የ8ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች !
ምድረ ገነት ሽረ ከ ሀዋሳ ከተማ
በዛሬው ዕለት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ቀን 7:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ምድረገነት ሽረን ከ ሀዋሳ ከተማ ጋር ያገናኛል። እስከ አሁን ካደረጓቸው ጨዋታዎች ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ በሁለቱ ተሸንፈው በሶስቱ አቻ የሆኑት ምድረ ገነት ሽረዎች ባሳለፍነው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ላይ የተቀዳጁቱን ድል ለመድገም ጠንካራ የሆነ አደረጃጀት ይዞ ከመጣው ሀዋሳ ከተማ ጋር ጠንከር ያለ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ይታመናል። በተመሳሳይ አራት ጨዋታዎችን በማሸነፍ በሁለቱ ተሸንፈው በአንዱ አቻ የወጡት ሀዋሳ ከተማዎች በሰባተኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ ሽንፈት ካስተናገዱበት ማግስት ወደ ድል ለመመለስ ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሽረ ምድረገነት በኩል የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ከሆነው ብሩክ ሐድሽ በስተቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በሀዋሳ ከተማ በኩል እስራኤል እሸቱ በጉዳት ሽመልስ በቀለ ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይኖሩም።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ አምስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ ቀሪውን አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። ምድረ ገነት ሽረዎች 10 ግብ ያስቆጠሩ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው 12 ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል።
ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የሊጉ መሪ የሆነውን ሲዳማ ቡናን ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 10:00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያገናኝ ሲሆን በዋና አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እየተመሩ ድንቅ የሆነ የውድድር አመትን እያሳለፉ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በሊጉ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች በአምስቱ አሸንፈው በአንድ ተሸንፈው በአንዱ ነጥብ ተጋርተው አስራ ስድስት ነጥቦችን በመሰብሰብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ አንደኛ መሆን የቻሉ ሲሆን በተቃራኒው የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን የነበረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ እየተመሩ በሊጉ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች በአንድ ጨዋታ ተሸንፈው በአምስቱ አቻ በመውጣት በአንዱ ብቻ ያሸነፉ ሲሆን ቡድኑ የወጥነት ችግር እንዳለበት በተለያዩ ጨዋታዎች ያስመለከተን ሲሆን ዛሬ ሁለተኛ ድላቸውን ለማሳካት ከጠንካራው እና ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በዛሬው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም። በሲዳማ ቡና በኩል የቡድን መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ20 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አመዛኙ 11 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነው። ሲዳማ 5 ጨዋታ ሲያሸንፍ ንግድ ባንክ ደግሞ 4 አሸንፏል። በግንኙነታቸው ንግድ ባንክ 24፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ 22 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና
በዋና አሰልጣኝ አብይ ካሳሁን እየተመሩ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አዲስ አዳጊውን ሸገር ከተማን ከመመራት ተነስቶ ድል ማድረግ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ባለፈው የውድድር አመት የነበራቸውን ጠንካራ አቋም በዚኛው የውድድር አመት ጅማሮ መድገም የከበዳቸው ሲሆን በሊጉ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ በማሸነፍ በአንዱ ነጥብ ተጋርተው በአራቱ በመሸነፍ ሰባት ነጥብ ሰብስበው በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 15ኛ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ያሉበትን ደረጃ ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይ አሰልጣኝ ኪሊድ መሐመድን የቡድናቸው ዋና አሰልጣኝ አድርገው የሾሙት ሀድያ ሆሳዕናዎች ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ በማሸነፍ በአራቱ ነጥብ ተጋርተው በሁለቱ በመሸነፍ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ 16ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።
ሁለቱም ቡድኖች በተገናኙባቸው 12 ግንኙነታቸው ነብሮቹ 5 ቡናማዎቹም በተመሳሳይ 5 ጊዜ ሲያሸንፉ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ከተቆጠሩት 22 ጎሎች ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕና 11 ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ 11 ግቦችን አስቆጥረዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ይታገሱ ታሪኩ በጉዳት ምክንያት የማይኖር ሲሆን በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ ዳግም ንጉሤ ፣ ሄኖክ አርፊጮ እና ጄይላን ከማል በጉዳት ምክንያት አይኖሩም።


