደሰትኩበት ቀን 1993 ላይ ኤልፓ በነበረው ቡድን ውስጥ በአንድ ዓመት ውስጥ የሊጉን ሁሉንም ክብሮች ዋንጫውን ፣ ኮከብግብ አግቢ ፀባይ ዋንጫ ጭምር ያሳካንበት ያ ጊዜ ለኔ ሁሌም ልዩ ቦታ የምሰጠው ነበር። በዛን ጊዜ የቡድኑ አምበል ነበርኩ። ቡድኑን እመራ ነበር ብዙ ኃላፊነትም ነበረብኝ እና ያን ሁሉ ነገር ተወጥቼ ዓመቱ በድል መጠናቀቁ ሁሌም በውስጤ ያለ ነው። በመብራት ኃይል ደጋፊዎች አዕምሮ ውስጥም ሁሌ የሚነሳ ይመስለኛል።

“ከኤልፓ ስወጣ የተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ በጣም አስከፍቶኝ ነበር። ምክንያት ኤልፓ ከልጅነት ጀምሮ የተጫወትኩበት ኳስን ጀመሬ ያቆምኩበት ክለብ ነው። እንደሁለተኛ ቤቴ ሆኖ ነው የሚሰማኝ። ከመስሪያ ቤቱ እና ከክበቡ ሰራተኞች ጋር የነበረው ቅርርብ ልብ የሚነካ ነበር። እንደቤተሰብ ነው ሁሉም ሰው ይነከባከበኝ የነበረው እና ያንን ስታይ በአንድ ክለብ ውስጥ ብቻ መጫወት ምን ያህል የተለየ ስሜት እንዳለው ያሳይሀል። አሁንም በዛ ጊዜ የነበሩትን ሰዎች ሁሌ እንዳሰብኳቸው እና እንዳመሰገንኳቸው ነው። መጨረሻ ላይ የተፈጠረው ነገር ግን የሚያሳዝን ነው። የኔን የኳስ ታሪክ ለማበላሸት የተደረገ ነገር ነው። ሊደብቁት እንኳ ቢችሉ እስከ መጨረሻው ሊያጠፉት አይችሉም። በወቅቱ በነበረው የክለቡ ስራ አስኪያጅ ነው ነገሮቹ ሁሉ የተደረጉት። እሱ ወደኛ ክለብ የተጫዋቾች ኃላፊ ሆኖ ሲመጣ እኔም አስተያየት ተጠይቄ ነበር። እኔ ስለማውቀውም ወንድሙም የኤልፓ ተጫዋች ስለነበር (ነፍሱን ይማረው አሁን በህይወት የለም) ‘ጥሩ ነው ፤ ተጫዋች ሆኖ አሳልፏል ወንድሙም ለኤልፓ ተጫውቷል’ ብዬ ለኮሚቴዎቹ ምላሽ ሰጥቼ ነበር።’ እና ሥራ አስኪያጅ ነበር። ብዙ ጊዜ በተጫዋቾች በኩል ችግሮች ሲኖሩ አብዛኞቹ ወጣቶች ስለነበሩ እኔ እና ፀጋዘአብ ነን የምንጋፈጠው ፤ አምበልም ስለነበርን። እናም የሚጠየቁ ነገሮችን ከማቅረብ ወደኃላ አልልም ነበር። ግዴታችንን እስከተወጣን ድረስ መብታችንንም መጠየቅ ይኖርብናል። በብዛት ግን የኔን ሳይሆን የሌሎችን መብት ለማስከበር ነበር የምጥረው። እኔ የቋሚ ስራ ደመወዝ ስለነበረኝ ብዙም አልቸገርም ነበር። ወጣቶቹ ግን ወር በገባ በሃያ እና በሃያ አምስት ቀን ነበር የኪስ ገንዘብ የሚሰጣቸው እና ይቸገሩ ነበር ፤ ይህን እጠይቃለሁ። የሚሰጠው መልስ ተመሳሳይ ሲሆን ግን ግጭት ይፈጠራል። በዛ ምክንያት እንጋጭ ነበር። ትክክለኛ ጥያቄ ነበር የጠየኩት ልጆቹ በጊዜው ደመወዛቸው ሊከፈላቸው ይገባ ስለነበር። ይሄ ጥያቄ ግን እሱን አላስደሰተውም። ብዙ ጊዜ እኔ ስለነበርኩ የምናገረው እኔ ላይ ነበር ትኩረቱ። በጊዜው ለነበረው የውጪ አሰልጣኝም አንድአንድ ነገሮች ይነግረው ነበር። ነገር ግን እኔ ልምምዴን በአግባቡ ሰርቼ ህግ አክብሬ የምጫወት ሰው ስለነበርኩ ምንም ማድረግ አልቻሉም ነበር። በወቅቱ ነገሮቹ ስላልተስማሙኝ ወደማቆሙም እየቀረብኩ ነበር። የውጭ ፕሮሰሴም ወደማብቂያው ላይ በመሆኑ ወደ ዝግጅትም እንደማልሄድ ገልፅኩላቸው። እነ ጋሽ አርዓያ ተስፋይ አናግረውኝ ነበር። ዝግጅት እንደማልሄድ እንጂ ኤምባሲ እንደምገባ አልገለፅኩላቸውም ነበር። ከዛም ዝግጅቱን ቀረው ኤምባሲ ገብቼም ቪዛውን እንዳገኘው ወደ መብራት ኃይል ነበር የሄድኩት ፤ ያለውን ነገር አሳውቂያቸው መልቀቂያ ለመቀበል። ከዛ በኃላ ብዙ ዓመት በማገልገሌም እኔም ሌሎች ሰዎችም ሽኝት ይኖራል ብልን ጠብቀን ነበር። ነገር ግን ምንም አልነበረም። ጋሽ አርአያ አናግሮኝ መሄጃዬን በሦስት ቀናት አራዝሜም ነበር። እነሱ እንኳን ጥረት አድርገው ነበር። ሆኖም በወቅቱ ስራ አስኪያጁ ይሄን አጋጣሚ ተጠቅሞ ነገሩን አራዝሞ አስቀረው። ከመምጣቴ በፊት ሬድዮ ላይ በቀጥታ ስርጭት ገብቼ ስናገር እሱም ነበር። ሽኝት እንደሚኖር ገልፆ ነበር። ያው ተጫዋቾች እና እነ ጋሽ አረአያ ለክለቡ የነበረኝ ነገር ስለሚያውቁ የክለቡን መለያ በስጦታ መልክ ሰጥተውኛል። ከነበረኝ ነገር አንፃር በዚህ መልኩ ከኤልፓ እወጣለው ብዬ አላስብም ነበር። ለኔ ብቻ ሳይሆን ለወጣቶቹም ትምህርት ይሆን ነበር። ምክንያቱ ለረጅም ጊዜ ያገለገለን ተጫዋች በአግባቡ ካልሸኘኸው እነሱስ ምን ሊሰማቸው ይችላል ? የተለየ ነገር ጠብቄ ሳይሆን በፍቅር እና በምስጋና መለያየት ለወጣቶቹ የወደፊት የክለቡ ቆይታ ካለው አስተዋፅዖም አንፃር ነበር። በቃ በዚህ አዝኜ ወደ ኳስ እንዳላስብ ሆኜ የወጣሁበት ወቅት ነበር። አሁን ግን ባለቤቴ እና ልጄቼ አዲስ አበባ በመጡ ሰዓት የክለቡ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ኢሳይያስ ደንድር በይቅርታ መልክ ለባለቤቴ፣ ለልጆቼ ፣ ለአባቴ እና ለኔ የመለያ ስጦታም አበርክተዋል። የዘመናት የልጆቼም ጥያቄ መልስ አግኝቷል። እኔም ይቅርታውን ተቀብዬዋለው። በዛ ምክንያት ሁሉንም ነገር ትቼዋለው እንጂ ልብ የሚሰብር ነገር ነበር የተደረገው።

“በኤልፓ ቆይታዬ የማልረሳው አጋጣሚ እኔ ወደ ዋና አሰላለፍ ከምምጣቴ በፊት ቦታው ላይ የነበረው ኃይሌ ኳሴ ከኪራይ ቤት ወደ ኤልፓ ገብቶ ነበር። በወቅቱ እሱ የመሐል ሜዳ ተጫዋች ነበር። ሁል ጊዜ ልምምድ ቦታ ላይ ‘የኔን ቦታ የሚረከበው አፈወርቅ’ ነው ይል ነበር። ያ ነገርም እንዳለው ሆኗል። በአንድ ወቅት እኔን ከህዝብ ያስተዋወቀኝ እና ለዚህ ያበቃኝ አሰልጣኝ ተስፋዬ ቱታ ነበር። ተስፋዬ ቱታ የኔን ችሎታ እንዲወጣ እና እንዲታወቅ ያደረገ አሰልጣኝ ነው ፤ በጣም ላመሰግነውም እፈልጋለሁ። እና በአንድ ወቅት ከሱ ጋር አለመግባባት ይፈጠርና ትንሽ ተጋጭተን ልምምድ ጥዬ ልወጣ ስል ኃይሌ ካሴ ሲያገኘን ፊቴን አይቶ ‘ምን ሆነህ ነው?’ ሲለኝ ነገርኩት። ‘አይሆንም ልብስህን ቀይረህ ና !’ አለኝ። እንደታላቅ ወንድምም ስለማየው አክብሮቱም ስላለኝ ያለኝን ሰምቼ ቀይሬ መኪናው ውስጥ ገባው። ከዛ ልምምድ ሰርተን የእርስ በእርስ ጨዋታ ተጀመረ። እኔ ወደ ሜዳ ስገባ ነገሮችን እረሳለሁ። በኳስ ሁሉን ነገር ነው የምረሳው። ህይወቴ ነው የምለውም ለዛ ነው። ጨዋታው እየተደረገ ሳለ ኃይሌ ተቃራኒ ቡድን ነበር ከዋና ተሳላፊዎች ጋር የኛ ቡድን ደግሞ የተቀያሪዎች ነበር። እየተጫወትን ሳለ በመሀል መጥቶ ይነካኝ እና ‘አፈወርቅ ሁሉን ነገር ረሳኀው አይደል ? ‘ አለኝ (ሣቅ)። ይህን ሁሌም አነሰዋለው። ኃይሌ እኔን በደንብ ያነበኝ ነበር።

“ረጅም ዓመት የመጫወቴ ምክንያት አንደኛ ልምምዴን በሚገባ እሰራለው ፣ እረፍት አደርጋለው ፣ ራሴን እጠብቃለሁ ፣ ለኳስ መደረግ ያለባቸውን አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ አደርጋለው። ኳስ በጣም እወዳለው ኳስ ህይወቴ ነበር። ደግሞም የምተዳደርበት ሙያም ነበር። ስለዚህ ሁል ጊዜ ስራዬን አከብራለው አሰልጣኞቼ እና ለተጫዋቾችንም አከብራለው። ኳስ ተጫዋች በደንብ መጫወት ከፈለገ ልምምዱን ማሟላት አለበት። አሰልጣኙ የሚሰጠውን ነገር ሁሉ በአግባቡ መከታተል አለበት። እኔ አሰልጣኜ የሚሰጠኝን ልምምድ አከብራለው ፤ አልቃወምም። ማንም አሰልጣኝ በኔ ላይ ከተሾመ እሱ ለኔ አሰልጣኜ ነው። ስለዚህ የሚሰጠኝን መመሪያ ተከትዬ ሁሉን ነገር አደርጋለው። እናም አክብሮት ፣ ፍቅር እና ኳስ መውደድ ይመስለኛል ለረጅም ዓመታት እንድጫወት ያደረጉኝ።

“አሜሪካ ቺካጎ ነው የምኖረው። ከመጣሁ በኋላ አንዴ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሻለው። ግን የመጣሁባቸው ብዙ የግል ጉዳዮች ስለነበሩኝ እነሱ ላይ ነበር ያተኮርኩት ወደ ስታዲየም አካባቢ ሄጄ ኳስ የማየትም አጋጣሚው አልነበረኝም። አሁን የሁለት ልጆች አባት ነኝ ፤ የ 11 እና የ12 ዓመት ልጆች አሉኝ። ትልቁ አሮን አፈወርቅ ትንሹ ማቲው አፈወርቅ ይባላሉ። ልጆቼ በደም ነው መሰለኝ ኳስ ይወዳሉ። በዚያም ምክንያት ህፃናቶችን ሰብስቤ አሰለጥናለሁ። ትንሹ ልጄ ኳስ ጎበዝ ነው ከኔ ጋር የሚመሳሰሉ ነገሮችም አሉት። እኔን ይገልፃል ብዬ አስባለው። ትልቁም ጎበዝ ነው እያሰለጠንኩ ነው ያመጣሁት እንጂ መጀመሪያ ለኳስ እምብዛም ነበር። አሁን ግን በደንብ ይከታተላል። ትልቁ የሮናልዶ ትንሹ ደግሞ የሜሲ አድናቂዎች ናቸው። ቤታችን አንዳንዴ በሁለቱ ተጫዋቾች ዙሪያ ጭቅጭቅ ይፈጠራል (ሣቅ)።

“ወደፊት አሰልጣኝ ስለመሆን እስካሁን ድረስ ስለአሰልጣኝነት ምንም አላስብም። ያው የራሴ የቤተሰብ ኃላፊነት ስላለብኝ እሱን እየተወጣው ነው የምገኘው። ግን ኮርሶች ለመውሰድ አስባለው። ለማሰልጠን ሀሳቡ ባይኖረኝ እንኳን እዚህም ልጆች ላይ እየሰራው ስለሆነ ወረቀቱን መያዝ ስላለብኝ ነው። የወደፊቱን ደግሞ የምናየው ይሆናል። እስካሁን ግን የአሰልጣኝነት ህይወት ሀሳቤ ውስጥ የለም።

“ኤልፓ አሁን ያለበትን ሁኔታ አምኖ መቀበል ይከብዳል። በአሁን ሰዓት ታች ወርዶ በዚህ ሁኔታ ላይ መገኘቱን ለመቀበል ይከብደኛል። ግን በኳስ ዓለም ላይ መውረድ እና መውጣት ያለ ነው። አሁን ግን ሁለት ዓመት ሆነው መሰለኝ ። ቀደም ሲል እንኳን ብዙም አልከታተልም ነበር የወጣሁበትም መንገድ ብዙዎች እንደሚያስታውሱት በጥሩ ሁኔታ አልነበረም። ያ ነገር ከኳሱ እንድርቅ አድርጎኝ ነበር ያበሳጨኝም ስለነበር። አሁን ላይ ግን ኤልፓን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ማየት ቢከብድም አንዴ ከወረደ እንዴት ይመለስ የሚለው ነው መታሰብ ያለበት። ኤልፓ በፊትም የተለመደው አንድ ሳይሆን 11 ተጫዋቾችን አንድ ማድረግ ላይ ነው የሚመሰረተው። ተጫዋቾች የሚፈልጉት ነገር እና ችግሮቻቸውን በመነጋገር መረዳትም ያስፈልጋል። መከፋፈሎችም እንዳይመጡ ቶሎ ቶሎ ችግሮችን መቅረፍም ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። ያ ነገር ከሆነ የበፊቱ ነገር በሂደት ይመለሳል ብዬ አስባለሁ።

“ወደ ፊት ወደ ሀገር ቤት ስለ መምጣት ሀሳብ እሱን ወደፊት የምናየው ይሆናል። አሁን ሀሳቤ ልጆቼን መጨረሻ ላይ ማድረስ ነው። ወደፊት የሚሆነውን አብረን የምናየው ይሆናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: